ዘረኝነት ቆሻሻ ነው! | ከአንተነህ መርዕድ

ዘረኝነት ቆሻሻ ነው! | ከአንተነህ መርዕድ

ፈብሯሪ 2018 ዓ ም

“የጎ ፖለቲካ” “የክልል ፖለቲካ” “የማንነት ፖለቲካ” …. እያልን ልዩ ልዩ የክርስትና ስም ብንሰጠውም የዘረኝነት ክርፋቱን ልናፀዳለት አንችልም። ማንም ያንሳው ማንም ሰው ከመሆኑ ባለፈ “እነሱ”፣ “እኛ” በሚል ቅርጫት ውስጥ ክቡር የሆነውን ሰው ከትቶ በመከፋፈል የተለየ ተጠቃሚ፣ የተለየ ተበዳይ እያደረገ የሚተርከው የአገራችን ፖለቲካ አገር የሚያጠፋ የከረፋ ዘረኝነት ነው።

ጣልያኖች ዜጎቻቸውን አበሻ የማይደርስበት መኖርያ፣ መናፈሻ፣ መገበያያ… አዘጋጅተው ነበር። አባቶቻችን ይህንን ፋሺስታዊ ዘረኝነትን ተዋግተውና ሙተው በአቆዩት አገር ዛሬ የተለያየ ስም የተሰጣቸው  “የእኛ” ፋሺስቶች ብዙ ሺዎችን ገድለው ብዙ ሚሊዮኖችን አፈናቅለዋል።

ህወሃቶች ጋምቤላ፣ ኦጋዴን፣አሶሳ፣ አዲስ አበባና በመላ አገሪቱ ሲገድሉና ሲያስገድሉ ጨርሶ “ኢትዮጵያዊ ናቸው?” በሚያስብል ሁኔታ የጭካኔአቸውን ጣሪያ አገር በሚያጠፋ ዘረፋ ደምድመውታል። ህዝባዊ አመፁ ከነበሩበት ማማ አውርዶ ቢያንኮታኩታቸውም እነሱ የተከሉት መርዝ አገሪቱን ሲያጠፋ ተቀምጠን ልናይ አያስፈልግም።

ኢትዮጵያዊ አባቶቹ ባቆዩአት አገር፣ ትናንት ወጣቶቹ በአጋዚ ጥይት እየወደቁ ነፃ ባደረጓት መሬት ሰበዊ ክብራቸውን በመግፈፍ “አንተ፣ አንቺ ከዚህ አይደለህም አይደለሽም” እያሉ ሲገድሉ ሲያፈናቅሉና ሲዘርፉ የማየትን ያህል አሰቃቂ ወጀል የለም።

ያለፈውን አልፈናል። እንዴት ከወያኔ መከራ የወጣ አገር ራሱን ወደ ሌላ መከራ ያዘጋጃል? “የለውጥ ኃይል” የሚባለው ቡድንስ ምን ተዓምር መስራት ይችላል? እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያገኘውን ድል እያጠናከረ ለበለጠ መንቀሳቀስ ካልቻለና የቅልበሳ ኃይሉን ለመቋቋም ፍላጎትና ሃሞት ካጠረው ማን ሊያድነው ይችላል?

ሚሊዮን ኦሮምኛና ሶማልኛ ተናጋሪዎች ለፍተውና ደክመው በኖሩበት አገር ሲፈናቀሉ ሲገደሉና ሲዘረፉ፣ መቶ ሺዎች ከአሶሳ፣ ከጉጂ፣ ከጎንደር፣ ሲባረሩና ሲገደሉ ለመቃወምና ከጎናቸው ለመቆም የግድ የእነሱን ቋንቋ መናገር ይጠበቅብናል?

የሃረርን ህዝብ ጉረሮ አንቀው ውሃ ሲከለክሉት፣ የምዕራብ ወለጋን ህዝብ ለመግደልባንክና መስሪያ ቤት ለመዝረፍ ከአዲስ አበባ ሆነው ትዕዛዝ ሲሰጡ፣ የአዲስ አበባን ጉሮሮዋን እናንቃለን ብለው በሚድያ ሲፎክሩ ተውው! የምንልበትና የምናስቆምበት  ሃሞት ሊኖረን ግድ የአንድ ቡድን ጭምብል ማጥለቅ ይኖርብናል? ኢትዮጵያዊና ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው!

“ነገ አገር እንመራለን” ብለው የተደራጁ ፖለቲከኞች ዘረኞች ሲጮሁባቸው በፍርሃት አንገታቸውን አሸዋ ውስጥ የሚከትቱ ከሆነ “ዛሬ ካላወቃችሁን እኛም ነገ አናውቃችሁም” ልንላቸው ይገባል።

“ዐይን አፋር ልጃገረድ ከወንድሟ ታረግዛለች” እንደሚባለው በዴሞክራሲ ስም የሚምሉ ፖለቲከኞች የትናንቱን ህወሃት ለመምሰልና ለማከል “በአካባቢዬ ዝር እንዳትል” የሚል ማስጠንቀቂያ በአማራው፣ በትግራይ፣ በኦሮምያ፣ በደቡብ፣ በድሬደዋና በሃረር ከማቀንቀን አልፈው እንደሰርገኛ ጤፍ የተዘነቀውንና ሊለያይ የማይችለውን አዲስ አበቤ ለመጋለብ ኮርቻ ሊጭኑበት የትናንት አይነት መሳፍንቶች ከሁሉም አቅጣጫ ሲያቅራሩ እየሰማን ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሁሉም የኢትዮጵያ መሬት የመኖርና የመስራት ብት እንዳለው አስረግጠን መንገር፤ እምቢ ካሉ ተደራጅተን የመቋቋም ተፈጥሮአዊ ብት አለን።

ሻሸመኔ፣ ቡራዩ፣ አሶሳ፣ ጎንደር የተፈፀመው ፀያፍ ነገር የካቲ 12 ቀን ጣልያኖች የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ከፈፀሙት የከፋ ነው። ምክንያቱ ወገን በወገኑ ላይ ያደረገው አረመኔነት ነውና።

ቢቢሲ ላይ የሰማነው አጥንት ውስጥ የሚገባ ዘግናኝ ዘረኝነት “እባካችሁ ሚስቴ ከወለደች ሶስት ቀኗ ነው። ትንሽ ታገሱኝ ብዬ ስጠይቃቸው ‘ምን አገባኝ ከእኔ አልወለደች’ አለኝ አንዱ ጎረምሳ” ያሉት ሰው እንባ ምን ያህል እንደ አገር ወደታች መዝቀጣችንን ያሳያል። “ከእኔ አልወለደች” ያለው ጎረምሳ በህጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የጎስ ድርጅቶች እውነተኛ ስማቸው የዘረኝነት አስፋፊ ድርጅቶች ድምፅ ነው። በእሱ ከመፍረዳችን በፊት ተደራጂተው “እኛ” እና “እናንተ”የሚስብኩንን ነጋዴ መሳፍንት ነው መታገል ያለብን።

በለገጣፎ ዘግናኝና ኢሰብአዊ በሆነ የማፈናቀል ዘመቻ “ህጋዊ ስለአልሆኑ ገና የምናፈርሳቸው (የምናፈናቅላቸው) ብዙ ሺህ አሉ” ሲሉ ትልልቅ ባለስልጣናት በሚድያ ወጥተው ፎክረዋል። ለመሆኑ የህጋዊነት ጥያቄ ከተነሳ የእናንተን ስልጣን የትኛው ህዝብ ነፃ ድምፁን ሰጥቶ ነው ህጋዊ ያደረገው? አባይ ፀሃዬ “ልክ እናሳያችኋለን” ብለው ፎክረው የህዝብን ልክ አይተዋል። እናንተም የአባይ ፀሃዬን ቃል ቀይራችሁ ልክ እናስገባችኋለን ከሆነ ትግሉ ይቀጥላል። ሁላችንም በየልካችን እንገኛለን።

ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቃት

LEAVE A REPLY