“የእኛ ኃላፊነት የክልላችን ህዝብ ከአገሩ ልማት እየተጠቀመ ሌሎች ህዝቦችም በሰላም አብረው እንዲኖሩ...

“የእኛ ኃላፊነት የክልላችን ህዝብ ከአገሩ ልማት እየተጠቀመ ሌሎች ህዝቦችም በሰላም አብረው እንዲኖሩ ማድረግ ነው”- አቶ ሙስጠፋ ሙሃመድ የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳን

የለውጥ አካል ሆኖ ለህዝብ መታገልና ለውጤት ማብቃት ብቻ ሳይሆን በኋላም የለውጡ መሪ ሆኖ መገኘት እንደ እድለኝነት የሚታይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይሄን እድል በሚገባ ተጠቅሞ ለውጡ የህዝብ እንዲሆን ማስቻልና በአግባቡ መምራት ሌላ አቅም ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ አመራሮች መካከል ደግሞ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ አንዱ ናቸው፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን በክልሉ ለውጡን ተከትሎ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎችንና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሚወዱት የታገሉለት ህዝብ መሪ ሆነው በመሾምዎት ምን ተሰማዎት?

ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ፡- በጣም ደስ የሚል ስሜት ነው ያለው፡፡ እኔም ለዚህ ህዝብ ስታገል እሾማለሁ፣ ባለስልጣንም እሆናለሁ ብዬ አይደለም፡፡ በወቅቱ የነበረው ጫናና በህዝቡ ላይ ይደረጉ የነበሩ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በምችለው አቅም (በትግልም ይባል ተቃውሞ) ለመናገር ያክል ነበር፡፡ በዚህም ለኢትዮጵያውያንና ለሌሎች የዓለምአቀፍ ማህበረሰብም ችግሮችን እንዲያውቅ በብዛት እንደ ጸሐፊ ሆኜ ነበር የምጽፈው፡፡

ስጀምር ይሄን ያህል ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አልጠበቅሁም፡፡ በኋላ በክልሉ የነበረው የፕሬስ ነጻነት ሲዘጋ፤ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች እንዳይገቡ ሲከለከል፤ ያለው የመረጃ ፍሰት ሲቀንስ እና በዚህ ምክንያትም እዚህ ያለው ህዝብ የእኛን ጽሑፎች መከታተል ሲጀምር ነው በአጭር የጽሑፍ መልዕክትም ሆነ በሌሎች መንገዶች መረጃዎች ሲደርሱን ብዙ ተጽዕኖ እንደነበረው የተረዳነው፡፡ አሁን ያ ሁሉ አልፎና ከዛ ሁሉ አልፈን፤ እንዲህ እየተደረገ ነው የምንልነትን ህዝብ ለመምራት እድል በማግኘቴ ደስ ብሎኛል፡፡

ይሁን እንጂ ደስታዬ የበለጠ ደስታ የሚሆነው፤ ህዝቡ ይፈልጋቸዋል ብዬ አምንባቸው የነበሩ ነገሮችን እንዲያገኝ ማድረግ ስችል እና የሰብዓዊ መብት እንዲከበር፤ የመናገር፣ የመስራትና የመንቀሳቀስ መብት እንዲኖረውና እንዳይገደልም ማድረግ ስችል ነው፡፡ እናም እንዲህ አይነት ነገሮች ሙሉ በሙሉ ተሟልተው፤ ህዝቡም አሁን ካለው ሽግግርም ሙሉ በሙሉ ወጥቶ ሲረጋጋና ወደልማት ሲዞር ደስታዬ የበለጠ ሙሉ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይሄን ኃላፊነት ወስደው ሲሰሩ እነዚህን ችግሮች ሊፈታ የሚችል አሰራርና መዋቅር ዘርግቻለሁ ብለው ያምናሉ? እንዴት እየሰሩ ነው?

ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ፡- ላለፉት 27 ዓመታት የሶማሌ ተወላጆች በተለያዩ ስሞች ሲጠሩ፤ አክራሪ፣ አሸባሪና ኦብነግ እየተባሉም ብዙ ህዝብ አልቋል፡፡ ይሄም አልበቃ ብሎ ደህና በነበረችው ጅግጅጋ ከተማ ላይ በደገኛው የህብረተሰብ ክፍል ላይ የጥላቻ ቅስቀሳ በማድረግ በሐምሌ 28 በርካታ ንጹሐን ዜጎች ምንም ሳያጠፉና መንግስት ሕግ ያስከብራል፤ ከለላም ይሰጠናል ብለው በሚያስቡበት ቦታ በክልሉ በነበሩ ባለስልጣናት አማካኝነት መንግስት ራሱ አጥቂ ሆኖ ሰፊ ጥፋት ሊደርስ ችሏል፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያኖች የተቃጠሉበት፤ ቀሳውስት የታረዱበት፤ ሴቶች የተደፈሩበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡

እነዚህን ችግሮች ከመፍታት አኳያ አሁን ያለው የስራ ሁኔታ ጅምር ነው፡፡ ሆኖም እንደ አጀማመራችን ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰሞኑን በተካሄደው የከተሞች ፎረም፤ በኤግዚብሽን ማዕከልም አካባቢ የነበረውን ድባብ እንዳየኸው ደማቅና ሰላማዊ ነበር፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ብሔር ብሔረሰቦች በህብረትና በአንድነት ደስ ብሏቸው፤ አንዱ የአንዱን ንብረት እያስተዋወቀ፤ አንዱ የአንዱን ሙዚቃ እያዳመጠ፤ እንዲህ ተቀላቅለው ከማየት በላይ ደስታ የለም፡፡ እናም የለውጥ ሂደቱ ጅምር ቢሆንም ብዙ ነገር ተሳክቶልናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ እንዲሆንም መዋቅር ዘርግተናል፤ ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስም የእኛን ራዕይና ዓላማ ሊያሳካ የሚችል አስተማማኝ መዋቅርም አለ ብዬ አምናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ የነበረው ችግር በህዝቦች መካከል መጠራጠርን ትቶ ማለፉ ይታወቃል እና ይሄን መጠራጠር ወደ መተማመን ለማምጣትስ ምን ሰርታችኋል?

ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ፡- በዚህ ላይ በደንብ ሰርተናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በሁለቱም በኩል የሃይማኖት አባቶች እንዲገናኙና እንዲወያዩ ተደርጎ፤ የተፈጠረው ችግር በክልሉ የተፈጸመ ቢሆንም የሶማሌ ህዝብ ግን እንደሌለበት ከማንም በላይ ራሳቸው መስክረዋል፡፡ በችግሩ ወቅትም የክርስትና እምነት ተከታይ ምዕመናንን ሲከልሉ፣ በሚለብሱት ልብስ እየሸፈኑ ሲደብቁና ቤታቸው እያስገቡ ሲያተርፏቸው የቆዩት የሶማሌ ሴቶች ናቸው፡፡

እናም በወቅቱ ቅሬታ ያላቸው፣ የተጎዱና የተገደሉ ሰዎች ያሉብንን ያክል፤ በወቅቱ እንዳይጎዱና እንዳይሞቱ የሶማሌ ህዝብ ከለላ ያደረገላቸው በርካታ ህዝቦች አሉ፡፡ ይህ ጠቅሞናል፡፡

እስካሁን ትልቁ ጋሬጣ የነበረውም የህዝቦችን አብሮ መሆን የማይፈልጉና ጥቅማቸው የተነካባቸው ሃይሎች አሁንም ያሉትን ስሜቶች በመቆስቆስ ነገሩ እንዳይበርድ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ተግባራቸው መሳካትም በሶማሌው በኩል ከፍተኛ የማነሳሳት፤ ሶማሌኛ ተናጋሪ ባልሆኑት በኩልም ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

መቃቃር እንዲሰፋና ቁስሉ እንዲያገረሽ ለማድረግ የሚሰሩ ሃይሎች ሙሉ በሙሉ ያለመሸነፍ ደግሞ ህዝቡን የማቀራረብና ወደድሮው የማምጣት ስራው በፈለግነው ደረጃ ሄዶ ሊጠናቀቅ አልቻለም፡፡ ሆኖም እነዚያ ኃይሎች እየደከሙ ስለሆነ ከአሁን በኋላ ህዝቡ ሙሉ ለሙሉ ወደዚህ እንዲመለስ እናደርጋለን የሚል እምነት አለን፡፡ አሁን ያለው ሁኔታም በጣም ጥሩ ነው፡፡ አጥፊ ኃይሎችን ከውስጣችን ካጸዳን ደግሞ የበለጠ አስተማማኝ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አጥፊ ኃይሎችን እየተከታተሉ ፖለቲካዊም ሆነ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከማድረግ አኳያ ምን እየተሰራ ነው?

ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ፡- እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በክልሉ ዙሪያ በተለይም በአዲሱ አመራር ላይ ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳዎች ይነዙ ነበር፡፡ በዚህም የሕግ የበላይነትን እንዳይከበርና የህዝብ አንድነት ተጠብቆ ሁሉም በኢትዮጵያዊነቱ አብሮ መኖሩን የማይደግፉ ከፋፋይ ሃይሎችን ለመታገል ትንሽ ችግር ፈጥሮብን ነበር፡፡ ከእነዚህ ፕሮፖጋንዳዎች አንዱ፣ አዲሱ አመራር የሚወስደው እርምጃ የበቀል እርምጃ የማስመሰል ሁኔታ ነው፡፡ ክልሉ ሰው እየተበቀለ ነው፤ በጅምላም ሰው እየታፈሰና እየታሰረ ነው፤ ወዘተ. እያሉም ተደራጅተው እዚህም፣ አዲስ አበባም፣ ሌላም ቦታ ከፍተኛ የሃሰት ፕሮፖጋንዳዎችን ይነዙ ነበር፡፡ ይሄ በራሱ በሰዎች መካከል መቃቃር እንዲፈጠርና እዚህም እዚያም ግጭቶች እንዲፈጠሩ እያደረገ ስለነበር በስራችን ላይ የተወሰነ መጓተትና በተወሰኑ ኃይሎች ላይም እርምጃ ሳይወሰድ እንድንቆይ ጫና ፈጥሮብን ቆይቷል፡፡

ሁለተኛው፣ የእኛ የጸጥታ ሃይልም በወቅቱ ጊዜ ይፈልግ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው በተለይ በልዩ ፖሊስ አካባቢ የነበረው የቀድሞው አመራር ከፍተኛ ጥፋት ነው የፈጸመው፡፡ ስለዚህ ይሄንን ልዩ ፖሊስ ሪፎርም በማድረግ ከመከላከያም ጭምር የመጡ ልጆችን በማካተት ተደራጅቶ የህዝብ እምነት እስኪያገኝ ጊዜ መውሰዱ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮችና ሌሎች ነገሮች ምክንያት ስራው የተፈለገውን ያክል አልተሄደበትም፡፡

ካለፉት 20 ቀናት ወዲህ ግን በሕግ የበላይነት ዙሪያ እርምጃ መውሰድ ጀምረናል፡፡ በዚህም ህዝቡን የሚያቃቅሩ፣ ቀድሞ በክልሉ ይሄ ሁሉ ችግር ሲፈጠር ሲመሩ ከነበሩ ሶማሌም ሶማሌ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ትስስር ፈጥረው ለውጡን ለመቀልበስ ከሚያስቡ ኃይሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመራችንን ተከትሎ ነገሮች እየተረጋጉ መጥተዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ከአጎራባቾቹ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረው ምን እየተሰራ ነው? የፌዴራል መንግስቱስ ድጋፍ?

ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ፡- እዚህ ላይ የፌዴራል መንግስት እገዛ በጣም ወሳኝ እንደመሆኑ፤ እያገዙን ነው፡፡ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከዛሬዋ ቀን ድረስም ከመከላከያ ጀምሮ፣ የፌዴራል ፖሊስና የደኅንነት አካላት ክልሉ በእግሩ እንዲቆምና ጸጥታው እንዲከበር፤ እንዲሁም አሸባሪዎችም ሶማሊያ እንዳይገቡ በመከላከል ያላሰለሰ ጥረት ነው ያደረጉት፡፡

አሸባሪ ከውጭ እንዳይገባ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ረብሻ የሚፈልጉ ኃይሎች ህዝቡን እንዳያጋጩ መረጃ በመሰብሰብና ቀድሞ የመከላከል ስራ በመስራት፤ ወንጀለኞችንም አድኖ በመያዝ፤ ግጭቶች ሲፈጠሩም በቦታው ተገኝቶ ግጭቱ እንዲቆም በማድረግ ረገድ ከፍተኛ እገዛ ነው ያደረጉልን፡፡ በተለይ የእኛ መዋቅሮች ባልጸዱበት ጊዜ ላደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የእኛ የጸጥታ መዋቅሮች ሪፎርም እያደረጉና እየተጠናከሩ እየሄዱ ነው፤ በአሁኑ ሰዓትም የፌዴራል የጸጥታ አካላትና ክልሉ በሁሉም ጉዳይ ላይ መጠራጠር ሳይኖራቸው በቅንጅት እየሰሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መጀመሪያ አካባቢ በሞያሌና ሌሎችም አካባቢዎች ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ሲፈጠሩ የነበሩ የጸረ ለውጥ ኃይሎች የሚመሯቸው ግጭቶችን ለማስቆም አስችሏል፡፡ ከአሁን በኋላም ይነሳሉ ብለን አናስብም፡፡ የፌዴራል እገዛም ከመቼውም በላይ በአሁን ሰዓት ጥሩ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሰላም ሁሉ የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ፤ ክልሉም ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲሸጋገር ለማስቻል እንዴት እየሰራችሁ ነው?

ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ፡- በልማት ዙሪያ መጀመሪያ ያሰብነው ሙስናንና ሌብነትን መዋጋት ነው፡፡ መንግስት ለክልሉ ከፍተኛ በጀት ነው የሚመድበው፡፡ እናም የመጀመሪያው ልማት ክልሉ በራሱ የሚሰበስበውንም ሆነ የሚያገኘውን በጀት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ ማዋል ነው፡፡ ለዚህም ንጹህ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓትን ማስፈን የመጀመሪያው ስራ ነው፡፡

ይህ ደግሞ በየስብሰባው ላይ ሲደመጥ እንደነበረው እንዲህ ብያለው ከሚልና ለሚዲያ ፍጆታ ከሚውል የ27 ዓመት ጉዞ በተለየ መልኩ ሙስናን ለመዋጋት በቁርጠኝነት መነሳትና ሙስናን የሚጸየፍ ህብረተሰብ በመፍጠር ከራስ ጀምሮ ምሳሌ በመሆን መስራትን ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ሰዎች የሚያደርጉትም ሆነ የበታች አመራሮች የሚሰሩት መሪዎቻቸው ላይ የሚያዩትን ነው፡፡ አንተ እየዘረፍክ የቅርብ የሆኑ ሰዎችና ጎሳህ እንዲዘርፍ እያደረግህ በሚዲያ የምታወራው ነገር ትርጉም አይኖረውም፡፡

በዚህ ዙሪያ ያለው ስራ ፈታኝ እንደሚሆን አውቃለሁ፡፡ ግን በከፍተኛ አመራሩ ቁርጠኝነቱ አለ፡፡ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱም በአብዛኞቻችን አለ፡፡ ምክንያቱም የሶማሌ ክልል ህዝብን በዚህ ደረጃ ያስቀረውና ትምህርት ስርዓታችን እንዲወድቅ፣ ጤናውም በዚህ ደረጃ እንዲሆን፣ ከሦስት ሚሊዬን በላይ ህዝባችን የምግብ የእርዳታ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደረገው እኛ ሀብት ስለሌለን ሳይሆን የአመራር ብልሹነት ስለነበረ፤ ሌብነቱም ወደ ባህል የተለወጠበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ነበር፡፡ ስለዚህ ይሄንን መቀየር አለብን፡፡ ይሄን ከቀየርንም ልማት ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሌላው ስራ ከህብረተሰቡ ጋር ተመካክሮ ከመንግስት ባለፈ ህዝቡ ያለውን አቅም አጠናክሮ በራሱ ኢንቨስትመንት እንዲሰራ ማበረታታት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተገኘውን ሰላም በመጠቀም በአገልግሎት፣ መንገድ፣ በትምህርትም ሆነ ሌሎች ዘርፎች መንግስትን ለሚያግዙ ህብረተሰቡ በራሱ የሚሰራቸው በርካታ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሰማራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ኬንያና ሌላም ቦታ ኢንቨስት እያደረገ ያለው የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራ አሁን ያለውን ሰላም ተጠቅሞ እንዲገባ ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህ ባለፈም በሰላሙ ምክንያት ከክልሉ ርቀው የነበሩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች የመንግስት አቅም በደከመበት የልማቱ አጋር እንዲሆኑ ለማድረግ፤ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡

በእነዚህ ሦስት ጉዳዮች ላይ አተኩረን ብቃት ያለው አመራር እስከ ወረዳ አድርሰናል፡፡ በዚህ ዙሪያም ልማትን ማካሄድ የሚቻለው በሙከራ (በትራይ ኤንድ ኢረር) ስላልሆነ፤ በአሁኑ ሰዓት በየወረዳው የተቀመጡት ልማት ምን እንደሆነ የሚገባቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ በየደረጃው ከተቀመጡ አመራሮችም 80 በመቶ ያህሉ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ በራሱ የልማቱን ፍጥነት ይጨምረዋል፡፡ ለዚህ አጋዥ እንዲሆንም ህዝቡ ከመንግስት ጠባቂ ብቻ እንዳይሆን ተነሳሽነቱን ከፍ የማድረግ ስራ ይከናወናል፡፡ በዚህም በመንግስት እየታገዘና እርስ በእርሱ እየተደጋገፈ በራሱ መስራት እንዲችልና ከሱሶች ነጻ ሆኖም ወደስራ እንዲገባ ማስቻል ያስፈልጋል፡፡

አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት ከማሸጋገር አኳያ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ራሱ እየመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የእንስሳቱ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣትና የግጦሽ መሬትም ወደመኖሪያነት እየተለወጠ መምጣት፣ ከዓየር ሁኔታ መለዋወጥና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አሁንም በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 በመቶ ሰው አርብቶ አደርነቱን እየተወ በትናንሽ ቦታዎች ላይ ቤት እያቆመ ወደ ሻይ መሸጥና ወደሌሎች ስራዎች ለመሰማራት እየተገደደ ነው፡፡ ይህ አንድ ሂደት ነው፡፡

ሌላው ሂደት ደግሞ፣ በአርብቶ አደር አካባቢዎች በአንድ ቦታ እየተሰባሰቡ የመንግስት አገልግሎት የሚያገኙበትን እድል የመፍጠር ስራ ሲሆን፤ እኔም በግሌ የሶማሌ ህዝብ እድሜ ልኩን አርብቶ አደር ይሁን ብዬ ስለማላምን ለዚህ ስራ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ እናም ህዝቡ ትምህርት፣ ጤና፣ ውሃና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን በአንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ ማግኘት ስላለበትም ወደዛው መሄድ አለበት፡፡ በዚህ መልኩ የአርብቶ አደሩን ህይወት ማሻሻል፤ አስፈላጊው የሆኑትን እንስሳትም በተሻለ መልኩ የሚያረባበትንና ዘርፉን አብዝቶ ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ የሚሄድበትን እድል መፍጠርና በወቅት ያልታጠረ ስራ እንዲያከናወኑ ማገዝ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በፌዴራል የወጡ ዝርዝር የፖሊሲ አቅጣጫዎች ስላሉ እነርሱን ለክልሉ በሚሆን አግባብ የማስፈጸም ተግባር ይከናወናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ሰላምና ልማት ውስጥ የክልሉን ምሑራን ከማሳተፍና የተፈጠረውን ሰላም ተጠቅመው ከገቡ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ከመስራት አኳያ ምን አስባችኋል? በቅርቡ የተረከባችኋቸው የኦብነግ ታጣቂዎች ጉዳይስ?

ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ፡- የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከዳያስፖራውም ሆነ ከሌላ ቦታ ወደ ክልሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ተወላጆች እየመጡ ነው፡፡ ይሄን ሃይል ለመጠቀም ደግሞ ከዜግነትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ያሉ ጉዳዮችን እያየን ህጉ በሚፈቅደው መጠን በማሳተፍ አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረግን እንገኛለን፡፡

የኦብነግና ሌሎችም የፖለቲካ ሃይሎችን በተመለከተም፤ እኛ ክልል ላይ ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲያንሸራሽሩ እየተደረገ ነው፤ ህጉም ይፈቅድላቸዋል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያዊነታቸው ዙሪያ ብዥታ ካላቸው ሃይሎች ጋር አብሮ ለመስራት ይከብደናል፡፡ ምክንያቱም የእኛ ሀሳብ ኢትዮጵያን ብቻ ለመጥቀም ሳይሆን ለህዝባችን ጥቅምና ፍላጎት ስንል በኢትዮጵያዊነታችን እንጠቀማለን የሚል ነው፡፡ የእኛ ህዝብ የሚጠቀመውም አሳታፊ የሆነች ኢትዮጵያ ስትኖር ነው የሚልም ጽኑ እምነት አለን፡፡

ለምሳሌ፣ የሶማሌ ህዝብ የጎሳ አወቃቀር ከሶማሊያ ህዝብ የተለየ አይደለም፡፡ እናም እዛ የተፈጠረው ሁኔታ እኛጋ የማይፈጠርበት ምክንያት የለም፡፡ አያምጣውና የሆነ ነገር አገራችን ላይ ቢፈጠር ደግሞ ትልቅ መራበሽና መተላለቅ የሚኖረው የእኛ ክልል ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሰፋ አድርጎ በማሰብና በመተባበር አንድ አገር መፍጠር የህልውና ብቻ ሳይሆን፤ በሁሉም መስክ የሶማሌ ህዝብ ህልውናም በኢትዮጵያ ቀጣይነት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ሁኔታዎችን እያየ በሚለዋወጥ አካሄድ (ታክቲካል አፕሮች) እና ፈራ ተባ አያስፈልግም፡፡ በስትራቴጂ ወስኖና ይሄ ነው የሚጠቅመን ብሎ ወደዛ መግባት ነው፡፡

እናም ነገሮች ሳይመቹ ሲቀሩ ሰላምን መቀበል፤ ነገሮች ሲመቻቹ ደግሞ ጠመንጃ አንስቶ ሌላ ዓላማ ማንገብ አያስፈልግም፤ እኛም አንፈልግም፡፡ ሰው ደግሞ አንድ ቦታ ቆሞ ስለማይቀር፤ በተለያየ ምክንያትን ብሶት የተፈጠረን ስሜት ቀይሮ በዚህ ዙሪያ ለመስራት የሃሳብ ለውጥ ከመጣ ደግሞ የማንተባበርበት ምክንያት የለም፡፡

የእኛ ኃላፊነት የክልላችን ህዝብ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከአገሩ ልማት እየተጠቀመ ሌሎች ህዝቦችም በሰላም አብረው እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ለዛ ደግሞ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንከፍላለን፡፡ የኦብነግ ታጣቂዎችን በተመለከተም ከነገርኩህ ውጪ አይሆንም፡፡ ቀጣይነታቸውን የሚወስነው በዚህ ዙሪያ ያላቸው አመለካከት ነው፡፡ ምክንያቱም እዚህ ያለው የጸጥታ ሃይል ለአገሪቷ አስጊ መሆን ስለሌለበት፣ አስጊ ይሆናል የምንለውን ሃይል አናካትትም፡፡ አስጊ አይደሉም የምንላቸውን ሃይሎች ደግሞ በተለያየ መልኩ እያሳተፍን ነገሮች እንዲረጋጉ ለማድረግ ነው ዓላማችን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ለሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ በስኬት መጠናቀቅ እንደ ክልል ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለይቶ ከመስራት አኳያ ምን ዝግጅት አድርጋችኋል?

ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ፡- ለዚህ ቆጠራ መሳካት እንደ ክልል ከፌዴራል መንግስት ጋር በደንብ እየሰራን ነው፡፡ ከአመራሮችም ጋር በደንብ እያጠናንና እያየንም ነው፡፡ በዛ ላይ ያሉንን አስተያየቶችም ለመንግስት እያቀረብን፤ ጉድለቶች ካሉም እንዲታረሙ እያደረግን ነው፡፡ ዋናው ነገር እዚህ ያለው ህዝብ እንዲቆጠር ማድረግ ነው፡፡

ሆኖም አንዳንድ ጫናዎች እንደሚኖሩ እናስባለን፡፡ ለምሳሌ፣ ድንበር አካባቢ በጎሳዎች መፎካከር ምክንያት ቁጥር ለመጨመር ሰዎችን የማጓጓዝና የማስገባት ነገር ሊኖር ስለሚችል በዚህ ላይ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተነጋግረን አካባቢውን በጊዜ የምንዘጋበት መንገድ ተፈጥሮ፣ ውስጥ ያለው ብቻ እንዲቆጠር የምናደርግበት መንገድ መፈለግ አለበት፡፡ ውስጥ ያለውም በአግባቡና በተቀመጠው አቅጣጫ እንዲሰራ ማድረግ ነው፡፡ ጉዳዩ ብዙ የፖለቲካ ስራ ስለሚፈልግም የአገር ሽማግሌዎችን እያነጋገርን ነው፡፡

የህዝብ ቆጠራውን አጀንዳ ማድረግ የሚፈልጉ፤ ገና ምንም ሳይቆጠር ቁጥራችን ሊቀነስ ነው፤ እንዴት ታስቧል፤ እንዲህ ተደርጓል፤ እያሉ ውጤቱን ከአሁኑ ለመወሰንና የክልሉን አስተዳደር አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የሚሞክሩ ሃይሎች አሉ፡፡ እኛ ግን ይሄንን ከማራገብ ተቆጥበን ከፌዴራል መንግስቱ ጋር እየተነጋገርን በቆጣሪዎች ሁኔታና ለቆጠራ በሚያስፈልጉ ነገሮች ዙሪያ እየሰራን ነው፡፡ ምክንያቱም የፌዴራል መንግስቱም ህዝቡ እንዲቆጠር እንጂ ሌላ አላማ የለውም፡፡ ይሁን እንጂ ያለ ምንም ግድፈት 100 በመቶ የሚደረግ የህዝብና ቤት ቆጠራ እንኳን የመሰረተ ልማት ባልተሟላባት ኢትዮጵያ ቀርቶ አደጉ በሚባሉት አገራት ጭምር የትም ዓለም የለም፡፡ ዋናው ነገር አስተማማኝና ሊታመንበት ሂደትን መከተል፤ ምክንያታዊ የሆነ ውጤትም እንዲመጣ ለማስቻል ነው እየሰራን ያለነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሶማሌ ህዝብ ቀጣይ ሁለንተናዊ ለውጥ የእርሶና አመራርዎ ራዕይ ምንድን ነው? የህዝቡና ሌሎች ባለድርሻዎች ሚናስ ምን ሊሆን ይገባል?

ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ፡- ያለን ራዕይ ክልላችን የተረጋጋ እንዲሆን፤ በክልላችን ውስጥ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉም እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው በሰላም እየተንቀሳቀሱ በሰላም እንዲኖሩ፤ በህዝቦች መካከል ያለው ክፍፍልና ለ27 ዓመታት የተሰበከው ጥላቻም እንዲጠፋ፤ በተለይ በቅርበት የማውቀው በምስራቅ በኩል የነበረው አንድነትና ፍቅር ዳግም እንዲመለስ ማስቻል ነው፡፡ ሆኖም አሁን ያለው ችግር እንዲቀረፍ ጊዜ ያስፈልጋልና ጊዜ ተሰጥቶ መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ፡፡

ሆኖም እንደ ፖለቲካ አመራር እኛ ያለብን ኃላፊነት ሁሉንም እኩል የማስተናገድ፤ ሁሉንም እኩል የማየትና በፍትሃዊነት የማገልገል ነው፡፡ ፍትህና እኩልነት ከመጣ ደግሞ ሌላው ይመጣል፡፡ ህዝቦች በዘር፤ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ. ልዩነት ሳይደረግባቸው በእኩልነት እንዲኖሩም ነው የእኔ ራዕይ፡፡

ለዚህ ወሳኝ ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ ነው፤ ይሄ ደግሞ አለን፡፡ የፌዴራል መንግስት እገዛ ግን ወሳኝ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያንና የሶማሌ ክልል ምሑራንም እገዛ ወሳኝ ነው፡፡ አሁንም ብዙ እየሰራን ሲሆን፤ በዚህ ዙሪያ ህዝቦችን ለማቀራረብ የሚያስችሉ ተከታታይ የሆኑ አውደ ጥናቶች እንዲካሄዱም እቅድ አስቀምጠናል፡፡ ፍትህ፣ ከምንም በላይ ሰብዓዊነትና ሰላም ለክልሉ ህዝብ እንዲሰፍን ነው የምንሰራው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራትም በከፍተኛ ደረጃ ሰርተናል ብለን እናምናለን፡፡

በዚህ ረገድ መጥፎ አስተሳሰቦች እንዲወገዱ እየሰራን ቢሆንም፤ መጥፎ ሃይሎች ግን ሁል ጊዜ አይጠፉም፡፡ በተለይ በእኛ ክልል ይሄንን መጥፎ ተግባር ስራቸው ያደረጉ ሃይሎች አሉ፡፡ የዚህን ክልል ህዝብ ሲገድሉና ሲጨፈጭፉ፤ የክልሉን በጀት ከክልሉ አመራር ጋር ሲመዘብሩ የነበሩ ጥቂት ጄኔራሎች እና የእነርሱ የፖለቲካ ነፍስ አባቶች ከፍተኛ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት አሁንም ድረስ ይሄንን ክልል ወጥረው ነው የያዙት፡፡ እዚህ ያለው ህዝብ እንዳይረጋጋ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት፡፡

በእኔ እምነት ይሄ ተግባር የመገንጠል ዓላማቸው ምዕራፍ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ሶማሌ ክልል ተባልቶ ረብሻ ፈጥሮ፤ ይሄ ክልል ሲረበሽ ‹ኢትዮጵያ ስለፈረሰች እኛም እንሂድ› የሚል አመለካከት ያላቸው ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡

እኛ ደግሞ የሶማሌ ህዝብ ከጎረቤት ህዝቦች ጋር አብሮ ለመኖር ያለውን ፍላጎት እናውቃለን፤ የበለጠ ተቀራርቦ ለመስራትም ከሽማግሎዎች ጋር እየመከርን ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነቱ የመጠቀም ያለውን ፍላጎት ለማሳካትና ያሰብነው ራዕይ ከዳር እንዲደርስ ዋናው ስራ ቀድሞ የጠፋውን አመራርነት መስጠት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከሰራንና ያለውን የህዝቡን ድጋፍ ከተጠቀምን በእርግጠኝነት ማሳካት ይቻላል፡፡ ህዝቡም ይሄንኑ አውቆ ድጋፉን ሊያጠናክር ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልስሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፡፡

ም/ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፋ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011

ወንድወሰን ሽመልስ

Ethiopian Press Agency /የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/

/ ከመስከረም አበራ ገጽ የተወሰደ /

LEAVE A REPLY