የኢትዮጵያውያን ዜጎች ነጻነትና እኩልነት | ነአምን ዘለቀ

የኢትዮጵያውያን ዜጎች ነጻነትና እኩልነት | ነአምን ዘለቀ

የህግ የበላይነት እንጂ የትኛውም የብሄር የበላይነት ማንም አትራፊ ወደ ማይሆንበት ገሃነም እንዳይወሰድን የብሄር ፓለቲካ አቀንቃኝ ልሂቃን ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው።

አንድ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር [ኦነግ] አመራር አባል በቅርብ ቀን በቴሌቪዥን የሰጠውን ቃለ ምልልስ ተከታተልኩ። እጅግ ያሳዝናል፣ ። የብሔር ፓለቲካ ልሂቃን ፋሽስታዊና ኋላቀር አስተሳሰብ ምን አይነት ዋጋ እንደሚያስከፍል ለመረዳት ህሊናቸው እንደተጋረደባቸው የግለሰቡ ንግግር ሌላው ማረጋገጫ ነው። ግለሰቡ የተናገረው በኦሮሞ ክልል “የኦሮሞ የበላይነት ማረጋገጥ” ነው ያለው። ልብ እንበል’’ ፍትህ፣ ነጻነት፣ እኩልነት፣ እኩል ተጠቃሚነት ለኦሮሞም ሆነ ኦሮሞ ያልሆኑ ነገር ግን በኦሮሞ ክልል ከቅድመ አያቶቻቸው ጀምሮ በኦሮሞ ክልል ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ጭምር ይስፈን አልነበረም መልዕክቱ። ግለሰቡ በክልሉ “የኦሮሞ የበላይነት” በሚል ቃላት አስረግጦ ነበር የተናገረው።

እንዲህ አይነቱ ፋሽስታዊና የጨቀየ አስተሳሰብ ለታላቁ የአሮሞ ህዝብም ሆነ ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላምን፣ የህግ የበላይነትን፣ ማህበራዊ ፍትህን፣ ዴሞክራሲን፣ እኩልነትን፣ ለኦሮሞ ወጣቶችም ሆነ ለኢትዮጵያ ወጣቶች የስራ ዕድልን፣ አጠቃላይ ልማትን፣ ሀገራዊ እድገትን ፈጽሞ የሚያመጣ ሳይሆን ማለቂያ ለሌለው መከራና ትርምስ ሀገራችንን ላይ የሚጋብዝ እጅግ አደገኛ ጽንፍ የያዘ አስተሳስብ መሆኑ ግልጽ ይመስለኛል።

በአሜሪካን አገር ጥገኝነት ጠይቆ፡ እያንዳንዱ አሜሪካዊ ዜጋ የሚያገኛቸውን መብቶች፣ ነጻነቶች፣ ጥቅሞች የተከበሩለት የኦሮሞ ህዝብ ወኪል ነኝ የሚል ግለሰብ፣ በኦሮሚያ ክልል ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን መብት አልባ ለማድረግና አዲስ አበባ ከተማ የኦሮሞ ብሔር ልዩ ርስት እንደሆነች አስመልክቶ ከሚሰጠው መግለጫ በመነሳት ከሰሞኑ የተፈጠውን ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ከፍተኛ ስጋትና ውጥረት በጫረው የከረፋ ፋሽስታዊና ጠብ ጫሪ ንግግሮች ስናዝንና ስንቆዝም ከርመን ይስ ብሎ የኦነጉ አመራር ደግሞ ሌላ ቤንዚን አርከፈከፈበት።

በየቦታው ከሚነሱ ግጭቶች ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው የሚያስቡ በየክልሉና በየብሄሩ ያደፈጡና ግጭትና ጥላቻ የሚቀሰቅሱ እነዚህንና መሰል ህሊና እና ራእይ አልባ ጠባብ አክራሪዎችና ስግብግብ ራስ ወዳዶች የእኛ ወይንም “ኬኛ” የሚሉት “ብሔር የበላይነትን” በየክልሉ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ጭምር ለማረጋገጥ በሚወሰዱ የፋሽስታዊ እርምጃዎች ሀገር ወድሞ፣ ዚጎች ተላልቀው፣ ማህበረሰቡ እርስ በእርስ ተጋድሎና ደም ተቃብቶ ፣ አነሱ የሚጠቀሙበት፣ የሚያስቀጥሉት የፓለቲካ ስልጣንም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊኖር እንደማይችል ግልጽ ሊሆንላቸው ይገባል።

በየቦታው የሚነሱ ግጭቶች በሰፉ ቁጥር አደጋው፣ ግጭቱ በተነሳበት አከባቢ ለሚገኙ ማህበረሰቦች ሞት፣ መፈናቀል፡ የንብረት ወድመትና ሁለንተናዊ ኪሳራ የሚያስከትል ብቻ ሆኖ አይቀርም። የማህበረሰቡ ግጭት በሰፋ ቁጥር እነሱ “ወገኔ ነው/የእኔ ብሔር ” ነው የሚሉትና በሌሎች ክልሎች ነዋሪ የሆኑ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸውን ጭምር አደጋ ላይ የሚጥሏቸው መሆኑንን ሊገነዘቡ ይገባል።

ይህ “የእኔ ብሔር በዚህ ክልል የበላይ መሆን አለበት” የሚል ፋሽስታዊ አስተሳሰብ በብሔር /በዘውግ ወግኖ በየአካባቢው የሚገኙ ሌላ ቋናቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊያንን መበደል፣ መግፋት፣ መብታቸውን መንፈግና ወደ ማጥቃት ማምራቱ አይቀሬ በመሆኑ ሄዶ ሄዶ ሌላው ደግሞ በተራው አነሱ “ወገኔ” የሚሉትን በሌሎች ክልሎች የሚበቀልበት፣ በተራው በዚህ ክልል “የእኔ ብሔር በዚህ ክልል የበላይ ነው”፥ የእነቶኔ ብሔር ደግሞ የበታች ነው ወደሚል ሌላው ጽንፍ የያዘ ፋሽታዊ አመለካከት የሚያራምድና በመላው ምድሪቱ የሚያስፋፋ በመሂኑ እያንዳንዱ ከእያንዳንዱ ጋር የሚዋጋበት (A war of each against each) እርስ በእርስ የሚጠፋፋበት አሰቃቂ ሰደድ እሳት ሀገራዊ ገሃነም ሊያመራ እንደሚችል፣ ሁሉም ተያይዞ የሚጠፋበት ሁሉን አውዳሚ ጎዳና ሊሆን አንደሚችል እነዚህ የደነዘዙ በ21ኛ ክፍለ ዘመን ላይ ሆነው የአንድን ብሔር የበላይነት የሚገፉ የየብሄሩ ልሂቃን ቆመው በጥልቀት ማሰብ አለባቸው። ለማሰብ የሚችል ልቦና እና ህሊና ካላቸው ማለት ነው።

በእንደዚህ አይነቱ ማባሪያና ማለቂያ የሌለው ትርምስና የገሀነም እሳት የሚጠቀም፣ አሸናፊ የሚሆንም እንደማይኖር መረዳትም ይገባቸዋል። በተለይም ይህን የሚቀሰቅሱ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በሌሎችም ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የየብሄሩ ልሂቃን፣ ባለስልጣኖችና ባለሀብቶች በሚገባ ሊያውቁትና ሊረዱት ይገባል።

ይህ በብዙ አካባቢዎች የሚታይ፣ በአንዳንድ የየብሄሩ ሊሂቃን የሚራገብ የብሔር የበላይነት አስተሳሰብና ከዚሁ የሚመነጩ ግጭቶች ሄዶ ሄዶ እነሱንም የሚያጠፋ፣ የቤተሰብ ፣ የሀብት ንብረት መሰረታቸውን፣ የራሳቸውንም ህይወት ሊቀጥፍ የሚችል ገሀነም ተቀስቅሶ በሶሪያ፣ በየመን፣ በሶማሊያ፣ በዮጎዝላቪያ ከታዩት የሀገሮች መፈራረስና፣ መበታተንና የህዝቦች ዘግናኝ እልቂት የባሰ እሳተ ጎሞራ መጥቶ የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ህይወትና ህልውና ሊያጠፋ የሚችል፣ በዚች ምድር የተፈጠረ ዜጋ ከነቤተሰቡ የመኖር ያለመኖር፣ ኢትዮጵያንም እንደ ሀገር የመቀጠል ወይም ያለመቀጠል ከባድ የህልውና አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል በጥልቅ መረዳት አለባቸው። ማንም አሸናፊ አይሆንም።

በአሜሪካ አገር በሚታተመው የፎርዬን ፓሊሲ ጆርናል (Foreign Policy) የቅርብ ሳምንት እትም ላይ የወጣ ጽሁፍ እንዳስቀመጠው ኢትዮጵያ ወደ “ዩጎዝላቪያ መሰል ውድቀትና መፈራረስና እንዳታመራ ማዳን አለብን” በሚል ርእስ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚጫሩና ከማንነትና/ብሔር ተኮር ግጭቶች ወዴት አይነት ዘግናኝ ደረጃ ተቀናብረውና ተዳምረው ወደ ሀገር መፍረስ እንደሚያደርሱ ከፍተኛ ስጋት ፈረንጆቹ እንኳን ተረድተው እያስጠነቀቁ ይገኛሉ’።

የማነንት ፓለቲካ/የብሔር ፓለቲካ ሀገርን የሚያናጋ/ህዝቦችን የሚያጋጭ፣ ዜጎችን አግላይና ኢፍትሃዊ የሆኑ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን የሚቀፈቅፍ እንጂ አብሮነትን፣ ፍትህን፣ ነጻነትና፣ እኩልነትን የሚያረጋግጥ አለመሆኑ የአለፉት 27 አመታት ተሞክሮ በሚገባ አሳይቶናል። ይህ ነቀርሳ አሁንም የሀገራችንን ህልውና ለከፍተኛ አደጋ ላይ ጋርጦታል። ከ10 ወር በፊት የመጣውን ለውጥና የነጻነት አየር እንዳያጣጥም ከፍተኛ ስጋትና አደጋ እንዲያንዣብብ አድርጎታል።

ስለዚህ መፍትሄው አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ የሁሉንም ዜጎች እኩልትነት የተረጋገጠባት፣ ማንም ብሔር ከሌላው ብሔር በየትኛውም አካባቢ የበላይ ያልሆነባት፡ ሁሉም ብሄሮች በሁሉም ክልሎች በእኩልነትና በህግ የበላይነት፣ በሰላም የሚኖሩባት፣ ፍትህ፣ የግለሰቦች መብትና ነጻነት፣ የሁሉም ብሄሮች/የማህበረሰቦች የባህልና የቋንቋ እኩልነት፣ ማህበራዊ ፍትህ፣ ዴሞክራሲያዊ የፓለቲካ ስርአት እውን እንዲሆኑ መታገል ነው የሚያዋጣው፣ ሃገራዊ አንድነትን፣ ህዝባችን ከሚገኝበት ከድህነት ወደ ብልጽግና፣ከውድቀት/ድቀት ወደ ልማት እንድንጓዝ የሚያስችለን ይኸው መንገድ ብቻ ነው።

ከብሔር /የማንነት ፓለቲካ ወጥተን ወደ ዜግነት ፓለቲካ መራመድ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን ለሁሉም ዜጎች የምትመች፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች መብትና ነጻነት የሚከበርባት። የሁሉም ማህበረሰቦችና ቋንቋዎች እኩልነት የተረጋገጠባት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሀገር እንድትሆን የሁሉም ባለድርሻዎች፣ ሃይሎችና እንዲሁም የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት መውሰድን ይጠይቃል።

የብሔር ልሂቃን የሚራምዱትን አደገኛና ፋሽስታዊ አስተሳሰብ አጥብቆ መታገል፣ አደገኛነቱን ማሳየትና በሃሳብ መዋጋት አንዱ የቤት ስራ መሆን ይገባዋል። ሰላምና እርጋታ የተላበሰና የሰከነ ማህበረሰብ መፍጠር ካልቻልን ፣ ስራ አጥነትን ማጥፋት/በእጅጉ መቀነስ ፣ ኢኮኖሚያዊ ልማት ማሳደግ፣ የሕዝብና የሀገር እድገት፣ የዜጎች፣ የማህበረሰቦች የኑሮ፣ የህይወት መሻሻል ሊመጣ አይቻልም። በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሁሉንም ባለድርሻዎች፣ የሁሉንም ሃይሎች፣ የሁሉንም ዜጎች ርብርብና ድርሻ ይጠይቃል።

LEAVE A REPLY