1 – በጋምቤላ ክልል ልማት ላይ መሆናቸው የተነገረላቸው 36 እርሻ ልማቶች ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ብድር እና መሬት ወስደው ወደ ልማት ገብተናል ያሉ እርሻዎች ያልተገኙት የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ በጋምቤላ ባደረገው መስክ ክትትል መሆኑን ሸገር ዘግቧል፡፡ አንድ ባለሃብት ብቻ በቤተሰባቸው ስም 1 ሺህ 600 ሄክታር ወስደው ወደ ልማት አልገቡም፡፡ ባጠቃላይ እርሻቸውን ጥለው የተሰወሩ፣ 654 ሚሊዮን ብር ብድር ያለባቸው 36 ፕሮጀክቶች ተገኝተዋል፡፡ 2.5 ቢሊዮን ብር ብድር ያለባቸው 117 የልማት ፕሮጀክቶች ብድራቸውን የመመለሳቸው ዕድል አጣብቂኝ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ክልሉ እርሻቸውን ጥለው የጠፉ ባለሃብቶችን ለመያዝ ጥረት ያደርጋል፡፡
2 – ዋና ኦዲተር ለመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ መምህራን በነጻ የታደሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየመረመረ መሆኑን ካፒታል አስነብቧል፡፡ ለመምህራኑ የተሰጡት በቦሌ ቡልቡላ የሚገኙ 30 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ናቸው፡፡ መምህኑ በወር 5 ሺህ ብር የቤት አበል እያላቸው ነው በ500 ብር ኪራይ እንዲኖሩባቸው የታደላቸው፡፡ አካዳሚው በጠቅላይ ሚንስትር ጽፈት ቤት ስር ያለ የፌደራል ተቋም ነው፡፡ የአካዳሚክ ፕሬዝዳንቱ ጸሃፊ ዳዊት ለገሠ ግን ብቃት ያላቸውን አስተማሪዎች በተቋማችን ለማቆየት ስንል የሰጠናቸው ጥቅማጥቅም ነው ብለዋል፡፡
3 – የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ራስን በራስ ከማስተዳደር መብት፣ ከፌዴራል ሥርዓቱና በሕገ መንግስቱ ከተቀመጡ የመንግስት አስተዳደር ጉዳዮች ጋር አይጣረስም- ብሏል የግንባሩ ምክር ቤት ቤት፡፡ ሆኖም አሁን ጽንፈኛ ብሄርተኝነት እየጎላ መጥቷል፤ ብሄራዊ ማንነትና ሀገራዊ ማንነት ከማስተሳሰር አንጻር ግንባሩ ክፍተት ስለነበረበት ውህደቱ አስፈልጓል ሲሉም አክለዋል የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ምክጽል ሃላፊ መለሰ አለሙ ለፋና ብሮድካስት፡፡ ውህደቱ የጉባዔው ውሳኔ በመሆኑ ብሄራዊ ድርጅቶች ልዩነት አይኖራቸውም፡፡
4 – የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በየካ ክፍለ ከተማ በቅርስነት የተመዘገበውን የደጃዝማች አምኃ አበራ መኖሪያ ቤት በከፊል እንዳፈረሰው ሸገር ዘግቧል፡፡ የከተማዋ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ግን ቅርሱን እንዳያፈርስ ኮርፔሬሽኑ ጋር ደብዳቤ ተለዋውጠን ተስማምተን ነበር ብሏል፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ የቢሮው ሃላፊ ታርጋ የሌለው እስካቫተር ነው ያፈረሰው፤ አፍራሾቹን ከድርጊታቸው አስቁመን በፖሊስ አስይዘናቸዋል ብለዋል፡፡ ካሁን በፊትም ኮርፖሬሽኑ የቅርሱን እልፍኞች አፍርሶ ጉዳዩ ክስ ላይ ነበር፡፡ ቅርሱ የ90 ዐመታት ዕድሜ አለው፡፡ ደጃዝማች አምኃ የእውቁ አርበኛ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው አበራ ካሳ ከወንድማቸው ወንድወሰን ካሳ ጋር ከፋሽስት ጣሊያን ጋር ሲዋጉ ተይዘው በስቅላት የተገደሉ አርበኛ ናቸው፡፡
5 – ትግራይ ክልል ሀገር ዐቀፉ ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መራዘሙን ተቃውሟል፡፡ ለቆጠራው ዝግጅቶች ተደርገው ሳለ በአስቸኳይ ስብሰባ መራዘሙ ሕገ መንግሥቱን ይሸረሽራል፤ ሀገሪቱንም ለኪሳራ ይዳርጋል ብለዋል የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ለኢቢሲ፡፡ ውሳኔው የመንግሥትን የአመራር ግልጽነት አለመኖሩን ያሳያል፤ ሀገሪቱ በዐለም ላይ ያላትን አመኔታ ያሳጣል፡፡
6- ስኳር ኮርፖሬሽን የኦሞ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካን ከሜቴክ ነጥቆ ለውጭ ተቋራጭ ሊሰጥ መሆኑን ሸገር ዘግቧል፡፡ ፋብሪካው በ2005 እንደሚጠናቀቅ ታስቦ አርብቶ አደሮች በ13 ሺህ ሄክታር ማሳ ያለሙት ሸንኮራ አገዳ ከጥቅም ውጪ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አብርሃም ደምሴ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አስረድተዋል፡፡ ለአርብቶ አደሮቹ መጠነኛ ካሳ ሰጥተናል ብለዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለ700 ሠራተኞች ያለ ሥራ ደመወዝ ሲከፍል ኖሯል፤ እናም ከቁጥር 1፣ 590 ሠራተኞችን ወደ ቁጥር 3 ፋብሪካ አዛውሯል፡፡ ቁጥር 1ን ዘንድሮ ይጠናቀቃል ቢባልም ገና ተቋራጭ ስላልተተከበው መተማመኛ የለም፡፡
7 – ዜጎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ዋስትና አስይዘው ከባንክ ብድር እንዲያገኙ የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጅ ትናንት ለሕዝብ ተወካች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ረቂቁ የቢዝነስ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች ግዑዝ ወይም ግዑዝ ያልሆኑ ንብረቶችንና ሃብቶችን፣ ሰብሎችን፣ የመገልገያ መሣሪያዎችን፣ የባንክ ተከፋይ ሒሳቦችን፣ የተረጋገጡ የገቢ ማስረጃዎችን ወዘተ በዋስትና አስይዘው ከገንዘብ ተቋማት እንዲበደሩ ያስችላቸዋል፡፡ ለሥራው ቅልጥፍናም የዋስትና መዝገብ ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም ሃሳብ እንደቀረበ ሪፖርተር አስነብቧል፡፡
8 – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በቻይና ሀገር ዕጽ በማዘዋወር ተከሳ የታሰረችውን ናዝራዊት አበራ ጉዳይ የሚከታተል ቡድን አቋቁሜያለሁ ብሏል፡፡ ቡድኑ በተጠርጣሪዋ ላይ የሚደረገውን ምርመራ ይከታተላል፡፡ የምህንድስና ባለሙያዋ ናዝራዊት ቀደም ሲል ለእስር የተዳረገችው ጓደኛዋ ለሌላ ሰው እንድትሰጥላት አደራ ባለቻት ሻምፖ ቅባቶች ውስጥ ኮኬይን ዕጽ በመገኘቱ ነው፡፡
9 – ከታንዛኒያ ኡኮንጋ ከሚባል እስር ቤት የተገኙ 78 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ሊመልስ እንደሆነ በዳሬሰላም የኢትዮጵያ ኢምባሲ አስታውቋል፡፡ ኢምባሲው ሰሞኑን ከኡኮንጋ እና ሲገሪያ እስር ቤቶች ከ250 በላይ እስረኞችን አፈላልጎ አግኝቷል፡፡ ባለፈው ታሕሳስ የታንዛኒያን ድንበር ሲያቋርጡ ባንድ መኪና ውስጥ ተፋፍገው ሞተው ከተገኙት 14 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መካከል 9ኙ ባለፈው ቅዳሜ ሞሮጎሮ በተሰኘ ቦታ ተቀብረዋል፡፡
10 – የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞች ምልመላ መመሪያ ማሻሻሉን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የሚመረጡባቸው መስፈርቶችም የዳኛው ማስረጃን የመተንተንና የመመዘን ብቃት፣ የውሳኔዎች ጥራት፣ በዳኝነት ሥራ ላይ ያለው ትጋት፣ ሀቀኛነት፣ በነጻነት የመዳኘት ቁርጠኝነት፣ ዳኛው በሰጣቸው ዳኝነቶች የባለጉዳዩ እርካታና መተማመኛ፣ የተመሰገነ ሥነ ምግባርና ባሕሪው እንዲሁም መልካም ሰብዕና እንዲሆኑ ተደርገው ተሻሽለዋል፡፡ የቃል ፈተናም ይኖራል፡፡ ፈተናውን ያለፉ በሕዝብ አስተያየት ተሰጥቶባቸው በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት ለፓርላማው ቀርበው ይሾማሉ፡፡ በተያያዘ ዜና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አዋጅን የሚያሻሽል ኮሚቴም ሥራ ጀምሯል፡፡ ዐላማው የፍርድ ቤቶችን ነጻነትና ገለልተኛነት ማረጋገጥ ነው፡፡