– የዓድዋ ድል ታሪክ በፈታኝ ጦርነት መምጣቱን በሚያስታውስ ተጋድሎ ለፍፃሜ የደረሰው ጉዞ መሰናክሎቹን በሙሉ አልፎ ለድል ተቃርቧል።
– አዲስ አበባ የዓድዋ ድልን ለማግዘፍ እየደገሰች ነው። እውቁ ድምጻዊ ማህሙድ አህመድን ጨምሮ ታዋቂ ድምጻውያን ኮንሰርታቸውን በመስቀል አደባባይ ያቀርባሉ።
– ጉዞው ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት አቅጣጫ ተደርጓል።
– ከወር በላይ በእግራቸው ከተጓዙት ዘማቾች መሐል አስሩ የጦማር ዘብ አስታዋሾችን ተቀላቅለው በአብርሐ ወአጽብሐ መንገድ በጋራ ሮጠዋል።
– ስንቃጣ – ፍረወይኒ ላይ በልመና ውለው ያደሩ ተጓዦች አስገራሚ መስተንግዶ ገጥሟቸዋል።
– አቧራ በሚዘንብበት መንገድ ያቋረጡት ተጓዦች በሰላም ነበለት ከተማ ገብተዋል።
በአራት ተጓዦች ከሐረር የተጀመረው ጉዞ ዓድዋ 6 አዲስ አበባ ላይ 48 በመድረስ ፤ መቐለ ከተማ ላይ 52 በመሆን ፤ ውቅሮ ከተማ ላይ ደግሞ የዘማቾች ቁጥር ወደ 54 አድጓል። ከዓድዋ ድል የዘመቻ ታሪክ ጋር ቅርርቦሽ ያለው የመጨመር ታሪክ በዘንድሮው ጉዞ እውን ሆኗል።
*ለቀናት በውቅሮ ከተማ ላይ የእግር ጉዞውን በማቆም በንባብ የዓድዋ ድል ዘመን ላይ ለመድረስ ሲተጉ የቆዩት ተጓዦች በነበረው የእውቀት ልውውጥ መርሐ ግብር ስለ ድል ታሪኩ መጠየቅ የሚችሉ ብቁ ተጓዦችን ማፍራት ተችሏል።
*በንባብ ዝግጅቱ መሐል ከዛሬ 82 አመታት በፊት በወራሪው የጣሊያን ኃይል በግፍ የተገደሉ ከ 30 ሺህ በላይ ንፁኃን ኢትዮጵያዊያንን ለመዘከር የጧፍ ማብራት ስነሥርዓት ተካሂዷል።
*ከንባብ ቆይታው ፍፃሜ በኋላ ታሪካዊውን የአል ነጃሽ መስጊድ ለመጎብኘት በቦታው የተገኙ ተጓዦች ስለ ታሪኩ ሰፊ ማብራሪያ ከታሪክ ባለሙያ እና ከመስጊዱ ሊቃውንት አግኝተዋል።
*የአል ነጃሽ መስጊድን ለመጎብኘት ከተገኙ ተጓዦች መሐል አስር የሚሆኑ ብርቱ ተጓዦች በመምረጥ ወደ ውቅሮ ከተማ በሩጫ እንዲመለሱ ሆኗል። በዚህም ከአዲስ አበባ በ15 ቀናት ሩጫ ውቅሮ ከተማ የደረሱትን ሁለቱን የጦማር ዘብ ዘካሪ ሯጮችን ተቀላቅለዋል።
*በማግስቱ በነበረው 47 ኪ.ሜትሮችን የሚሸፍን ሩጫ ለ12 በመሆን የመጀመሪያውን የሐገራችንን ታሪካዊ ከፊል ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን አብርሐ ወአጽብሐን ጎብኝተው ሐውዜን ከተማ ላይ መዳረሻቸው አድርገዋል።
*በእግር ጉዞ ወደ ስንቃጣ ያመሩት ቀሪ 41 ተጓዦች ከዛሬ 123 አመታት በፊት ከመቐለ እንዳየሱስ ምሽግ እጅ ሰጥተው የወጡትን የማጆር ጋሊያኖን ጦር አጅበው ወደ እዳጋ ሐሙስ ያመሩትን የፊታውራሪ ደሳለኝ ጦር የገጠማቸውን የስንቅ ማጠር ለማሰብ ጾማቸውን በመዋል ከማህበረሰቡ በልመና ስንቅ ሲሰበስቡ ውለው በማምሸታቸው የስንቃጣ ፍረወይኒ ነዋሪ የሚበላውን የሚጠጣውን አቅርቦ ማደሪያ ጭምር ሰጥቶ አስተናግዷቸዋል።
*በመለመን ሂደት ውስጥ ፈጽሞ የማይረሱት ርህራሔ ከማህበረሰቡ የገጠማቸው ተጓዦች ከእለቱ ስንቃቸው አልፈው ለማግስቱ የሚሆን እርዳታ ከህዝቡ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
*በስንቃጣ ስንቅ አጥተው ከነዋሪዎቹ ከፍተኛ እርዳታ ያገኙትን የዚያን ጊዜ ጀግኖች በመዘከር ለአካባቢው ማህበረሰብ ስለ ጉዞው ፋይዳ እና ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ህብረትና አንድነት በየቤቱ በመዞር የፍቅር ጥሪያቸውን እያቀረቡ ተልእኳቸውን በተገቢው መንገድ ፈጽመዋል።
*”ህዝቡ አስገራሚ ነው። በእጅጉ ፍቅር አዋቂ ነው። ገና ሳንጠይቃቸው ነበር በየቤታቸው እየወሰዱ ሲመግቡን የነበረው። እኛም አላማችንን እያስረዳን ስለ ዓድዋ ድል ታሪክ እውቀታችንን አካፍለናል። መቼም የማልረሳው አጋጣሚ ደግሞ አንዲት ሰላማዊት የተባለች ወጣት ለመሸጥ ያዘጋጀችውን አንባሻ ከሙሉ ፔርሙዝ ሻይ ጋር ገበያዋን ትታ ለእኛ መስጠቷ ነው” በማለት የሚገልፀው የቡድኑ ተጓዥ ብርሀኑ ይህንን የመሰለ ፍቅር ባለው ማህበረሰብ መሐል ማለፍ የሚሰጠው ደስታ የተለየ መሆኑን ይመሰክራል።
*የፊታውራሪ ደሳለኝ ጦር እና የንጉሰ ነገስቱ የአፄ ምኒልክ ጦር መልሰው ከተገናኙበት ታሪካዊው የሐውዜን ከተማ በሁለት ተከፍለው ጉዞ ያደረጉት ተጓዦች አመሻሹ ላይ አንድ ቦታ ላይ ተገናኝተዋል።
*ከሐውዜን መነሻቸውን በማድረግ ወደ ነበለት ከተማ ያመሩት ተጓዦች አቧራ የሚዘንብበትን መንገድ እያቆራረጡ እጅግ ፈታኝ በሆነው በረሀማ ጎዳና አልፈው ማራኪ የሆነው የእንባ ነበለት ተራራ ግርጌ የተቆረቆረችው ነበለት ከተማ ሲደርሱ የአካባቢው ማህበረሰብ ከነ አቧራቸው ተቀብሎ በክብር አስተናግዷቸዋል።
*በዘንድሮው ጉዞ ዓድዋ 6 እጅግ ፈታኝ የሆኑ አካላዊና ስነልቦናዊ ጫናዎችን በመቋቋም ከ1540 ኪ.ሜትሮች በላይ ያቆራረጡት ዘማቾች ፍቅርና ህብረትን ለመዘከር ወጥተው በፍቅር ተፈትነው በህብረት ነጥረው ጉዞውን ለፍፃሜ አድርሰውታል። ዓድዋ ድል ከመሆኑ በፊት ጦርነት መሆኑን በውል የተገነዘቡት ተጓዦች ከአካላዊ ትግል ባሻገር በስነልቦና ጦርነት መሐል መሆናቸውን በመረዳት በተቃራኒው ለተሰለፈው ኃይል ትልቅ መልዕክት አስተላልፈዋል። “ዓድዋ የኢትዮጵያዊያን ውድ ልጆች የደም ርስት፣ የህብረት ምልክት፣ የአንድነት ውጤት። በመሆኑ ከመቀነስ የላቀው መጨመር ልኩ ራሱ ድሉ ነው” ሲሉ መስክረዋል።
*የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የካቲት 23 ቀን ከማለዳው ጀምሮ በታላቁ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ነቅሎ በመውጣት የዓድዋን ድል ለመዘከር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ከማለዳው የሚጀምረው ልዩ መሰናድዖ ማጠናቀቂያውን የሚያደርገው በመስቀል አደባባይ በሚደረግ ግዙፍ የሙዚቃ ኮንሰርት ይሆናል። የጉዞ ዓድዋ 6 ጀግኖችን በእለቱ ጉዟቸውን ፈጽመው አመሻሹ 11:00 ሰዓት ላይ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመድረስ በመስቀል አደባባይ ተሰብስቦ ከሚጠብቃቸው በሙዚቃ ኮንሰርቱ ላይ ከሚታደመው ህዝብ ደማቅ አቀባበል እንደሚጠብቃቸው አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።
*አንጋፋና ታዋቂ ድምጻዊያን ማህሙድ አህመድ ጌታቸው ካሳ ብርሃኑ ተዘራ ታደለ ሮባ መስፍን በቀለ ቤቴ ጂ አስጌ (ዲንዳሾ) እሱባለው ይታየው እና ሌሎችም እውቅ ድምጻዊያን ከመሀሪ ብራዘርስ ባንድ እና ቶራ ባንድ ጋር በጥምረት የዓድዋን ድል በዓል ለማግዘፍ በመስቀል አደባባይ ለአዲስ አበባና አካባቢው ነዋሪዎች የሙዚቃ ኮንሰርታቸውን በነፃ ያቀርባሉ። ሁሉም ሀገር ወዳድ እንዲገኝም አዘጋጆቹ ጋብዘዋል።
*ባለፉት ጥቂት ቀናት ለጉዞው መሳካት የስንቅ ድጋፍ ያደረጉትን የሸገር ራዲዮ ከቤት እስከ ከተማ አዘጋጁን ማህደር ገብረ መድህን፤ ኑሮዋቸውን በአውስትራሊያ ያደርጉ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ለእህት ዛቲ ሜቴ ፤ ለኮረማሽ ቡድን አባላት ፤ ለካሳዬ አዲስ፤ ለናኦሚ እና በየመንገዱ ትብብር ላደረጉ ውድ ኢትዮጵያዊያን ከፍ ያለ ምስጋና የጉዞ ዓድዋ አዘጋጆች ያቀርባሉ።
*የካቲት 23 ቀን ዓድዋ እና አዲስ አበባ ላይ በድል መንፈስ ደምቀን ስለኢትዮጵያችን ፍቅር በጋራ እንገናኝ በማለት አዘጋጆቹ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ።
#ፍቅር_ለኢትዮጵያ!!
#ኢትዮጵያዊነት_ይለምልም!!