አንዳንድ ነገሮች | በአቢይ አፈወርቅ

አንዳንድ ነገሮች | በአቢይ አፈወርቅ

አንዳንድ ነገሮች፣

. . . ዕጹብ ድንቅ ናቸው፦

እንደ ንጋት ጸሀይ፣ መንፈስ የሚያሞቁ፤

እንደ አመሻሽ ጀምበር፣ ውበት የሚያፈልቁ፤

የልብ የሚያደርሱ፣ ለነፍስ የቀረቡ፤

ከኮተኮቷቸው፣ ሁሌም የሚያብቡ።

 

አንዳንድ ነገሮች፣

. . . ግዙፍ እልፍኝ ናቸው፦

ሁሉን ያካተቱ፣ ከባህር የሰፉ፤

ሁሉ የኔ ‘ሚላቸው፣ በፍቅር የፋፉ፤

ውብና ፀዓዳ፣ ልዩ አዳራሽ ናቸው፤

እልፍኝ አስከልካዩ፣ ካላጠበባቸው።

 

አንዳንድ ነገሮች፣

. . . ልዩ ፍቅር ናቸው፦

እንደ ዓይን ብሌን፣ እንደ ህጻን ገላ፤

ወድቆ እንደሚሰበር፣ እንደልዩ ሸክላ፤

የሚሳሳላቸው፣ ለትልቅ ትንሹ፤

ሁነኛ ተመልካች፣ ተሟጋች የሚሹ።

ጉድፍ አራጋፊ፣ ቢያጠፉ መካሪ፤

የምር ካገኙ፣ ዓይን ከፍቶ አፍቃሪ፤

አንዳንድ ነገሮች፣ ሁሌም ህያው ናቸው፤

ማደግ ማበብ እንጂ፣ ሞት የማያውቃቸው።

 

አንዳንድ ነገሮች፣

. . . መገበዝ አያውቁም፦

ቢያጠፉ እንዳላየ፣ ቢስቱ እንዳልሰማ፤

በዝምታ አርጩሜ፣ በ’ዕውር ፍቅር’ ሳማ፤

ክቦ ከሚያሳንስ፣ እልፍ ስሜተኛ፤

ፍቅር ይደረጃል፣ በአስር እውነተኛ።

 

LEAVE A REPLY