በዙረት ካገኘሗቸው እውቀቶች አንዱን በማካፈል ወጌን ልጀምር:: ያፍሪካ ስደተኞች ያንዱን ያውሮፓ አገር ድንበር አቋርጠው ይገቡና አንድ ከተማ ውስጥ አድፍጠው ይቀመጣሉ:: በከተማው ባንድ ስፍራ ላይ መንግስት ገንብቶ ያልጨረሰው ባዶ ህንፃ ይኖራል:: ስደተኞች ከለታት አንድ ቀን ተደራጅተው ህንፃውን ወርረው ይይዙታል:: የህንፃውን አፓርታማ ተከፋፍለው መኖር ይጀምራሉ:: መንግስት እንዴት ተደፈርኩ ብሎ ለወግ ያክል ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል :: የታጠቀ ህግ አስከባሪ ልኮ አካባቢውን ይቀውጣል:: ወድያው ጠበቆች ሳምሰናይታቸውን አንጠልጥለው ከተፍ ይሉና የሰው ልጅ መጠለያ የማግኘት መብቱን ጠቅሰው ለስደተኞቹ ይከራከራሉ:: የማታ የማታ ጠበቆች ያሸንፋሉ:: “ወራሪዎች ” ኑዋሪዎች ሆነው ይቀጥላሉ::
አውሮባዎች በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምን እያሉን ነው:- ያለህግና ደንብ አገር አይኖርም:: ይሁን እንጂ ዞሮ ዞሮ ህግና ደንብ ሰውን ለማገልገል የተፈጠሩ መሆናቸውን አንርሳ:: ከርህራሄና ከፍቅር ተቃራኒ የቆመ ህግ መሻሻል ወይም መወገድ አለበት::
መድረሻ ያጡ ዜጎች : በለገ ጣፎ : ጠፍ መሬት አግኝተው: ቤት ሰርተው ቤተሰብ መስርተው ግብር እየከፈሉ ይኖሩ ነበር:: አስተዳደሩ ግሪደር ልኮ ቤታቸውን አፈረሰባቸው:: ለምን? ” ለአረንጓዴ ቦታ የታጨውን ቦታ በህገወጥ መንገድ ሰሩበት!! ህግ ህግ ነው “ጥሩ!! ግን ዜጎችን ከቤታቸው አውጥቶ ጎዳና ላይ መጣል ሌላ ህገወጥነት አይሆንም?
መንግስትና ህዝብ በጋራ ድል የሚያረጉበት መፍትሄ በጊዜ ይፈለግ!! ቤታቸው የፈረሰባቸው ሌላ ምትክ ቦታ ይሰጣቸው!! ኪሳራውም ይከፈላቸው!! ለምን? እያንዳንዱ ርምጃ አፀፋ ይጋብዛል :: ሶስት መቶ ሰው ስታፈናቅል ሶስት መቶ ሽፍታ ታፈራለህ :: ለመናፈሻ ያሰብከው ሜዳ : ነገ መከሳከሻ ሆኖ ታገኘዋለህ:: አረንጉዋዴ ሳይሆን በደም የቀላ መስክ ይጠብቅሃል::
ባገራችን ” ስለፍቅር በስመ አብ ይቅር ” የምትል አሪፍ ተረት አለች:: የዚህን ተረት መነሻ እንዲህ ሊሆን ይችላል:: አንድ ክርስቲያን ሙስሊም ባለንጀራውን ቤቱ ይጋብዛል:: ራት ላይ ሁለቱ ወዳጆች ማእድ ለመቁረስ ተቀምጠዋል:: ጋባዡ ራቱን በክርስትያን ደንብ የመጀመር ግዴታ እንዳለበት ያውቃል:: ግን ይሄንን በማድረግ የወዳጁን ስሜት ማስቀየም አልፈለገም:: ምን ይሻላል?? ለጊዜው የማእዱን ስርአት ሊያልፈው ወሰነ:: ” ስለፍቅር በስመአብ ይቅር::” ብሎ ማእዱን በገለልተኛ መፈክር ጀመረው::
The terminal የሚለው የስፒል በርግ ፊልም ላይ ህግ የሚያመልክ ያውሮፕላን ጣቢያ ባለስልጣን አለ:: አለቃው ከለታት አንድ ቀን እንዲህ አለው:: ” አንዳንዴ ለፍቅር ስትል ህጉን ባላየ ማለፍ አለብህ :: የዚህ አገር መሰረት ፍቅር ነው::
እኔ የዚህ አገር መሰረት ፍቅር ነው አልልም:: የኢትዮጵያ መሰረት በዋናነት ጉልበት ግድያና ማፈናቀል ነው:: ግን ይሄ ትውፊት የሆነ ቦታ ላይ መገታት የለበትም?!