ጨፌ ኦሮሚያ 9ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የካቲት 19፣ 2011 | ኤፍ.ቢ.ሲ |
አዲስ አበባ | ጨፌው ለሁለት ቀናት በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባው የክልሉን መንግስት የ6 ወራት የስራ አፈፃፀም በመገምገም ላይ ይግኛል።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በመደበኛው ስብሰባ ላይ በመገኘትም የክልሉን መንግስት የ6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ለጨፌው አቅርበዋል።
አቶ ለማ በሪፖርታቸው፥ የክልሉ መንግስት ባለፉት 6 ወራት ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን እንዲሁም እንደ ሀገር የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰላም እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ህዝቡ በፖለቲካው ያገኘውን ድል እና መስመር እየያዘ የመጣውን የኦሮሞ ህዝብ ትግል በትእግስትና በብስለት በመምራት ኪራይ ሰብሳቢዎች እና ፀረ ዴሞክራሲ ሀይሎች በሚሸርቡት ሴራ ወደ ኋላ መመለስ በማይችሉበት መልኩ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሸጋገር መቻሉን ጠቅሰዋል።
አቶ ለማ መገርሳ፥ ጠላቶች የጥፋት አላማቸውን ከግብ ለማድረስ በአንድ በኩል የኦሮሞን እና የኦሮሚያን ጠላት በማብዛት በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሞን እርስ በእርስ ለማጋጨት ከፍተኛ ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድረስ በማቅረብ ሲሰሩ ነበር ብለዋል።
እነዚህ የጥፋት ሀይሎች ሲሸርቡት የነበረውን ሴራ ህዝቡ እና መንግስት ፊታቸውን ወደ ልማት እንዳያዞሩ ለማድረግ ሲከናወን በነበረው ስራ ውስጥ ጠላት ከሚሰራው ውጪ እርስ በእርስ የነበረው መከፋፈል ፈተና ሆኖ ቆይቷ ብለዋል።
በተለይም በአራቱ የምእራብ ኦሮሚያ ዞኖች እና በጉጂ ዞን የነበረው ግጭት ምክንያት ያልነበረው እና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተደረሰውን ስምምነት የተቃረነ ቢሆንም መንግስት ራሱን መስዋእት በማድረግ ህዝቡን ከጎኑ በማድረግ በትእግስትና በብስለት ወደ ሰላማዊ ትግል ለማምጣት ከፍተኛ ስራ መስራቱን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ ግጭቶችን ለመግታት ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመሆን ህብረተሰቡ ችግሮቹን በራሱ መንገድ እንዲፈታ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ በክልሉች መካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስቀረት በሚሰራበት ወቅትም የተለያዩ ግጭቶች ተፈጥረው እንደነበረም አቶ ለማ በሪፖርታቸው አቅርበዋል።
ለምሳሌም በጉጂ እና በጌዴኦ መካከል እንዲሁም በቡራዩ ከተማ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ያነሱ ሲሆን፥ በቅንጅት በተሰራው ስራ በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ መኖሪያቸው የመመለስ እና አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ ያጋጠመውን ችግር ያነሱ ሲሆን፥ በዚህም በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸው፣ የበርካቶች ህይወት ማለፉንና የመንግስትን መዋቅር እስከ ማፍረስ የደረሰ ቢሆንም፥ በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ ችግሩን የማስቆም እና አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልልን ከሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ቦረና እና ሀረርጌ አካባቢዎች ግጭት እንዲፈጠር የተለያዩ ሴራዎች ሲሸረቡ ቢቆዩም የሁለቱ ክልሎች መንግስታት ችግሩ እንዳይፈጠር በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋልም ነው ያሉት።
የሀይማኖት ግጭት ለማስነሳትም ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ በተቀናጀ መንገድ በጎባ እና በአሰላ ከተሞች እንዲሁም በአርሲ ዞን የነበረው እንቅስቃሴ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ያሉ ሲሆን፥ የፀጥታ ሀይሎች እና ህብረተሰቡ ባደረጉት ጥረት እቅዱ መክሸፉን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በክልሉ አስተዳደር እና ሰላም ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ እንደ መሬት ወረራ፣ የኢንቨስትመንት ጉዳት፣ የደን ሀብት ዘረፋ እና ምንጣሮን ጨምሮ ሌሎች አደገኛ እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም፤ እልባት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ የመንግስት ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ይቀጥላል ያሉ ሲሆን፥ የክልሉ ህዝብም አስፈላጊውን ማድረግ አለበት ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ለማ አክለውም ባለፉት ስድስት ወራት የህግ የበላይነትን ከማስከበር እና ሰላምን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በክልሉ የተጀመሩ የኢኮኖሚ አብዮትን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውንም አንስተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በግብርናው ዘርፍ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱ ሲሆን፥ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳደጉ የተለያዩ አሰራሮች ወደ ስራ እንደገቡ መደረጉን አንስተዋል።
በዚህም መሰረት በ2010/2011 የምርት ዘመን በበልግ ወቅት ከታረሰው 819 ሺህ ሄክታር መሬት 9 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ሰብል መሰብሰቡን የማእከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያመለክትም በሪፖርታቸው አቅርበዋል።
በተመሳሳይ በመኸር እርሻ ከታረሰው 5 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይም 171 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ሰብል ይሰበሰባት ተብሎ መገመቱንም አንስተዋል።
በቡና ልማት በተከናወነው ስራም በ17 ዞኖች በተካሄደው የቅድመ ምርት ስብሰባ ግምት ከ687 ሺህ በላይ ቶን ቡና ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል ያሉ ሲሆን፥ ክልሉ 54 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡንም አስታውቀዋል።
በመጠጥ ውሃ አቅርቦትም በ2010 በጀት ዓመት መጨረሻ 63 ነጥብ 8 በመቶ ነበር ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፥ ባለፉት 6 ወራት በተሰራው ስራ ወደ 64 ነጥብ 5 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
በመንገድ ልማት ባለፉት ስድስት ወራት በገጠር መንገድ ልማት 317 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ እና የድልድዮች ግንባታ መጀመሩን እንዲሁም 1 ሺህ 415 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና መከናወኑ በሪፖርታቸው ተመልክቷል።
በስራ እድል ፈጠራም በአጠቃላይ ለ355 ሺህ 900 ዜጎች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የስራ እድል ተፈጥሯል ያሉ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ በከተሞች ለ72 ሺህ 300 ሰዎች፤ በገጠር ለ116 ሺህ ሰዎች ቋሚ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ናቸው።
በኢንደስትሪ ልማትም የክልሉን ግብርና ለማዘመን እና የግብርና ምርት ላይ ግብአት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉት የቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ኢንደስትሪ ፓርክ እና የሻሸመኔ የገጠር ትራንስፎርሜሸን ማእከል ግንባታ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
እንደ ሪፖርታቸው በትምህርት ዘርፍም በክልሉ በሚገኙ 16 ሺህ 234 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 9 ነጥብ 6 ሚሊየን ተማሪዎች በመደበኛ እና በቅድመ መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
23 ሺህ 500 መምህራንም የአመራር እና የስራ አቅማቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ የትምህርትና ስልጠና እድሎች መመቻቸታቸው ተነግሯል።
በጤናው ዘርፍ በተሰራው ስራም በተለይም የማህበራዊ የመድሀን አገልግሎትን በአዳዲስ 46 ወረዳዎች እና 5 ከተሞች ማስጀመር ተችሏል ያሉ ሲሆን፥ በጥቅሉም 242 ወረዳዎች እና 5 ከተሞች የማህበራዊ የመድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ያነሱት።
በገቢ አሰባሰብም ባለፉት ስድስት ወራት 9 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ተሰብስቧል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፥ ይህም ከእቅዱ አንፃር ሲታይ አፈፃፀሙ 102 ነጥብ 7 በመቶ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት የክልሉ መንግስት አፈፃፀም እንደ መስሪያ ቤቶቹ ልዩነት ቢኖረውም መልካም መሆኑን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ፥ ክልሉ ከነበረበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የታቀደውን ስራ ሙሉ በሙሉ መስራት ባይቻልም በቀሪ ጊዜያት ያለውን የሰው ሀይል፣ እውቀት እና ገንዘብ በማቀናጀት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራም አንስተዋል።
በሙለታ መንገሻ | ፋና