የማለዳ ወግ … ድምበር ተሻጋሪው አድልኦ ! || ነቢዩ ሲራክ

የማለዳ ወግ … ድምበር ተሻጋሪው አድልኦ ! || ነቢዩ ሲራክ

* ኦኤም ኤን በጅዳ ኮሚኒቲ እርዳታ ሊሰበስብ ነው 

* የጅዳ ቆንስል የእርዳታውን ፈቃድ አጽድቆታል

በሀገር ቤት የተለያዩ ተቋማትና በአደባባይ የዘር መድልኦ ተደረገ ሲባል ነገር ላለማክረር ዝምታ የመረጥን ብዙዎች ነን። መድልኦና ተጽዕኖው ድንበር ተሻግሮ ተመልክተንም ቢሆን ሆደ ሰፊ ሆነን ባሳለፍነው ቁጥር ነገሮች መደራረብ ይዘዋል። ለውጡን ተከትሎ ብዙ የመድልኦ መረጃዎች ተመልክተናል። በእርግጥም ያፈጠጡ ጭብጥ መረጃዎች በሀገሬ ምድር ተመልከተናል። ያም ሆኖ የሚታይ የሚሰማው የኦሮሚያ ፖለቲከኞች ተጽዕኖ ጅዳ ደርሶ ተመልክቻለሁና ሀቁን እንናገረው ዘንድ ግድ ነው።

የጅዳና የሪያድ ኮሚኒቲ አዳራሾች ለእናት ሀገር ጥሪ፣ ለአባይ የህዳሴ ግድብ፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስና ዜጎች በአደጋ ሲፈናቀሉ እርዳታ ይሰበሰብባቸዋል። ይህ የሚሆነው የተለያዩ ማህበራትና ድርጅቶች ጥያቄ ቀርቦ ቢሆንም ላንዱ ፈቃድ ሲሰጥ ላንዱ ሲነፈግ ታዝበናል። ይህም ይሁን ብለን አይተን እንዳላየን ዝም ጭጭ ያልንባቸው ጊዜያቶች በርካታ ናቸው።

አድልኦ ደንበር ሲሻገር ያስባለኝ የኦቦ ጁሃር የኦሮሚያ ኔትወርክ ቴሌቪዠን በጅዳ ኮሚኒቲ አዳራሽ እርዳታ ሊሰበስብ ፍቃድ እንደተሰጠው መረጃ ደርሶኛልና ነው። የግል ተቋም የሆነው የቄሮው ዘዋሪ የኦቦ ጁሃር ቴሌቪዥን ጣቢያ በመንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚሲዮን መ/ቤቶች ተጽዕኖ ማሳረፉ ስንሰማ ግን ለምን ? እንዴትስ የቀደመውን የአንድ ዘር የበላይነት የማግዘፍ ስራ በንጉሱ ዶር አቢይ ዘመን ድንበር ተሻግሮ ቀጠለ ? ማለቴ አልቀረም።

የጅዳ ቆንስል መ/ቤት መንገድ በሳተ ሁኔታ ለኦቦ ጁሃር መሐመድ ድጋፍ ሲያደርግ የመጀመሪያው አይደለም። ቆንስል መስሪያ ቤቱ ከውጭ ጉዳይ መጣ በተባለ ቀጭን መመሪያ ጁሃር ለሐጅ የመጣ ሰሞን የዲፕሎማሲ ክብር ያለው መኪናውን ሰጥቶ ፣ በዲፕሎማሲ ክብር ከፍተኛ ዲፕሎማት ለደህንነቱ ጥበቃ መድቦና ላቅ ባለ ክብር ማስተናገዱ እያወቅን በዝምታ ማለፋችን ፣ ለጁሃር ክብር አድናቂዎቹ በጅዳ ከተማ አለ በሚባል ሆቴል አቀባበል ሲደርጉለትና እርዳታ ሲሰበሰብ በዲፕሎማት ክብር በኃላፊው ታጅቦት በመሆኑም አልተቃወምንም ።

ከሰሞኑ በሚሲዮን መ/ቤቱ ውስጥ በሚገኘው የኮሚኒቲ አዳራሽ ለግለሰቡ የቴሌቪዥን ጣቢያው ለእርዳታ የተሰጠው ፍቃድ ግን ፍትሐዊ ነው ማለት አይቻለንም።

ያፈጠጠውን እውነት ይዘን ግን ለምን ? እና እንዴት ይሆናል ? የሚል ብርቱ ጥያቄ ማንሳታችን የሚለውጠው ነገር ባይኖርም መሆን የሌለበት ሊደረግ ስራው ሲሰራ ተቃውሞ ማሰማታችን ግድ ነው። ከሰሞኑ የደረሰኝ መረጃ በኦሮሚያ ነጻነት አቀንቃኝ በታዋቂው የፖለቲካ ተንታኝ በኦቦ ጁሃር መሀመድ ለሚመራው የኦሮሚያ ኔትወርክ ቴሌቪዥን እርዳታ ሊሰበሰብ ፍቃድ ቀርቦ ቆንስል መ/ቤቱ እንዳጸደቀው ሁነኛ መረጃ ደርሶኛል።

አዎ ሁሌም እንደምለው በዜጎች መብት አያያዝ ጉዳይ እንጅ በዘር ተኮር ፖለቲካው ዙሪያ ባልገባ እወዳለሁ ። ያም ሆኖ አድልኦው አፍጥጦ ሲመጣ ፣ እያየን እየሰማን ህብረትን የሚንድ ስራ ሲሰራ ስመለከት ህመሙ እንደ ዜጋ ያመኝና እናገራለሁ ። ሰትቶ የምደግፈው የንጉሱ ዶር አቢይ አህመድ መንግስት ሹመኞች በተጽዕኖ ስር ወድቀው አደገኛ ውሳኔ ሲያስተላልፉ እቃወማለሁ። ተጽዕኖው ገፋኤ ሆኖ በሚተላለፉ ጥቃቅን ግን ግዙፍ አድልኦውን የሚያሳዩ ስራዎች እየተመከትን ነውና ሳይደርቅ በእርጥቡ ይታረም ዘንድ የዜጋ ድምጼን አሰማለሁ።

አድልኦ ድንበር ተሻገረ ብየ የቆንስሉን አካሄድ የምቃዎመው በንጉሱ ዶር አቢይ መንግስት መብት አስጠባቂ ያጣው ነዋሪ ቅሬታው ያይላል ብየ በጽኑ አምናለሁ ። ይህ ቅርታ ደግሞ ህዝብን ይለያያል። ህዝብ ከተለያየ ደግሞ ሀገርን በህብረት ማሳደግ አይቻለንም። ለዚህች ሀገርና ለዚህ መንግስት የእንጀራ ልጅ የሆነ ዜጋ ፣ ማህበረሰብ ፣ ብሔርም ሆነ ድርጅት መኖር የለበትም። አድልኦው ቢያንስ ድንበር ተሻግሮ እንዲህ ባፈጠጠ መልኩ መስተናገድ የለበትም። ትናንት ልዩነትና አድልኦ ጭቆና ነበር እያልን ለውጥ አምጥተን ዛሬ ወደ ሌላ የአድልኦ አዙሪት መዘፈቅ የከብንም። ዜጎች እኩል መታየት አለብን!

እስኪ ቸር ያሰማን !

ሚያዝያ 2 ቀን 2011 ዓም

LEAVE A REPLY