የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ባለፉት 6 ወራት የህዝብና የመንግስትን ጥቅም የሚያስጠብቁ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግባቸው የፌዴራል ተቋማት ፕሮጀክቶችን ውል ስምምነት በማየትና በመመርመር ማስተካከያ ሰጠ፡፡
የተቋሙ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ታሪኩ እንደተናገሩት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዋጀ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 ንዕስ አንቀጽ 4 (ሀ)ና (ለ) የፍትሐብሔር ጉዳዮችን በተመለከተ የፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሕዝብና የመንግስት መብትና ጥቅም ወኪል በመሆን ይከራከራል፣ ያስከብራል፣ እንዲከበሩ ያደርጋል፣ የሚከበሩበትን ሂደት ይከታተላል እንዲሁም ግዙፍ የሆኑ የመንግስት ፕሮጀክቶች የውል ዝግጅት እና ድርድር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማድረግና የማማከር ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን በ2011 ዓ.ም በጀት አመት የመጀመሪያው 6 ወራት እቅድ አፈጻጸም የ21 የፌዴራል ተቋማት ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግባቸውና 2 ውሎች በውስጣቸው 9 የግዥ ማዕቀፍ የያዙ በአጠቀላይ 30 ውሎችን የህዝብና የመንግስት ጥቅምን የሚያስጠብቁና ሕግን የተከተሉ መሆናቸውን በማየትና በመመርመር ማስተካከያ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው አያይዘው የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጡ ፕሮጀክቶች የውል ስምምነት በሚፈራረሙበትና ድርድር በሚያደርጉበት ወቅት በህዝብና በመንግስት ላይ ጉዳት ከመፈጠሩና ኪሳራ ከመድረሱ በፊት መፍትሔ ያለው ግልጽ የሆነ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ውል ማዘጋጀት ላይ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል፡፡
በውል ዝግጅትና ድርድር ወቅት የውል ስምምነት ምርመራ በማድርግ የሀብት ብክነትን መከላከል፣ ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ የሆኑ ተግባሮችን ማስቀረት እና ውል የተያዘላቸው ፕሮጀክቶች ከመፈፀማቸው በፊት ትክክለኛውን የሕግ ማሰሪያ በማዘጋጀት አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩና ከተፈጠሩም ጉዳት ሳይደርስ ለመፍታት የውል ስምምነቶች ሕግን የተከተሉ መሆናቸውን ተቋማት ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ሊያሳውቁ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት የመንግስት ፕሮጀክቶች የውል ስምምነትን ማርቀቅ፣ የተረቀቁ ውሎችን መመርመር እና ድርድር በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ድርድር በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወናቸውን ጠቁመው የፌዴራል ተቋማት ውሎችን በሚፈራረሙበት ወቅት ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ በማክብር ማሳወቅና ማሳተፍ ሲገባቸው እያወቁ በማጥፋት ከፍተኛ የገንዘብ የሚያሰውጡ ውሎችን በመዋዋል በህዝብና በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት ሲደርስ ይታያል፡፡
ተቋማት የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የውል ስምምነት በሚያደርጉበት ወቅት የውል ስምምነት ከማን ጋር እንደሚደረግ ማወቅ፣ ውልን ለማስፈፀም የሚያገለግሉ የሕግ ስምምነትን ማድረግ፣ አስገዳጅ ሁኔታዎችና ዋስትናዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የውል ስምምነት ማዘጋጀት እና አለመግባባቶች ቢፈጠሩ በምን አግባብ እንፈታዋለን የሚለውን መመለስ እንደሚገባና ሁሉም የፌዴራል ተቋማት የሚያደርጓቸውን የውል ስምምነቶች ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማሳወቅና በማስመርመር አገራዊ ንብረትን ከሙስናና ከብልሹ አሰራር መከላከል ይገባል በማለት ተናግረዋል፡፡