ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ነው። በስያትል ትልቅ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ስብሰባ ተዘጋጅቷል። በዋዜማው እየተንጠባጠቡ የገቡትን እንግዶች እየተቀበልን ሻይ ቡና እያልን አመሸን። ባንዱ ጠረጴዛ ዙርያ፣ የአፋር ህዝብ የትግል ታሪክ ማውሳት እንዲሁ ሳይታሰብ ተጀመረ። የማውቃትን ታሪክ ማካፈል ጀመርኩ።
“እንደ አፋር ህዝብ ቀድሞ የህወሃት ተልዕኮ ከአገር በፊት ገብቶት የታገለ የለም” አልኩኝ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከ 1 ሺ 600 ኪሜ ርዝማኔ ያለውን ከዳህላክ ደሴቶች እስከ ጅቡቲ የተዘረጋው የአፋር ህዝብ ግዝት እንደ ዱባ ቀርዶዶ ለኤርትራ አሳልፎ ሲሰጥ፣ የተቀረው ኢትዮጵያ በአራት ኪሎ እየተካሄደ የነበረውን የሽግግር መንግስት ምስረታ ድራማ አንጋጦ ሲከታተል፣ የአፋር ህዝብ በኢትዮጵያ ላይ የወደቀውን አደጋ ዓለም እንዲያውቀው እና እንዲያቆመው ሦስት የአፋር ተወላጆች ኢትዮጵያውያንን የያዘ ልዑክ ኒውዮርክ ወደ ሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ም/ቤት ደብዳቤ አስይዞ ላከ።
የደብዳቤው መልእክት በግርድፉ “ሁለት የኤርትራ አማጽያን ድርጅቶች አስመራ እና አዲስ አበባ ተቆጣጥረዋል። አንዱ ኢሳያስ አፈወርቂ ሲቆጣጠረው፣ አዲስ አበባ የገባው አክራሪ የኤርትራ ብሄርተኞች የሚመሩት ህወሃት የተባለ ድርጅት ደግሞ መለስ ዜናዊ ይቆጣጠረዋል። ሁለቱ ድርጅቶች በማናለብኝነት ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ላይ ጥሎ የማያውቀውን የአፋር ህዝብ ለሁለት በመሰንጥቅ፣ በቀይ ባህር ዳርቻ ያለውን መሬትና ኗሪው ህዝብ ለኤርትራ፣ የተቀረው ደግሞ ለኢትዮጵያ በመተው፣ የአፋር ግዛት በኤርትራ እንዲነጠቅ (annex) አድርገዋል። ስለዚህ የተባበሩት መንግስታት ም/ቤት ይህ እጅግ አደገኛ አካሄድ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ጠፍቶ፣ ወደ ግጭትና የጦርነት ቀጣና እንደሚቀየር ተገንዝቦ፣ ወንጀሉን እንዲያወግዘውና የአፋር ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ በሁለቱ የኤርትራ አማጽያን ድርጅቶች የተነጠቀውን ሉዓላዊ ግዛት እንዲመለስ ያደርግልን ዘንድ እንማፀናለን” የሚል ነበር አልኩኝ።
ተናግሬ እንደጨረስኩኝ፣ አንዱ ከአውሮፓ የመጡት እንግዳ ፈገግ አሉ። “አሁን አብርሃ የነገረን ታሪክ ሀቅ ነው” አሉ። “ከሦስቱ ወደ ኒውዮርክ ከተላኩት የአፋር መልእክተኞች አንዱ እኔ ነበርኩ” ሲሉ ሁላችንም ደነገጥን። አዎ ሰውየው ተወዳጁ ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ ናቸው።
ቃታ መሳብ እንጂ የገዛ አገሩን እየገደለ እንዳለ እንዳያውቅ የተደረገው የህወሃት እግረኛ ሰራዊት ጀርባ ላይ ቆሞ፣ በኢትዮጵያ ስልጣን ጨብጦ፣ ኢትዮጵያን ሲያፈራረሰ የኖረው ጽንፈኛው የኤርትራ አክራሪ ብሄርተኛ መለስ ዜናዊ የክቡር ሱልጣን አሊሚራህን ኢትዮጵያዊነት ለማሸማቀቅ ሲሞክር፣ “እንኳን የአፋር ህዝብ፣ ግመሎቻችንም የኢትዮጵያ ባንዴራ ያውቁታል” ብለው እንዳሳፈሩት ሁሉ፣ እነ ዶ/ር ኩንቴ ሙሳም በዲፕሎማቲኩ መስክ ተሰማርተው ኢትዮጵያ ያጣችውን ሉዓላዊ ክብሯን ለማስመለስ አልህ አስጨራሽ ትግል ሲያካሂዱ ኑረዋል። የወገን ድጋፍ ግን ሳያገኙ ቀሩና ሁላችን ተጎዳን።
ዛሬስ? እንደዛ ህወሃት የገባ ሰሞን ፈዘን እንደቀረን፣ አሁንም የዘር ፖለቲካ ጡዞ አገራችንን እንዲያፈርስ እንፈቅድ ይሆን? ወይስ ገና ከጥዋቱ ለዜግነት ፖለቲካ ታግለን አገራችንን ከመፈራረስ እንታደጋለን?