የአዲስ አበባንና ዙርያዋን የህዝብ ተዋጽኦ Demography ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን አቶ ለማ መገርሳ በኦሮምኛ ቋንቋ የተናገሩት | ርዕዮት
“የከተማ ፖለቲካን (አርበን ፖለቲክስ) ማጤን አለባችሁ፤ ችላ ልትሉት አይገባም፤” ያላችሁት፣ ትክክል ነው፡፡ የከተማ ፖለቲካ (አርበን ፖለቲክስ) ሊጤን ይገባዋል፣ ምክንያቱም የዚህ ሀገር ፖለቲካ ማእከል (ሴንተር ኦፍ ፖለቲክስ) ከተሞች ስለሆኑ ነው፡፡ የዚህን ሀገር ፖለቲካ የሚወስነውም ከተማ ነው፤ ከተሞች ናቸው፡፡ የከተማ ውስጥ ፖለቲካ ማለት አንድ ቁጥር ዲሞግራፊ (የህዝብ ስርጭት) ነው፡፡
እዚያ ላይ አንዱን ወደዚያ መግፋት፣ አንዱን ወደዚህ መጎተት፣ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት ሳይሆን፣ እንደ ኦሮሚያ ብዙ ነገሮች እየሰራን እንዳለን መገንዘብም ያስፈልጋል፤ በቂ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የጀመርነው በጣም አበረታች ነው፡፡ ከሶማሌ የተፈናቀሉትን ከ 500፣000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ የሆኑ ሰዎች፣ እንደምንሆነው ሆነን፣ ገፍተንም፣ ምንም ብለን፣ ከዚህም ከዚያም ብለን፣ የገዳ አባቶችንም፣ ሽማግሌዎቻችንንም ይዘን፣ እንደለመድነው እርቅ ፈጥረን፣ አቅፈን፣ ስመን ወደ ነበሩበት ቦታ ልንመልሳቸው እንችል ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ መመለስ ይቻል ነበር፤ እኛ ግን ልንመልሳቸው አልፈለግንም፡፡ ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ለኦሮሞ አንድነት፣ ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ዛሬም ችግር ላይ ያሉ ቢሆንም፣ ገጠር አላሰፈርናቸውም፤ ከተማ ነው ያሰፈርናቸው፣ እነዚህን ሰዎች፣ እወቁ፡፡
በአንድ ጊዜ ከ 500፣ 000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ ሰዎችን፣ እንዲያውም አዲስ አበባ ዙሪያና አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 6000 (ስድስት ሺህ) አስገብተናል፤ አዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ አይደለም፡፡ እኒህን ከዚያ የተፈናቀሉትን ሰዎች፣ የዚህን አካባቢ ባህል የማያውቁ ሰዎች፣ በብዙ ነገሮች ከአካባቢው ጋር የማይመሳሰሉ፣ ይቸገራል መችም፣ ይቸገር፤ ዛሬ ችግር
የማያጣው ቢሆንም፣ ከተቸገረም እዚሁ ከተማ ውስጥ ይቸገር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በእግሩ የሚቆምበት መሬት ይኑረው፤ እሱ ቢቸገርም ለልጆቹ የሚሆን ስለሆነ፣ ብለን ህዝባችንንም አስቸግረን ካለን ነገር ላይ አዲስ አበባ ዙሪያ ነው ያሰፈርናቸው፡፡ አብዛኛው የሀረርጌ ሰዎች ናቸው፣ እወቁ፡፡ ቦርደዴ ማስፈር ይቻል ነበር፤ ምስራቅ ሀረርጌ ልናሰፍራቸው እንችል ነበር፡፡ ማስፈር ትክክል ከሆነ እንዲያውም እዚያው አካባቢ ነበር ማስፈር የሚገባው፤ ያን ባህል ነው የሚያውቀው፣ ያን አየር ነው የሚያውቀው፡፡
ወደማያውቀው ባህል እዚህ አምጥተን አዲስ አበባ ውስጥ አሰፈርነው፡፡ ቢቸገር ቢቸገር ሁለት ዓመት ነው ሊቸገር የሚችለው፤ ከዚያ በኋላ ሰው ሆኖ ይወጣዋል፡፡ ይሄ በፖለቲካ ላይ ያለው ፋይዳ፣ ሄዶ ሄዶም በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ በመሆኑ፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ ስለሚፈይድ፡፡
ወጣቱንም ስራ እናስይዛለን ብለን በንግድ ስም፣ በሌላም ነገር ስም ብዙ ነገር ስናደርግ ነበር፤ እናም አብዛኛውን ከተማ ውስጥ አስገባነው፡፡ ወደ ከተማ ስናስገባው የሚኖርበት ቦታ ኖሮት ነው፡፡ ከ500፣ 000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ የሚሆኑ የኦሮሚያን ክልል ሰራተኞች ዘንድሮ መሬት የሰጠናቸው ገጠር ውስጥ አይደለም፤ ይብዛም ይነስም ከተማ ውስጥ ነው የሰጠናቸው፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ ነው የሰጠናቸው፡፡ ብዙ ልንቆጥር እንችላለን፡፡ ይሄ በቂ ነው ብዬ አይደለም፤ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ሆኖም ችላ ያልነው ነገር አይደለም፤ እየተሰራበት ያለ ነገር ነው፡፡ ስንሰራም በከፍተኛ ጥንቃቄ መስራት የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ይህም በዚሁ ረገድ ቢታይ መልካም ይሆናል ብዬ ነው የማየው፡፡