ወጣት ሆይ! ለህልውናህም ሆነ ለክብርህ ወደ ባህልህ! || በላይነህ አባተ

ወጣት ሆይ! ለህልውናህም ሆነ ለክብርህ ወደ ባህልህ! || በላይነህ አባተ

አገር ይቃጠላል ሕዝብ ግን ለፖለቲካ ፍጆታ መንገድ ጠረጋ በአዋጅ ተጠርቷል፡፡ እንደ መንገድ ጠረጋው ቃጠሎን ለማጥፋት ሕዝብን በአዋጅ ለመጥራት ምን ያህል ገንዘብ ይጠይቃል? ላሊበላን ከመፍረስ ለማዳን ሕዝብን በአዋጅ ለመጥራትስ ምን ያህል ጥበብ ይጠይቃል? ጣናን በአረም ከመድረቅ ለማዳን ሕዝብን በአዋጅ ለመጥራትስ ምን ያህል ጉልበት ያስፈልጋል? በከንቲባ ከፈረሱ ቤቶች መንገድ የወደቁትን ህጻናትና እርጉዝ ሴቶች ወደነበሩበት የሚመልስ አዋጅ ለማወጅስ ምን ያህል በጎ ፈቃድ ይጠይቃል? በዘመናዊ መሳሪያ የሊጥ ዕቃና ዳቦ የሰረቁ የወታደር ልብስ ለባሽ ሽብርተኞችን ችሎት ለማቅረብስ ምን ያህል ጊዜ ያስፈልጋል?

ወጣት ሆይ! ህልውናህን የመፈታተኑ አደጋ በህይወትህና በቅርስህ በከፋ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ ይኸንን አደጋ ደርምሰህ ህልውናህን ለማስቀጠልና በክብር ለመኖር ወደ አያቶችህ ባህልና ጀግንነት መመለስ ግድ ይላል፡፡

ሃይማኖትህ ዓለም በቅዱሳን የምትመራ የፍትህ ምድር እንድትሆን ያዝዛል፡፡ ዳሩ ግን የትናንትናዋም ሆነ የዛሬዋ ዓለም ለጉልበተኞች እንጅ ለቅዱሳን ተመችታ እንደማታውቅ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ድርሳናትም ዓለም የጉልበተኞች እንጅ የቅዱሳን ሐብት የሆነችበት ዘመን እንዳልነበረ አስረድተዋል፡፡
ጉልበተኞች ጉልበትን በጠመንጃ፣ በስብከትና በገንዘብ እንደ ጆፌ መጭልፈው ዓለምን እንደ ኳስ እያነጠሩ ሲያሽከረክሯት ኖረዋል፡፡ ዓለም እስከ ዓለም ፍጣሜም ተጉልበተኞች መዳፍ መውጣቷ ያጠራጥራል፡፡ ይህ እውነታ ጉልበት ለህልውና ያለውን ወሳኝ ሚና ያመለክታል፡፡ ጉልበት ለህልውና ያለው ወሳኝ ሚና በዳርዊን ምርምር ተረጋግጧል፡፡ ዳርዊን “ሰው በአዝጋሚ ለውጥ ተፈጠረ” ያለው ስብከት ውሀ ባይቋጥርም “ጉልበታም ደካማውን አጥፍቶ ዓለምን ይቆጣጠራል!” የሚለው ክርክሩ ትክክል እንደነበር ያለም ታሪክ ይመሰክራል፡፡

ጉልበት ለህልውና የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና አያቶችህ ተረድተውት እንደነበር ግብራቸው ይመሰክራል፡፡ አያቶችህ በአጥንታቸው ካስማነትና በደማቸው ምርግነት ገንብተው በጠበቋት አገር እንደ ጠላት የምትገደለው፣ የምትፈናቀለውና የምትሰደደው ያሁኑ አማራም እንደ አያቶችህ ከአውሬዎች ራስህን ተከላክለህ ትውልድን ለማስቀጠል ከጥበብ ጎን ለጎን የጉልበትን ጠቀሜታ መገንዘብ ይኖርብሃል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረው” ከሚለው የድስት ሺህ ዘመን እምነትህ በተጨማሪ በዚች ከንቱ ዓለም ለህልውና ጉልበት አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ይኖርብሃል፡፡ እግዚአብሔር “ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጥ”ን ያዘዘው አምላክ በመልኩ የፈጠረው ሲመታህ እንጅ ሰይጣን ተእግዚአብሔር ፈልቅቆ በተንኮልና በጭካኔ ያደቆነው አውሬ ሲነክስህ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርብሃል፡፡

ሰይጣን ተእግዚአብሔር ጉያ ነጥቆ ያደቆነው ወራሪ ቀኛቸውን ሲመታቸው ግራቸውን በመስጠት ፋንታ አያቶችህ ወራሪውን እንደ አውሬ በመቁጠር እንደ አንበሳ አግስተው ከአናቱ ተጎምረው እስተንፋሱን እየዘጉ ዘርረውታል፡፡ እንደ አያቶችህ ተአውሬዎች ራስህን ተከላክለህ በክብር ለመኖር ያያቶችህን ፈለግ መከተል ይኖርብሃል፡፡ ሁለት እጅ፣ ሁለት እግር፣ ሰላሳ ሁለት ጥርስና እሚናገር ምላስ ያለውን ሁሉ እግዚአብሔር በመልኩ እንደፈጠረው ሰው በመቁጠር “ለኢትዮጵያ ህልውና ስል ቀኝ ፊቴን ሲመቱኝ ግራ ፊቴን ሰጠሁ” የሚል በምድር የመኖር መብትህን የሚነሳ በሰማይም ከገነት የሚያርቅህን ጅል ዐመል ማቆም ይኖርብሃል፡፡ ለግማሽ ክፍለ ዘመን የዘር መጥረግ ወንጀል እየተፈጠመብህና በእየ አስር አምቱ በሁለት ሚሊዮን እየጎደልክ ህልውናህ እንዳያከትም ያያቶችህን ፈለግ መከተል ይኖርብሃል፡፡ ያያቶችህን ፈለግ መከተል እንድትችልም ወደ ባህልህ መመለስ ግድ ይልሃል፡፡

ከባህሉ ያፈነገጠ ማህበረሰብ ከባህሩ እንደሸሸ አሳ በህልውናው አደጋ ይጋረጥበታል፡፡ አማራ በጀግና አፍላቂ ባህሩ በሚዋኝበት ዘመን ከዱር አራዊት አንበሳና ነብርን፤ ከሰው አራዊትም ቅኝ-ገዥዎችንና ተስፋፊዎችን አንድ ለአምስት የሚገጥሙ ጀግኖችን እንደ ብርቱካን እያንዠረገገ ሲያፈራ ኖሯል፡፡ ከባህሩ ባፈነገጠባቸው ግማሽ ክፍለ-ዘመናት ወዲህ ግን በክብሩ ብቻ ሳይሆን በህልውናውም አደጋ ተጋርጦበት ይገኛል፡፡

ወጣት ሆይ! ስንዴ ጉዛም እስተ ሆድ ዕቃው በርቅሶ ታረሰው ለም መሬት ተዘርቶና ታርሞ እንደሚያፈራው ጀግናም በጀግንነት መንፈስ ከለማ የባህል ማሳ ሲተከልና ሲኮተኮት ፍሬው ይጎመራል፡፡ ጠላትን እንደ ፍልጥ ተርክከውና እንደ ማገዶ አንድደው ድል ስልነሱ የምትዘፍንላቸውና የምትኮራባቸው አርበኞችህ በተፈጥሯቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህን ሰዎች ከአላህ በቀር ማንንም የማይፈሩ ጀግኖች ያደረጋቸው ሲወለዱ የተነቀሩበት በጀግንነት ባህል የታሸ ቅቤ ሲያድጉም የበሉት በጀግንነት መንፈስ የተቦካ የባህል እንጀራ ነበር፡፡

በጀግንነት ባህል የተቦካ እንጀራን ጀግና አፍሪነት የተገነዘቡ ምዕራባውያን ከአምስቱ ዘመን ዳግም ሽንፈታቸው በኋላ ባህልህን በተለያዬ መንገድ ማጥቃት ጀመሩ፡፡ ብፁእ ቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እንዳሉት ያገራቸው ባህልና ታሪክ ያልተቀዳበትን የጭንቅላት ቶፋ ይዘው ወደ ምዕራብ የተላኩትን ተማሪዎች በምዕራባውያን ርዕዮተ ዓለም እያጠመቁ የራሳቸውን ባህል እንደ አተላ እንዲደፉት አደረጉ፡፡ እነዚህ የራሳቸውን ባህል እንደ አተላ የደፉ “ስልጡን” ተማሪዎችም ጠጉራቸውን እንደ ጫጉላ ሙሽራ እየከፈከፉ በባህላቸውና በሃይማኖታቸው ዘመቱ፡፡ ጀግና እንደ ደን የሚያፋፉ ቀረርቶዎችና ፉከራዎችን እንደ አልሰለጠነ ባህል ቆጥረው “ዘመናዊ” በሚሉት የምዕራባውያን ዳንስ እንደ ጋማ ከብት መራገጥ ጀመሩ፤ እርግጫቸውን ለሌሎችም አስተማሩ፡፡

እነዚህ የዳንስ እርግጫ ወረርሽኝ ተጠቂዎች ቅረርቶንና ፉከራን በዳንስ ኮቴ ስብርብር ከማድረግም አልፈው የቅኔን ፍልስፍና ማስተማሪያ የሆኑትን የባህል ዘፈኖች እያጠፉ የምዕራባውያንን ሙዚቃና ሲኒማ አስፋፉ፡፡ በእነዚህ ወራሪ ሙዚቃዎችና ሲኒማዎች ወጣቱን እያነፈዙ ለአገሩ ባህል ባይተዋር አደረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት የቆንጆ ወንድ መለኪያው ጀግንነት መሆኑ ቀረና ሱሪን ከጪን ታጥቆ መዥገር እንደ ሸበባት ግታም ላም እየተውለደለዱ መራመድ ሆነና አረፈው፡፡

ይህ ጀግና አምራች ባህል ከአምስቱ ዘመን ድል ማግስት ጀምሮ በምዕራባውያን የባህል ጎርፍ እንደ ዓባይ ሸለቆ ዳገት መሸርሸር ቢጀምርም ጭራሹን የተጠረገው አማራን በጠላትነት የፈረጀ የወንበዴዎች አገዛዝ ከመጣበት ሶስት አስርተ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቀረርቶና ፉከራ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ብቻ ሳይሆን በሰፈርና በመንደርም እንዳይሸለል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተከለከለ፡፡ በዚህ ክልከላ ምክንያትም ይህ ጀግናን እንደ አሳ ገንዳ የሚያራባው ባህር እንደ ጣና በእምቦጭ ተመጦ እንዲደርቅ ትልቅ ሴራ ተሸረበ፡፡ በዚህ ሴራም አዲሱ ትውልድ በቀረርቶና በፉከራ አይምሮንን በጀግነት እንዳያንፅ በምዕራባውያን አጉል ሱስ ተጠምዶ በባህል ሸቀን እንዲቆሽሽ ተደረገ፡፡

ወጣቱ እንደ አያቶቹ በጀግንነት እንዲታነፅ ይህ የባህል ቆሻሻ በሕዝባዊ ዘመቻ መጠረግ ይኖርበታል፡፡ የባህል ቆሻሻው በበረኪና ታጥቦ ወጣቱ በራሱ የባህል ባህር መዋኘት ሲጀምር እንደ አያቶቹ እንኳን ራሱን ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን በጎርፍ ከመጠረግ ያድናል፡፡ ከሸረኞች ደባ የፀዳ ባህል እንደ አያቶችህ ቆራጥ፣ ታማኝና ሩህሩህ ጀግኖችን ያፈራል፡፡ ባህልህ ከቆሻሻ ሲፀዳ በእግዚአብሔር ሚዛን የሚፈርዱ ሽማግሌዎችና ዳኞችን ይፈጥራል፡፡ ከተንኮለኞች ሸቀን የፀዳ ባህል ሲኖርህ እንደ ጥንቱ ለቆባቸው የሚያድሩ ሼሆችና መነኩሴዎች ይኖሩሃል፡፡ ከባህል እድፍ የፀዳ ባህል ሲኖር የሰው የማይነካ የራሱንም የማይሰጥ ኩሩና ሙሉ ትውልድ ይገነባል፡፡

ወጣት ሆይ! ስለዚህ ለህልውናህም ሆነ ለክብርህ ወደ ባህልህ መመለስ ይኖርብሃል፡፡ ሱሪህን ከጪንህ ከፍ አድርገህ ከወገብህ በቀበቶ ማጥበቅ ይጠበቅብሃል፡፡ በባዕዳን ዳንስ እንደ ማይክል ጃክሰን እንደ ጥንዚዛ መፈናጠሩን ትተህ እንደ ሞላ ሰጥአርጌ በሽለላና በፉከራ መንጎራደድ ይኖርብሃል፡፡
ወጣት ሆይ! ወደ ባህልህ ተመልሰህ የቅድመ አያቶችህን ዱካ ስትከተል የማትወጣው ተራራና የማትሻገረው ባህር አይኖርም፡፡ ከፊትህ የተገተረው ተራራ ከኦቶማን ኢምፓየዬር ወይም ከአውሮጳውያን ቅኝ ገዥዎች አጠገብ የሚደርስ አይደለም፡፡ ይኸንን ዳገት ሜዳ ማድረግ አቅቶህ ሕዝብህንም ሆነ ቅርሶችህን ማስፈጀት አይኖርብህም፡፡ ዓለም በሚያንቀላፋበት ዘመን ቅደመ-አያቶችህ የጠበቡትን ላሊበላን ማደስ አቅቶህ እንደ አይምሮ በሽተኛ ፈረንሳይን እየለመንክ ክብርህን እንደ ድሪቶ መጣል የለብህም፡፡ እሳት ማጥፋት አቅቶህ በአያቶችህ እርዳታ ትናንት ነፃ የወጡትን ደቡብ አፍሪካውያን እንደ ዕድ-አልባ
“በእይነተ- ስመዓለማርያም” እያልክ የዓለም መሳቂያ መሆን አይኖርብህም፡፡ የሙሴ ጽላት ለስምንት መቶ ዓመታት የተጠለለበት፣ የብዙ የሃይማኖትና ፍልስፍና መዛግብት የሚገኙበትና የእልፍ አእላፍ ፍጥረታት መኖሪያ የሆነው ጣና ሲደርቅ እንደ ባዕድ ቆመህ ማየት የለብህም፡፡
ወጣት ሆይ ህልውናህም ሆነ ክብርህ ያለው ከባህልህ ነውና ለህልውናህና ለክብርህ ወደ ባህልህ! አመሰግናለሁ፡፡

ሚያዚያ ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.

LEAVE A REPLY