የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በአስረኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች መነሻ በማድረግ የተከናወኑ የባለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸም ገምግሟል፡፡ በሂደቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን ይበልጥ በማጎልበት የታዪ ጉድለቶችን በሚያካክስ መልኩ ለማረም የሚያስችል ግምገማ አካሂዷል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው በድርጅቱ መሪነት፣ በህዝቦች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ባለቤትነት በሀገርና በክልል ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ያለበትን ደረጃ በጥልቀት መክሮበታል፡፡ እንዲሁም በጠንካራ የህዝቦች ትስስር ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት፣ ልማትን ለማፋጠንና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ የክልላችን የአደረጃጀት ጉዳይና በደኢህዴን የወደፊት ጉዞ ላይ በስፋት ተወያይቷል፡፡

እንደሀገር የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ጥልቅ ከመሆኑም በላይ የመጣው ተስፋና እየተመዘገበ ያለው ውጤት ሰፊ እና ሁሉንም ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ሆኖ እያለ ፣ ማንኛውም እምርታዊ ሪፎርም እንቅስቃሴ ሊያጋጥሙት የሚችል ከተስፋው በተቃራኒ ለውጡን በእጅጉ የሚፈታተኑ ሥጋቶችም የተጋረጡበት እንደሆነ ደኢህዴን በእጅጉ ይገነዘባል፡፡ ድርጅታችን ከሁሉም በላይ ክልላችንን ለአደጋ የዳረጉ ድክመቶችን ለይቶ በማውጣት የህዝቡ መሠረታዊ የሆኑ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የአደረጃጀት ጥያቄዎችን የህዝቡን አዳጊ ፍላጎት በዘላቂነት መመለስ በሚያስችል የአመራር ቁመና መምራት እንዳለበት በመረዳት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡

ደኢህዴን ራሱን ከለውጡ ጋር እያስተሳሰረና እያጣመረ ለሀገራዊ ለውጡ የራሱን የማይተካ ሚና የተወጣ እንደመሆኑ መጠን በክልላችን የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲሰፋ፣ ዜጎች የመሰላቸውን ሃሳብ በነፃነት የሚያራምዱበት ዴሞክራሲያዊ አሰራሮችን በመዘርጋት የተፈጠረውን የለውጥ ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው እየሰራ ይገኛል፡፡

በፌዴራል ስርዓት ውስጥ የህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ፣የእኩልነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በነፃነት የመስራት፣ የመኖር መብቶች ሁሉ በትክክለኛ ገፅታና በተሟላ መንገድ እንዲከበሩ፣ በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀል እንዲቆምና ህገ – መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበር የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አፅንኦት ሰጥቶ ገምግሟል፡፡

በክልላችን ውስጥም ሆነ ከክልል ውጭ የዜጎቻችን ህይወት እና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ አስነዋሪና ሊደገም የማይገባው መሆኑን ድርጅታችን ያምናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የህይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡ በቀጣይ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ ችግር የፈጠሩና የህዝቡ ሰላም እንዲናጋ ምክንያት የሆኑ አካላትን ለህግ የማቅረብ ተግባሩ ጎን ለጎን ችግሮች በተፈጠሩበት አከባቢ የህዝብ ለህዝብ ስራን የማጠናከርና ጉድለቶችን የመፍታት፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ኑሯቸው በፍጥነት ማስመለስና መልሶ ማቋቋም እንዲሁም በዘላቂነትም ዜጎች በሁሉም አከባቢ በሰላም መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ዋስትና ማረጋገጥ ለምርጫ የማይቀርብ መሆኑንም አይቷል፡፡

የፌዴራል ስርዓቱ ለክልላችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ድርጅታችን ያምናል፡፡ በመሆኑም ብዝሃነትን በመምራት ልምድ ያለው ድርጅታችን የክልሉን ህዝቦች አንድነት ማጠናከር ለኢትዮጵያዊ አንድነታችን ያለው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ ስለሆነም ህብረብሄራዊነትን የሚያስተናግደው የፌደራል ስርዓት አጠናክሮ ማስቀጠል የክልሉ መሪ ድርጅት የሁል ጊዜ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል እንዳለበት ተሰምሮበታል፡፡

አሁን በክልሉ ውስጥ የሚነሳውን ተጨማሪ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄ መላውን የክልሉን ህዝብ በሚጠቅም አኳሃን በተረጋጋና እጅግ ኃላፊነት በተሞላው እና ዘላቂ መፍትሄ በሚያመጣ መንገድ በድርጅቱ መመራት እንዳለበት መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ ስለሆነም እየተነሱ ያሉ አዳዲስ የክልል ጥያቄዎች የክልሉን መሪ ድርጅት ቀጣይነት፤ አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ እና የሁሉንም ህዝብ ጥቅም ማእከል ተደርጎ መታየት እንዳለበት ማእከላዊ ኮሚቴው አፅንኦት ሰጥቶ መክሮበታል፡፡ ድርጅቱንም ከየትኛውም ጥቃት መከላከል የሚችል አመራርና መዋቅር በቀጣይነት መገንባት እንደሚገባንም አይተናል፡፡ የተጀመረውን የለውጥ ፍላጎት መምራት የሚችሉ ምሁራን፣ ወጣቶችን እና ሴቶችን ማእከል ያደረገ የምልመላና የግንባታ ስራ አጠናክረን መቀጠል እንዳለብን ወስደናል፡፡

በመላው የክልላችን አካባቢዎች የግብርናን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የተቀናጀ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አኳያ የሚታየውን ቀርፋፋ አፈፃፀም፣ የወጣቱን ጉልበቱንና ዕውቀቱን አስተባብሮና አደራጅቶ ወደ ምርት ተግባር እንዲገቡ አሳምኖ በብቃት ከመምራት፣ ሴቶችና ወጣቶች በሁሉም የልማት መስኮች በሰፊው እንዲሳተፉ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ የሚታዩ ጉድለቶች ለማረምና ውጤት ለማምጣት በማኑፋክቸርንግ ዘርፉ ላይ ትኩረት በመስጠት የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ለማቀጣጠል ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተመክሮበታል፡፡ የብዙሃን ማህበራትና ሌሎች የዴሞክራሲ ግንባታ ተቋማት አያያዝና አጠቃቀምን በሚገባ ተንትኖ ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል አለብን፡፡
በአጠቃላይ በድርጅታችን አስረኛ ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መነሻ በማድረግ የህዝቡን ፍላጎት በለውጥ መንፈስ በፍፁም ቅን ልቦናና ህዝባዊ ወገንተኝነት በመስራት የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ይበልጥ ማጠናከር ታሳቢ በማድረግ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከተውን ባለ ዘጠኝ (9) ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1. ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው፡፡ ሰላም ለህዝቦች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጥን ለመጓዝ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ በመሆኑን በተለያዩ ጊዜያት በክልላችን ውስጥ ሆነ ከክልላችን ውጪ የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት ነባር የሆኑ ባህላዊ እሴቶቻችንን በመጠቀም አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ እንሰራለን፡፡ በእስካሁኑ ሂደት የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች ያበረከቱት አስተዋፆኦ ከፍተኛ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው በአድናቆት ገመገመ ሲሆን በቀጣይነት ዘላቂ የሆነ ሰላም እና ፀጥታን ለማስፈን ህብረተሰቡ በጋራ የመኖር እና የአብሮነት እሴቱን ማጠናከር እንደሚገባ አስምሮበታል፡፡ በፀጥታ ችግር ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ እና የህግ የበላይነት ከማስከበር አኳያ በርካታ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም አሁንም ወደቀያቸው ያልተመለሱ ዜጎች እና ለህግ ያልቀረቡ ወንጀለኞች በመኖራቸው የፍትህ ተቋማትን አቅም በማጠናከር መላው ህዝባችንን በማሳተፍ ችግሮችን በዝርዝር የመፍታት ሁኔታ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተቀምጧል፡፡ በማያያዝም ክልሉን የሚያዋስኑ አጎራባች ሃገራት ድንበር አካባቢ የሚታዪ የፀጥታ ችግሮችም ሆነ በውስጣችን ከወሰን ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሱ አለመግባባቶችን ከፌደራል መንግስት እና ከክልሎች ጋር በመሆን በዘላቂነት እንዲፈታ አፅንኦት ሰጥተን እንሰራለን፡፡

2. ብዝሃነትን ያለ አድልዎ ማስተናገድ የሚችል እንዲሁም ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ማጠናከር የሚችል የፌደራሊዝም ስርዓት ዕውን እንዲሆን መላው የሀገራችን ህዝቦች ከዳር እዳር በጋራ የታገሉለት ዓላማ መሆኑን ደኢህዴን በፅኑ ያምናል፡፡ ክልላችን የተለያዩ ብሄር ብሔረሰቦች እና ህዝቦችን ያቀፈ እንደመሆኑ በፌደራሊዝም ስርዓት ይበልጥ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በዚህም ህዝቦችን በፍትሃዊነት መንገድ ማስተናገድ የሚችል የፌደራሊዝም ስርዓት እያጠናከርን መሄድ ለክልላችን ህዝቦች የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ህብረብሄራዊነትን ለመናድ የሚነሳው የትኛውም ኃይል የብሄር ብሄረሰቦችን እና የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ድርጅታችን ደኢህዴን ስርዓቱን ለመጠበቅና ለማበልፀግ ግንባር ቀደም ሆኖ ይታገላል፡፡

3. በሀገራችን የተጀመረው የመለውጥ ፍላጎት ከጫፍ እስከ ጫፍ በህዝባዊ ማዕበል ታጅቦ በተቀሰቀሰበት ወቅት ለዉጡ እዉን እንዲሆን ድርጅታችን ደኢህዴን የራሱን የማይተካ ሚና ተጫዉቷል፡፡ ለለውጥ በር ከፍቶ መቀበል ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ለውጡን በብቃት መምራትና ከጫፍ ማድረስ መላው ህዝብ ከለውጡ ትሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ድርጅታችን ያለበት ታሪካዊ ሃላፊነት እንደሆነ በሚገባ ይረዳል፡፡ ስለሆነም መላው የክልላችን ህዝቦች ከለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተጀመረውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የህግ እና የመ/አስተዳደር ሪፎርም ስራዎችን በላቀ ደረጃ ለመተግበር የሚሰራ ይሆናል፡፡ የለውጡ አደናቃፊ የሆኑ አስተሳሰቦችን እና ተግባራትን ከአባሉ፣ ደጋፊዎችና ከመላው ህዝባችን ጋር በመሆን እንታገላለን ለውጤታማነቱም ሌት ተቀን እንሰራለን፡፡

4. ድርጅታችን የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ይበልጥ እያጠናከረና እያሰፋ ለመሔድ በውስጡ ገምግሞ የለያቸውን ድክመቶች ሙሉ በሙሉ እየቀረፈ መጓዝ አለበት፡፡ ስለሆነም ራሱንም እየለወጠ ለውጡን መምራት የሚያስችል እርምጃዎች ይወስዳል፡፡ ከዚህ አኳያ በአመራር፣ በአሰራርና አደረጃጀት የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት የአመለካከት እና የተግባር አንድነት በማዳበር ህዝቡን ለመካስ ልዪ ትኩረት ተሰጥቶ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ በመሆኑም የድርጅቱ የወቅቱን የህብረተሰብ አስተሳሰብ ደረጃና ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ከድርጅቱ አርማና ስያሜ በተጨማሪ ውስጣዊ የይዘት ለውጥ በማድረግ ለህዝቦች ጥያቄ ፈጣንና አርክ ምላሽ ለመስጠት አበክረን እንሰራለን!!

5. በ10ኛው የደኢህዴን ድርጅታዊ ጉባኤ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ አቅጣጫ ከተቀመጠላቸው ጉዳዮች አንዱ አዳዲስ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ጥያቄ በክልላችን አሁን ያለበት ደረጃና በጉባኤው በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየተፈፀመ ስለመሆኑ በዝርዝር ተገምግሟል፡፡ ዘላቂ መፍትሄውን በተመለከተ፤ በሰከነ እና ሃላፊነት በተሞላ መንገድ ማየት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ማእከላዊ ኮሚቴው ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቶበታል፡፡ በመሆኑም በክልላችን እየተነሱ ያሉ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄዎች የህዝቦችን ትስስርና አንድነት በሚያጠናክር፣ የድርጅት ቀጣይነትና የሁሉንም ህዝቦች ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አኳኋን በደኢህዴን መሪነት እንዲፈፀም ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፡፡

6. በደኢህዴን ጉባኤ ወቅት ከተወሰኑ ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ ሌብነት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን በየደረጃው ፈትሾ አስተማሪ እርምጃዎችን በመውሰድ ሂደት ከህዝብ ጋር ግልጽኝነትን ፈጥሮ መንቀሰቀስ እንደሚገባን የተቀመጠ ቢሆንም የተሰሩ ስራዎች በቂ አለመሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ ስለሆነም የተጀማመሩ ተግባራትን ማጠናከር እንደተጠበቀ ሆኖ ከላይኛው እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ህዝቡን ባሳተፈ መንገድ ተጨማሪ ፍተሻ እና የማጥራት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥልና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አበክረን የምንሰራ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

7. የዴሞክራሲ ምህዳርን ከማስፋት ረገድ የትኛውም የሀሳብ ልዩነቶች በነፃነት እንዲራመዱ ለማስቻል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሀሳብ ይዘው ሲቀርቡ በጥርጣሬ እና ወደ ፍረጃ ከመግባት ይልቅ ዴሞክራሲያዊ ትግል በማድረግ በኩል የተጀማመሩ ስራዎች ቢኖሩም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ይበልጥ በመቀራረብ ተቋማዊ በሆነ መንገድ የጋራ ምክር ቤቶችን በማቋቋም በጋራ መስራት ላይ ጉድለቶች እንዳሉ ተገምግሟል፡፡ በመሆኑም በከልላችን ሆነ በሀገር ደረጃ በሰለማዊ መንገድ ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሱ ካሉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር በማድረግ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፡፡

8. የኢኮኖሚ ልማታችንን በማፋጠን ረገድ በግብርና መስክ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችና ግብዓቶች ማቅረብ እንደ ወሳኝ ተግባር ተወስዶ አሁን ካለበት መፋዘዝ እንዲወጣ ሊሰራበት እንደምገባ ውይይት ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ክልሉ በእንስሳት ሃብት ያሉትን ጸጋዎችና ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ በማልማት የአርብቶ አደሩን ህይወትና የኑሮ ደረጃን ትርጉም ባለው ደረጃ በማሻሻል ረገድ ሰፊ ጉድለት የሚታይበት በመሆኑ በዝርያ ማሻሻል ስራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ህይወት የምናመጣው ለውጥ ለገጠር ትራንስፎርሜሽን ግባችን ስኬት ብሎም ለከተሞች ልማትና ወደ ኢንዱስትሪ ለምናደርገው ግስጋሴ ያለውን ወሳኝነት በመረዳት በዘርፉ የሚስተዋሉ አደናቃፊ አሰራሮችና ማዕቀፎችን ፈትሾ በማስተካከል የሚሰራ ይሁናል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአርብቶ አደር አከባቢ ለመንደር ማሰባሰብ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት እና ያሉ የመስኖ አውታሮችን የማጎልበት ስራ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በማንፋክቸርንግ ዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለይቶ በመፍታት በኢኮኖሚ ልማቱ የኢንዱስትሪ መሪነቱ እውን ለማድረግ ርብርብ ተደረጎ ልማቱን ለማሳለጥ የሚሰራ ይሆናል፡፡

9. ሴቶችና ወጣቶች በሀገራችን ሆነ በክልላችን ለተጀመረው ለውጥ ያበረከተው አስተዋፆኦ ግሉህ ድርሻ አለው፡፡ በክልላችን እና በሀገርቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመልካም አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በባህላዊ ልማት ውስጥ የተደረጀና የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ በየደረጃው የተከናወኑ ተግበራት ቢኖሩም አሁንም የወጣቶችና የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚፈለገው ደረጃ ያልደረሰ፣ መሆኑን አፅንዖት ሰቶ ተወያይቶበታል፡፡ በዚህም በለውጡ ሂደት ባበረከተው አስተዋፆ ልክ ተጠቃሚ እና ተሳታፊ እንዲሆን አሁን በወጣቱ ዘንድ እየታየ ያለውን ሰፋ ያለ የስራ አጥነት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማድረግ ከራሱ ከወጣቱ እና ከመላው የባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ቃል እንገባለን፡፡

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ
የካቲት 18/2011 ዓ.ም
ሀዋሳ

LEAVE A REPLY