ለሀገራችሁና ለሕዝባችሁ በመቆርቆር፣ ሀገራችሁም የተሻለችና የሠለጠነች እንድትሆን በማሰብ የጻፋችሁትን መልእክት ተመልክቼዋለሁ፡፡ እንደ እናንተ ካሉ በሳል ዜጎች የሚጠበቀውም ይሄው ነው፡፡ ችግሮችን በጨዋነት በመመካከርና የተሻለ የመፍትሔ ሐሳብ በማቅረብ መፍታት እንደሚገባ የእናንተ ተግባር አርአያ የሚሆን ነው፡፡
በሀገራችን የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተ ያነሣችሁት ሐሳብ ሁላችንም የምንጋራው ነው፡፡ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ማናቸውም ዓይነት መብቶቻቸው ተጠብቀው፣ በየትኛውም አካባቢ የመኖር፣ ሀብት የማፍራትና የመዘዋወር መብት እንዳላቸው መንግሥት ያምናል፡፡ ይሄንንም ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሕዝባችን የጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ የፈነጠቀውን ተስፋ ለማጨለም በሚሠሩ አካላት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቢሮክራሲው ውስጥ ያሉ ኃላፊዎች ችግሮችን በእንጭጭነታቸው ለመፍታት ባለመረባረባቸው የተነሣ የዜጎቻችን መፈናቀል መከሠቱን እናምናለን፡፡ ይህም አጥብቆ ያሳዝነናል፡፡
ይህን ችግር ለመፍታት ባለፈው አንድ ዓመት በክልሎችና በፌዴራሉ መንግሥት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ከመጋቢት 2010 ዓም በፊት በሀገራችን ከልዩ ልዩ ቦታዎች የተፈናቀሉ 1,179,061 ያህል ዜጎች ነበሩን፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት 1,581,058 ያህል ወገኖቻችን የመፈናቀል አደጋ ገጥሟቸዋል፡፡ ከመጋቢት 2010 እስከ አሁን 1,020,234 ያህል ወገኖቻችን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ተመልሰው ቋሚ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ አሁን በመጠለያዎችና በሌሎች ቦታዎች ሆነው ርዳታ የሚደረግላቸው ዜጎቻችን 1,739,885 ያህል ናቸው፡፡ እነዚህንም ወደ ቋሚ ኑሮ ለመመለስ እየሠራን ነው፡፡ ለእኛ ዋናው ቁጥሩ አይደለም፡፡ አንድም ዜጋ ቢሆን ያለ ፈቃዱ ከሚኖርበት ሥፍራ እንዳይፈናቀል መሥራት አለብን፡፡ ፈተናው ለብዙ ዘመናት ከተከማቹ ሀገራዊ ችግሮች ጋር የተሣሠረ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ከምንፈልገው ውጤት ላይ አልደረስንም፡፡ በሂደት ግን ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ ነው፡፡ እንደ ታማኝ በየነ ያሉ የወገኖቻቸው ሁኔታ የሚያሳስባቸው ዜጎች ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ እያየን በመሆኑ ችግሮቻችን እድሜያቸው እንደሚያጥር ርግጠኞች ሆነናል፡፡
እስክንድር ነጋን በተመለከተ በኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ሰብአዊ መብትም እንዲከበር ያደረገውን አስተዋጽዖ እኔም የማደንቀው ነው፡፡ ለዚህ ተጋድሎውም ተገቢው አክብሮት አለኝ፡፡ ያነሣቸውን አንዳንድ ሐሳቦች በተመለከተ ግን መፍትሔው ውይይት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በቅርቡም ባነሣቸው ጉዳዮች ላይ እንደምንወያይ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ባነሣቸው ሐሳቦች ምክንያት በመንግሥት በኩል የሚደርስበት ምን ዓይነት ጫናና ችግር አይኖርም፡፡ ይህን የማናደርገው መንግሥት ለሐሳብ ብዙኅነት ያለው አቋም የማይነቃነቅ በመሆኑ ነው፡፡ የለውጡ አንዱ ምሦሶ ሐሳብን በነጻነትና በኃላፊነት የመግለጥ መብት ነው፡፡
ኢትዮጵያ: አዲሲቷ የተስፋ አድማስ Ethiopia: A New Horizon of Hope
የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ባለፈው አንድ ዓመት የተለያዩ ተግባራትን አከናውነናል፡፡ የመከላከያና የጸጥታ አካላትን የማሻሻያ ሥራ ሠርተናል፡፡ የመከላከያ ሠራዊታችን በአደረጃጀት፣ በፕሮፌሽሊዝምና በትጥቅ ሀገሩን ለመጠበቅ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ለማስቻል አመርቂ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በብሔር ተዋጽዖ ኢትዮጵያን የሚመስል እንዲሆን እየተሠራ ነው፡፡ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ በሕገ መንግሥትና በሀገሪቱ ሕጎች ብቻ የሚመራ ተቋም እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ የማረሚያ ቤቶችን የታራሚዎች አያያዝ ለማስተካከል ሞክረናል፡፡ የፍትሕ ተቋማትን የማሻሻያ ሥራ ጀምረናል፡፡ ከዴሞክራሲና ከሰብአዊ መብቶች ጋር የሚቃረኑ ሕጎችን የማሻሻል፣ አሁን ላለንበት ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥኑ ሕግጋትን የማዘጋጀት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በቂ ናቸው ብለን አናምንም፡፡ የሕግ አስከባሪ አካላትና ማኅበረሰቡ ለሕግ መከበር የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲ ያለ የሕግ የበላይነትና ያለ ሥነ ምግባር ሊተገበር እንደማይችል ማስተማር እንደ እናንተ ካሉ ሊቃውንት እንጠብቃለን፡፡ የወረስናቸውን ችግሮች ሁሉ በአንድ ጊዜ ለመፍታት የምንችልበት ዐቅም የለንም፡፡ የተለያዩ አካላት የየድርሻቸውን እየተወጡ ሲሄዱ፣ ተቋማዊ ዐቅማችንም ሲዳብር፣ የሕዝባችን አመለካከት ከሚጠበቀው ደረጃ ላይ ሲደርስ የሕግ የበላይነት ይበልጥ እየተረጋገጠ እንደሚሄድ እናምናለን፡፡
ረዥሙን የለውጥ ጉዞ ጀመርን እንጂ አልጨረስነውም፡፡ ካሳለፍነው ይልቅ ከፊታችን ያለው ረዥም ነው፡፡ እንዲህ እንደናንተ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሰከነ መንገድ ለሀገራቸው የሚችሉትን ሁሉ ሲያበረክቱ ነገ ከትናንት የተሻለ ይሆናል፡፡ ጀግናውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዘን የማንፈታው ችግር አይኖርም፡፡ መንገዳችን ቢለያይም የሁላችንም ፍላጎት የበለጸገች፣ የሠለጠነች፣ አንድነቷ የተጠበቀ፣ በዓለም ፊት በሞገስና በኩራት የምትቆም፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ የሰፈነባት፣ ዜጎቿ የትም የሀገሪቱ ክፍል በሰላምና በጤና የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መገንባት ነው፡፡ ጉሙ እየተገለጠ፣ ፀሐይዋም ይበልጥ እየወጣች ትሄዳለች፡፡ ያገኘነውን ሀገርን የማሳደጊያ ዕድል ተጋግዘን በጠንካራ መሠረት ላይ እንድናቆመው በዚሁ አጋጣሚ የሀገራቸው ጉዳይ ለሚያሳስባቸው ሁሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር