የበረከትን ከጥረት ድርጅት ጋር በተያያዘ ሙስና መታሰር ዜና እንደሰማሁ በፌስቡክ ገፄ ላይ መደነቄን ከመግለፅ አልተቆጠብቅኩም። በረከት በመንግስት ሥልጣን ላይ በቆየባቸው የሩብ ምእተዓመት ዘመናትና፣ ይህ ሥልጣን በውስጡ ካጀበው የሰብአዊ መብት ረገጣና የሰቆቃ ታሪክ አንፃር ሲታይ፣ የሥርአቱ ጎምቱ አሳቢና ተከላካይ የሆነው ሰው ከደሙ ንፁህ ነው በሚል አልነበረም እስሩ የከነከነኝ ። በረከት የሚጠየቅባቸው የድህረ ምርጫ 97 ግድያዎች ፣ በንግድ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበርነቱ ለአድልኦ የተመቻቹ መጠነ ቢሊዮን ብድሮች ወዘተ ብዙ ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ።
ስለበረከት ሁሌም ስናገር ከነዚህ ሃላፊነቶቹ የሚመነጩ ተጠያቂነቶች አይኖሩበትም በሚል አልነበረም። ሁሌም በበረሃ የተንከራተተውን፣ ገና የ16 ዓመት ወጣት እያለ የወጣ የወረደውን ለህዝብ የመቆም ወገንተኝነት፣ በትግሉ ውስጥ ታላቅ ወንድሙን ማጣቱን፣ ደክሞ ያደራጀው ድርጅትና የታገለለትም ህዝብ በኤርትራዊነቱ ይሆን ይበልጥ የሱን ሃጢያት የሚያበዙበት በሚል ፍርሃትና መሰቀቅም ጭምር ነበር ።
በአደባባይ ወጥቼ “የበረከትና አዲሱ ሳቃቸው ይናፍቀኛል” ስል ከሚጠሉት ይበልጥ ማንጓጠጥ እንደሚደርስብኝ አጥቼው፣ ወይም በረከት ራሱ “እኔ በህይወቴ እያለሁ ጀቤሳ ይህችን መሬት አይረግጣትም” ማለቱን ስላልሰማሁ ወይም ስለማላውቅም አይደለም ። ተደጋግሞ ተነግሮኛል። እኔ የምመጣው ከተለየ ባህር ነው ። ለእኔ ፍቅር ሌላው ሲያፈቅርህ ብቻ የምትመልሰው ብድር አይደለም። የሚጠላህንም ማፍቀር ይቻላል ብዬ አምናለሁ። አጠገባችን የሌለ፣ በአፀደ ስጋ የተለየን፣ የማናውቀውን የሩቅ ሃገር ሰው ማፍቀር ይቻለናል ብዬ አስባለሁ። ፍቅር ለሌላው ሳይሆን ለራስ ነው። አንድን ሰው ስታፈቅር፣ የምታፈቅረው ለርሱ ብለህ አይደለም፣ ለራስህ ነው። በፍቅርም የደስታና የሃሴት ስሜት የሚሰማህ አንተ አፍቃሪው እንጂ ተፈቃሪው አይደለም። ለተፈቃሪው የሚተርፈው ነገር ያለ አይመስለኝም። ለበረከትም የገለፅኳቸው ሰናይ ነገሮች የግድ የሱን ተቀባይነት የሚሹ አልነበሩም። የኔ ነበሩ እንጂ።
የበረከትን መታሰር መቀበል ያቃተኝ ለሱ ካለኝ አስተሳሰብ በበለጠ፣ መታሰሩ የሚያስተላለፈው መልእክት ሽግግሩን ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል የሚል ፍርሃት ስላለኝ ነው። በንግድ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበርነቱ በመቶ ቢሊየኖች ያዝ የነበረ ጎበዝ፣ በአንዲት ከርታታ የፖለቲካ ድርጅት ኢንቬስትመንት አመራርና የኦዲት ክፍተት ሲጠየቅ ከጀርባው ፖለቲካ የለም ብሎ ለማሰብ አዳጋች ያደርገዋል። በኢህአዴግ ውስጥ አስር በሌብነት የማይጠየቁ ሰዎች ቢኖሩ በቁጥር አንድ ላይ የሚቀመጠው በረከት ይመስለኛል። ታዲያ ይህ ሰው በሙስና ታሰረ ሲባል፣ ለሰሚው ግራ ቢመስል ሊገርም አይገባም።
በሙስና ከማይጠየቁ ተራ ከሚመደቡት ጥቂት የአመራር አባላት መሃል ከመሆኑም የተነሳ፣ በረከት በሙስና ታሰረ ሲሰማ የሚበረግገውን የኢህአዴግ አመራርና ካድሬ ብዛት ማሰብ ነው። “በረከት ዘብጥያ ከወረደማ እኛን ምን ይጠብቀን ይሆን?” ብሎ የሚበረግገውን ያበራክተዋል። ይህ ደግሞ በየቀኑ እየዘቀጠ ያለውን የማንነት ፖለቲካ ይበልጥ በማጨማለቅ፣ ሽግግሩን ከድልድዩ ወደጭቃው የሚመልሰው ይመስለኛል። በተለይ መቀሌ ከትሟል የሚባለው የወያኔ ነባርና የአሁን አመራረ አባላትን ይበልጥ ተሽኪላቸውን አርቀው እንዲቆፍሩ ማንቂያ ደውል ሆኖ እንዳያገለግል እሰጋለሁ።
መቀሌን ይበልጥ ከማራቁም በላይ ግን ባለፉት 45 ዓመታት እየገነነ የመጣውን ፍትህን የፖለቲካ መሳሪያ የማድረግ፣ ፍርድቤቶችን የፖለቲካ ተቀናቃኝን ማጥቂያ የማድረግ አሰራር ልንተወው እንዳልቻልን እንዳይጠቁም እፈራለሁ። ከበረከት እስር በኋላ አቶ ገዱ በአማራው ክልል፣ ይበልጥም በአዴፓ ውስጥ፣ ይበልጥ ደግሞ በአዴፓ አመራር ውስጥ የሚፈራ ሰው ሆኖ እንዲወጣ ሊያግዘው ይችላል ብዬ አስባለሁ። በሙስና ወይም በሰብአዊ መብት ጥሰት ሊከሰስ የሚችለው በእንቅብ በመሆኑ፣ ሰጥ ለጥ ብለው እንዲገዙ ያደርጋቸው ይመስለኛል። አቶ ገዱም ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአቃቤ ህጋቸው በኩል የፈለጉትን ማሰር የሚችሉበት ሥልጣን ካላቸው፣ የሽግግሩ ጉዳይ አበቃለት ማለት ይመስለኛል። በጠቅላይ ሚኒስትሩም ዙሪያ ያሉ ባለሥልጣናት እንዲሁ በፍርሃት ዝለል ሲባሉ ምን ያህል ብለው የሚጠይቁ ታዛዦች የሚያደርጋቸው ከሆነ፣ አቢይ በመለስ መንገድ የማይሄዱበት ምክንያት የለም።
ሩብ ክፍለዘመን ስንዳክር በኖርንበት እስርቤት ውስጥ ለመመለስ መቻኮል ያለብን አይመስለኝም። ሽግግሩን ከዳር ለማድረስ ፍትህና ፖለቲካ መነጣጠል አለባቸው። የኢትዮጵያችን ትልቁ መርዘኛ ጠላት ፍትህ የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ ማገልገሉ ነው። ፍርድቤት የተቀናቃኝ ማጥቂያ ሆኖ መስራቱ ነው። በዚህ የሽግግር ወቅት ለአንዴና ለሁልጊዜ ይህን ሃገራዊ ሰንኮፍ ነቅለን ለመጣል እድል አለን። ከምእራባውያን ለመዋስ ከምንፈልገው የህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና፣ ህግ አስፈፃሚውን ሥልጣኖች ሚዛን ከመጠበቅ በላይ ሄደን፣ ምእራቡንም ሊያስተምር የሚችል የህግ ተርጓሚውን ነፃነት የሚጠብቅ አዲስ አደረጃጀት ማሰብ ይቻለን ይመስለኛል። ህግ አስፈፃሚው በምንም መልኩ በፍርድቤቶች ሂደት እጁን ሊያስገባ እንዳይችል ፊቱ ላይ ጥርቅም አድርጎ በሩን የሚቀረቅር አካሄድ ብንከተል፣ ከሽግግሩም ርቀን ብዙ የምንጓዝ ይመስለኛል።
ከዚህ እፁብ ከፍታ ከመድረሳችን በፊት ግን፣ በዚህ የሽግግር መድረክ ፍትህን እናስቀድም ብለን ብንስማማ እንኳ፣ ፍትህ የፖለቲካ መሳሪያ እንዳይሆን፣ ማ እንደሚከሰስና እንደማይከሰስ የሚወስነውን ሥልጣን ለጊዜው ከአቃቤ ህጉ ቢሮ አውጥተን በተለይ ለተቋቋመ “አጣሪ ኮሚሽን” እናድርገው። ይህን የምሞግትበት ምክንያት አለኝ። ሁላችንም በግልፅ እንደምናየው ኢህአዴግ ውስጥ መጠላለፍና ሽኩቻው እየባሰበት እንጂ ጋብ እያለ አይደለም። በመቀሌና አዲስ አበባ መሃል ያለው ልዩነት የትዬለሌ ነው። ሱማሌን በመሰሉ ክልሎችም ችግሩን እያየነው ነው ። ከመጠላለፉ በመነጨ፣ የተደመሩ ከህግ ሰይፍ የሚርቁበት፣ ያልተደመሩ ደግሞ የህግ ሰለባ የሚሆኑበት አደጋ ጥርሱን አግጦ ሃገሬው የሚያየው ነው። ስለሆነም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወዳጅ በሆነ አቃቤ ህግ ወገንተኛ ያልሆነ ፍትህ የማይታሰብ ስለሚሆን፣ የፍትህ መንገዱን እንሂድበት ከተባለ የአጣሪው ኮሚሽን መቋቋም የተሻለው መንገድ ይመስለኛል።
በእኔ እምነት ግን የሽግግር ፍትህ ከብሄራዊ እርቅ መቅደም ያለበት አይመስለኝም። ከሽግግራችን ልዩ ባህርይ በመነጨም የተነሳ፣ ከታች በህዝባዊ ትግል የተገኘ ብቻ ሳይሆን በአመዛኙ ከላይ በአመራሩ ውስጥ በመጣ የአስተሳሰብ ለውጥም ጭምር የመጣ ሽግግር በመሆኑ፣ የሚመጥነው መፍትሄ ብሄራዊ እርቅ እንጂ የበደለን ሁሉ ወደፍትህ መድረክ በመጎተት አይመስለኝም። ፍትህን የማስቀደሙ መንገድ መጠላለፉን በማበራከት ሽግግሩን ከባድ ምናልባትም ከሃዲዱ የሚያስወጣው ሊያደርገው ይችላል። የብሄራዊ እርቁ መንገድ ግን፣ ማንም ላልተገባ ጥቃት እንደማይጋለጥ በማረጋገጥ፣ ህብረተሰቡም የደረሰበትን የሩብ ክፍለዘመን ሰቆቃ የሚተነፍስበትን መድረክ በማመቻቸት፣ በዳይና ተበዳይ ፊትለፊት ተነጋግረው በዳይም ከፍርሃቱ ተበዳይም ከውስጥ ቁስሉ ጋር በግሉ መብሰልሰሉ ቆሞ፣ በይቅርባይነትና እህትማማችነት ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን እንደ ሃገር የምንቆምበትን እድል ይሰጠን ይመስለኛል። የፍትሁን ጉዳይ ያኔ፣ በደላቸው የከፋውን፣ ምናልባትም ከመክፋትም አልፎ ለመፀፀት ፈቃደኛ ያልሆኑትን ብቻ ለፍትህ በማቅረብ ሽግግሩን ለማጠናቀቅ ያስችለናል ብዬ አስባለሁ።
የነገ ሰው ይበለን!