በዴሞክራሲያዊ ሥርዓትግንባታ ውስጥ የሞጋችና ነፃ ተቋማት ሚና
ባለፉት ጥቂት ወራት በአዲስ አበባና በአካባቢዋ በተቀሰቀሰው የ”ባለቤትነት ጥያቄ “ የተነሳ አዳዲስ ተጫዋቾችን ያካተቱ የፖለቲካ ክስተቶች በመታይት ላይ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ “አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እራሷንም ችላ መተዳደር የሚገባት ከተማ ነች “ በሚል አመለካከት ሥር የተሰባሰበውና በታዋቂው ጋዜጠኛ በእስክንድር ነጋና በአጋሮቹ የሚመራው “የባለአደራ ምክር ቤት ወይም ባልደራስ ” የተሰኘው የህዝብ ስብሰብ (ሲቪክ ማህበር) አንዱ ነው። በዚህ ጽሁፍ ፤ ይህ የሲቪክ ድርጅት የተመሰረተበትን አግባብና እያካሄደ የሚገኘውን ትግል፤ እንዲሁም እየደረሰበት ያለውን ፈታኝ ተግዳሮት በተመለከተ፤ በሀገራችን የፖለቲካ ሽግግርናዴሞክራያዊ ስርአትን ለመመመስረት ከሚደረገው ጎዞ አኳይ የሚኖረውን እንደምታ በጨረፍታ አሳያለሁ።
የሲቪክ ድርጅቶች ወይም ማህበራት የሚያስገኙዋቸው ጠቀሜታዎች እጅግ ሰፊ ሲሆኑ እነዚህም በሁለት ዋና ዋና ጉዳዩች ዙሪያ ሊመደቡ ይችላሉ። አንዱ ማህበረሰብአዊ ጠቀሜታቸው (ሶሻል ካፒታል) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የፖለቲካ ጠቀሜታቸው (ፖለቲካል ካፒታል ) ናቸው፡፡
የሲቪክ ድርጅቶች ማህበራዊ እሴት (ሶሻል ካፒታል)
የሲቪክ ድርጅቶች ማህበራዊ እሴት (ሶሻል ካፒታል) የሚባለውየስቪክ ድርጅቶች በሚመሰረቱበት ዋና ሀሳብ ዙሪያ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸውን ግለሰቦችና ማህበረሰቦች ማሰባሰብ፤ እርስ በርስ እንዲተዋወቁ በአላማና በግብ ዙሪያም እንዲቀራረቡ የማድረግ ጠቀሜታቸውን ያመለክታል። በዚህ አይነት ተግባርሰዎች ተጨበጭ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ይበልጥ እንዲቀራረቡአንዳቸው ከሌላው ድጋፍ እንዲያገኙ ብቸኝነትና የተገላይነት ስሜት እንዳያጠቃቸው ያግዛል።
የሰው ልጅ ኑሮ እየተወሳሰበና በአብዛኛው ህይወቱም በግል ስራ ላይ አተኩሮ በሚኖርበት ጊዜ በእነዚህ በማህበራዊ እሴቶች ላይ ያተኮሩ ድርጅቶች አስፈላጊነት ታላቅ ቦታ አላቸው። ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችንም ይህንኑ በመገንዘብ ይመስላል እድር፣እቁብ፣ ጅጌ፣ ደቦ… ወዘተ የመሳሰሉ ማህበራዊ ድርጅቶችን መስርተው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ እንዲቀጥሉ ያደረጉት፡፡
የዚህ አይነት አደረጃጀትና ስብስብ ውስጥ የሚታዩ ማህበራዊ ድርጅቶች አገልግሎታቸው ሰፊ ቢሆንም በፖለቲካ ድርጅቶች ፖሊሲና አስተሳሰብ ላይ ተጽእኖ ለማድረስ የሚኖራቸው ክህሎትግን ዝቅተኛ ነው። የምስረታቸው አላማም ሆነ አደረጃጀታቸው የፖለቲካ ተጽእኖ መፍጠርን ወይም ፖሊሲን ማስፈጸምን በእሳቤ ውስጥ አሰገብቶ ስላልሆነ በዚህ ረገድ የሚያደርገው ተጽእኖም ዝቅተኛ ነው።
ይህ ማለት ግን በሶሻል ካፒታል ዙሪያ የተሰባሰቡ ሲቪክ ድርጅቶች ውሎ አድሮ በዙሪያቸው ያሰባሰቡትን እምቅ ሀይል ወደ ፖለቲካ ካፒታልነት ሊቀይሩት አይችሉም ማለት አይደለም።
የሲቪክ ድርጅቶች ፖለቲካዊ እሴት (ፖለቲካል ካፒታል)
በፖለቲካ እሴት (ፖለቲካል ካፒታል) ተብሎ የሚጠራው ደግሞ የሲቪክ ድርጅቶች የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍልን የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ በተለይም በመንግስትና፣ በፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ተጽእኖን ለማሳደር የሚያሰትለውን ከመደራጀትና የህዝብን እምቅ ሀይል ለፖለቲካ ግፊት ከማዋል ጋር የተያያዘ ችሎታን የሚመለከት ነው።
ይህን ተግባር መሰረታዊ ስራቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ (ማሀበራዊ) ድርጅቶች የመብት መረገጥን ለማስቆም፣ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ በሚኖራቸው በመንግስትና የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር…ወዘተ የሚቻለው በዋናነት በተደራጀና በተቀነባበረ መንገድ ነው ብለው የሚያምኑ፣ የግለሰብ ጥረቶች በድርጅት መልክ ካልተሰባሰበ መንግስትም ሆነ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቀላሉ እንደማያዳምጡ ግንዛቤን የወሰዱ አካሎች ናቸው።
በተለይም ደግሞ ብዙሀዊነት በሚታይበትና የተለያዩ ክፍሎች ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ ፍላጎታቸውን (አጀንዳዎችን) የመንግስት ፖሊሲ ለማድረግ ግፊት በሚያደርጉበት ህብረተሰብ ውስጥ የዜጎች ጥቅም የሚጠበቀው በተናጠል ሳይሆን ተሰባስቦ በሚደረግ ተጽእኖ ፈጣሪነት ነው። በዚህ አውድ ውስጥ ያልተደራጁ የህብረተሰብ ክፍሎች በአብዛኛው ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል ሀይል እንደማይኖራቸው በመገንዘብ ዜጎች የተደራጀ ሀይላቸውን የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችላቸው ስብስብ አስፈላጊ ይሆናል። ይህ እውን የሚሆነውም የመደራጀትንና በጋራ ተጽእኖ የመፍጠርን የፖለቲካ እሴት (ካፒታል ) በተገነዘበ ሲቪህ ድርጅት አማካኛነት ነው።
የፖለቲካ መሪዎች ውሳኔ በዜጎች ህይወት ላይ እጅግ መሰረታዊ የሆነ በጎም ሆነ መጥፎ ተጽእኖ የማሳደር ችሎታ አለው። አንድ መንግስት አንድን ህበረተሰብ መሰረታዊ በሆነ መልክ ለዘመናት እንዲለወጥ የሚያደርገው ውሳኔ ሊያሰተላልፍ ይችላል ። ይህን የመንግስት ተጽእኖ ለማስቀየርም ሆነ ለመቋቋም ተጽእኖ ፈጣሪ የሲቪክ ማህበራት መደራጀት እጅግ አሰፈላጊ ይሆናል ።ይህ በህብረተሰብ ላይ የሚደርስ ተጽእኖን የማስቆምና የማስቀየር እምቅ ሀይል ነው ፖለቲካዊ እሴት የሚባለው።
የፖለቲካ ብዙሀዊነት አውን በሆነበትና የፖለቲካ ስልጣን በህዝብ ድምጽ ብቻ በሚያዝበት ህብረተሰብ ውስጥ ፖለቲከኞች የህዝብን ድምጽ እንዲያዳምጡ ከሚደረጉበት መንገዶች ውስጥ አንዱ በድምጽ አሰጣጥ ላይ ድጋፍን በመንፈግና በመስጠት የሚገለጽ ነው። በዚህ መልክ ድምጽን በተደራጀ መልክ ለመንፈግም ሆነ ለመስጠት በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ህዝብን የማደራጀት፣ ማስተማርና በድምጽ አሰጣጡ የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት የሚያስችለውን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችለውን ክህሎት (ፖለቲካል ካፒታል)እውን ለማድረግ የሲቪክ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው።
በአጠቃላይ የሲቪክ ድርጅቶች የፖለቲካ ካፒታላቸውን በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ህዝብን በማሰባሰብ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የፖለቲካ ሀይሎች ለህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ትኩረት እንዲሰጡ ተጽእኖ ለማድረስ የሚያደርጉትን የዜጎች እንቅስቃሴ ያሳያል።በፖለቲካ ሽግግር ወቅት ይህን ተግባር ትኩረት ሰጥተው የሚንቀሳቀሱ ማህበራዊ ድርጀቶቸ ለዴሞከረሰያዊ ለውጥ ማሳካትና ዴሞከራሲያዊ ስርአት ግንባታን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ በሚደረግው ጥረት ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ይታያል፡፡
ሽግግርና ሲቪክ ድርጅቶች
ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር በሁሉም ገጽታው ከፈላጭ ቆራጭ እኔ የምለውን ብቻ ስማ ከሚል አገዛዝ ወደ የህዝብ መብት የተከበረበት የህዝብ ድምጽ ወደሚደመጥበትና ሰብአዊ መብትና የህግ የበላይነት ወደተረጋገጠበት ስርአት የሚደረግ የለውጥ ሂደት ነው።
በዚህ ዓይነት የሽግግር ሂደት ውስጥ የሲቪክ ማህበራት ዋነኛው ተግባር ባንድ ሀገር ውስጥ የሚገኝ መንግስት በስልጣን እንዳይባልግና በሚያሰተዳድረው ህዝብ ህይወት ላይ ተገቢነት የሌለው ተጽእኖ እንዳያደርግ የሽግግሩ ሂደትም ፈሩን ስቶ እንዳይሄድ መንግስት ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያከብር እንዲሆን አበክሮ መስራት ነው።
ከአምባገነን ስርአት ተላቆ ወደ ዴሞክራሲ በሚያመራው የሽግግር ሂደት ውስጥ መንግስት እንዳለፉት አምባገነኖች ሁሉ መብት መርገጥ እንዳያገረሽበት፣ ከሚገባው በላይ በመሄድ የህዝብን መሰረታዊ መብት እንዳያኮላሽ፣ የህዝብን ፍላጎትና መብት ወደጎን ገፍቶ የራሱን እና የደጋፊዎቹን ጠባብ ፍላጎት ብቻ በህዝብ ላይ እንዳይጭን፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ግንባታ ታማኝ ሆኖ እንዲቀጥል በስልጣን መባለግ አድልኦ… ወዘተ የመሳሰሉት አስከፊ ክስተቶች እንዳይከሰቱ ቢከሰቱም በጊዜ እንዲጋለጡ ታላቅ ሚናን የሚጫወቱት የሲቪክ ድርጅቶች ናቸው።
የሲቪክ ድርጅቶች የህዝብ ዓይናና ጆሮ በመሆን ህዝብን ለመብቱ እንዲቆም በማስተማርና በማደራጀት በለውጡ ሂደት ንቁና ቆራጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ የለውጡ ሂደት በአስተማማኝ መልክ አንዲቀጥል የለውጥ ሀይሎች እንዲጠናከሩ ለውጡም ተቋማዊ እየሆነ ስር እየሰደደ እንዲሄድ ያግዛሉ።
ይህ ሲሆን ደግሞ ህዝብ በለውጡ ሂደትና በመንግስት ላይ እምነቱ እንዲጠናከር ለመንግስት ያለው ከበሬታና እምነትም ከፍ እንዲል ታላቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ነው ዴሞክራሲያዊ ስርአት የህብረተሰቡን ታላቅ አመኔታና ድጋፍ የሚጎናጸፈው። የዚህ አይነቱን ስርአት ነው ህብረተሰቡም የኔ ነው ብሎ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚንከባከበው።
ባጭሩ ከአምባገነን ስርአት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ህዝብን ማዕከል ያደረገ (ህዝብን ያሳተፈ) መሆን ይገባዋል። ይህ ደግሞ በዋናነት የሚገለጥበት አንዱ መንገድ ህዝብ በራሱ ፍላጎት በሲቪክ ማህበራት አማካኝነት በንቃትና በድፍረት መሳተፍ ሲችል በመሆኑ እነዚህ ድርጅቶች ሊበረታቱም ሊደገፊም ይገባቸዋል።
የሀገራችን ፖለቲካዊ ምህዳር መስፋትና የባለአደራ ምክር ቤት መወለድ
በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የህወሀት የበላይነት ከተወገደና ዶክተር አብይ አህመድም የጠቅላይ ሚኒስቴርነቱን ስልጣን ከያዙ ወዲህ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የህብረተሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅም የተለያዩ ድርጅቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ከነዚህ ውስጥ አንዱና በቅርቡ ተመስርቶ ትልቅትኩረትን የሳበው ባልደራስ ወይም ባለአደራ ምክር ቤት የተሰኘው ድርጅት ነው።
የባለ አደራ ምክር ቤት ምስረታ መነሻው አዲስ አባባ በማን ትተዳደር በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተነሳውን ሀሳብ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተውን ከፍተኛ ውጥረትና አለመረጋጋት ተከትሎ ነው፡
ኢህአዴግ ለ27 ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ አዲስ አበባን በተመለከተም ህዝቡን ሳያሳትፍ “መሪው ድርጅት” በፈለገው መልክ ሲፈልግ ላንዱ ክልል ሲሰጥ ሌለ ጊዜ ደግሞ ሲነጥቅ፣ እንደቆየ ይታወቃል። በዚህም ተግባሩ ፖሊሲ አሁን ለምንመለከተው በአዲስ አባባ ላይ ለተቀሰቀሰው የይገባኛል ጥያቄ ተጨማሪ የግጭትና የጭንቅ ድባብ የተፈጠረበትን ሁኔታ እንዳመቻቸ እናያለን።
ይህ ሁሉ ሲሆን ኢህአዴግ የአዲስ አባበን ነዋሪዎች ፍላጎትና ስሜት ምን እንደሆነ አንድም ጊዜ ጠይቆ እንደማያውቅ ታሪክመዝግቦታል።
ባልደራስ ወይም የባላአደራ ምክር ቤት የተሰኘው ንቅናቄ በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ኢህአዴግም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ከተማችንንና ህዝቧን ወዲያ ወዲህ ሊያደርጉአይገባም፣ በስጦታም፣ በፖለቲካ ዳረጎትም ይሁን በሌላም ምክንያት ለፈለገው አካል ያለፍላጎታችን አሳልፎ ሊሰጡን አይገባም በሚል እሳቤ የተነሳና የሚንቀሳቀስም ነው።
ባለአደራ ገና ከጅምሩ የቆመለት ዓላማ የአዲስ አባባን ነዋሪወችን አስተባብሮ በመንግስትንም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ አዲስ አበባን በተመለከተ ባላቸው አመለካከት አኳያ ተጽእኖ ማሳደር እና መሞገት መሆኑን በግልጽ አስፍሯል። ይህ ሁኔታ ላለፉት 27 ዓመታት ባልተለመደ መልክ እንደሲቪክ ድርጅት የፖለቲካ ካፒታሉን ባግባቡ ገምግሞና አውቆ የተደራጀ መሆኑን ያሳያል።
ይህ ከሞጋች ህብረተሰብና ህዝብ የሚጠበቅ የዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ መሰረት ግንባታውንም እጅግ የሚያጠናክር፣ ፖለቲከኞችንም ከራሳቸው ፍላጎት ባለፈ በህዝብ ፍላጎት እንዲገዙ የሚያደርግ አበረታች ተግባር ነው፡፡ ’ይህ መንግስትም ሆነ ሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች ተጠያቂነትን እንዲያውቁ፣ የሚያግዝ የዴሞክራሲያዊ ሂደት መሰረት ነው።
የዴሞክራሲያዊ ስርአትን እውን መሆን ለምንናፍቅ ጠያቂ ነጻና የተደራጀ ህብረተሰብን ለምንፈልግ ሁሉ ይህ አስደሳች እንጂ አስጊ ክስተት አይደለም። ባላአደራወች (ባልደራሶች) ለማድረግ የሚፈልጉት በማንኛውም ዴሞክራሲን አከብራለሁ በሚል ሀገር ማህበራዊ ድርጅቶች ከሚያደርጉትን የተለየ አይደለም።
ለዚህ ነው ይህ ሲቪክ ድርጅት ሊበረታታና አይዞህ ሊባል እንጂ እንዲሸማቀቅ እንዲዳከም ወይም እንዲጠፋ መደረግ የለበትም የምለው። በርግጥ እንደጀማሪ ድርጅት ባላደራ ምክር ቤትም ስህተት ሊሰራ ድክመትንም ሊያሳይ ይችላል። ይህ የሚጠበቅ ነው።
ሀገራችን ዴሞክራሲያዊ እንድትሆን ከፈለግን ማድረግ ከሚገባን ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ፍላጎታችንን እውን ሊያደርጉ የሚችሉ ተቋማትን (ሲቪክ ድርጅቶችን ጨምሮ) ድክመታቸውን እንዲያሰተካክሉ እያገዙ አቅማቸውን መገንባትና ማጠናከር ነው። በእነዚህ ዓይነት ድርጅቶች ላይ የሚደረግ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ተጽእኖን መቃወም ደግሞ ለመሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር መቆም ነው።
ሲቪክ ማህበራት ለማበብ አበረታች ድባብ ይሻሉ
የሲቪክ ማህበራት በተዛዋሪም ሆነ በቀጥታ በጥቃት ስር ሲሆኑ (በፖሊስ ሲሳደዱ መሪዎቻቸው ሲወገዙ፣ የሚታሰሩ ስብሰባ ሲከለከሉ…ወዘተ) ህብረተሰቡ እንደልቡ ተንቀሳቅሶየሲቪል ግዴታውን ለመወጣት አስቸጋሪ ይሆንበታል። በዚህ ዓላማ ስር የሚቋቋሙ ሲቪክ ድርጅቶችም አያብቡምአይጎለብቱም።
በህወሀት መራሹ ኢህአዴግ የ27 ዓመታት አገዛዝ የተመለከትነውም ይኽንኑ እውነታ ነው ። ከተነሳሽነት ማነስ ሳይሆን በመንግስት ተጽእኖ የተነሳ ሲቪክ ማህበራት በተለይም የፖለቲካ ጥያቄዎችና የዜጎች መብት ላይ ያተኮሩት ሁሉ ድምጥማጣቸው እንዲጠፋ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሴት ጠበቆች ማህበር፣ የሰብአዊ መብት ጉባዔ፣ የመምህራን ማህበር፤ የሰራተኞች ማህበር…ወዘተ ከሚጠቀሱት ሰለባወች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡
አሁን ባለው የሀገራችን ሁኔታም ባለአደራ ምክር ቤት የተሰኘው ሲቪኽ ማህበር ገና ብቅ ከማለቱ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት መሪዎችና የፖለተካ ድርጅት ተወካዮች ማውገዝና መኮነን መጀመራቸው፤ ስብሰባ እንዳያደርጉ የተለያየ ተጽእኖ ማሳደራቸው…ወዘተ፣ በለውጡ ማግስት የተከፈተውንየፖለቲካ ምህዳር መልሶ እንዲጠብ የሚያደርግ እንጂ የሚያዳብረው አይደለም።
አንዳንዶች ባልደራስ ወይም ባለአደራ ቆሜለታለሁ ከሚለው ዓላማ ውጭ የራሳቸውን ትርጉም በመስጠት “የአዲስ አባባ ከተማን ምክር ቤት ተክቼ መስራት ያለብኝ እኔ ነኝ “ ብሏል በማለት ሊፈርጁትና የህዝብ ድጋፍን ሊያሰነፍጉት፣ የሚጥሩበት ሁኔታ ይታያል። አንዳንዶች ደግሞ “የአዲስ አባበን ህዝብ እወክላለሁ እንዴት ይላል” እኔም የአዲስ አባባ ነዋሪ ነኝ ሆኖም ለስበሰባ እንኳ አልተጠራሁም” ይላሉ። ይህን የሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ለመሆኑ እናንተ እንወክለዋለን እያላችሁ በስሙ የምትናገሩት ህዝብ መቼ ተሰብስቦ ነው ለናንተ ውክልና የሰጣችሁ ቢባሉ ምን እንደሚሉ ይገርመኛል።
ሕወሀት መራሹ ኢህአዴግ የሲቪክ ማህበራትን በተመለከተ ይከተለው የነበረው አንዱ ፖሊሲ እነዚህን ድርጅቶች ከፖለቲካ ድርሻቸው ለመነጠልና በእርዳታና ሌሎች በማህበራዊ ተግባሮች ላይ ብቻ ያተኮሩ በማድረግ ላይ ያጠነጠነ ነበር። ባጭሩ ነጻ ሞጋችና ፖለቲካዊ ተጽእኖ ፈጣሪ ሲቪክ ድርጅቶችህወሀትን አይመቹትም ነበር።
ለዚህ ማሳያ ሀገር በቀል የሆኑትንም ሆነ በውጭ የሚገኙ ሲቪክ ድርጅተች ከፖለቲካ ተግባር ተገልለው እርዳታ የማደል ወይም መንግስት በሚያጸድቀው ተግባር ላይ ብቻ እንዲሳተፉ ሲፈቅድ መቆየቱ ፣ በመብት ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ድርጅቶች (ሰብአዊ መብት፣ የሰራተኞች መብት፣ የመናገርና መፃፍ፣ የሴቶች መብት…ወዘተ) ደግሞ በሀገር ውስጥ ያሉት እንዲቀጭጩና እንዲጠፉ በውጭ ያሉት ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ድርሽ እንዳይሉ አድርጎ መቆየቱ ነው።
አሁን ደግሞ ያን ጨቋኝ ስርአት አስወግደን ራዕያችን ዴሞክራሲያዊ ስርአትን መገንባት ነው በሚባልበት ሰዓት ይህንኑ ሀላፊነት ተሸካሚ የሆኑ ጅምሮችን ማጥላላትና እንቅስቃሴያቸውንም በተለያየ ሁኔታ ማደናቀፍ እጅግ ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው። ይህ ደግሞ የሆነው ሀገራችን በለውጥ ውስጥ ነች፣ ሲቪክ ማህበራትም የለውጡ የጀርባ አጥንት ስለሆኑ ይህንን ለማገዝ የሚሆን አዲስ የማህበራት አዋጅ ተዘጋጅቷል ተብሎ በተገለጸ ማግስት መሆኑ እጅግ ግራ የሚያጋባና እጅግ አሳሳቢም ያደርገዋል።
በርግጥ ባለአደራ የተሰኘው ስብስብ እጅግ ሞጋችና ያነሳቸውም ጥያቄዎች ለፖለቲከኞች እጅግ ፈታኝ እንደሆኑመረዳት ይቻላል። ያም ሆኖ ግን ጥያቄው ገና ለገና ፈታኝና አከራካሪ (ሴንሲቲቭ) ነው በማለት የህዝብን የመደራጀትና ሀሳቡን በነጻ የመግለጽ መብት ማፈን አግባብ አይደለም። የዚህ አይነቱ ተግባር የመንግስትና ህዝብ ቅራኔ ያካርረዋል እንጂ አያረግበውም። እንደ ባላደራ የመሰሉ ሲቪክ ድርጅቶችን አግልሎና ድምጻቸውን አፍኖ በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ ውሳኔ ማስተላለፍ ቢቻል እንኳን የውሳኔው ቅቡልነቱ እጅግ ዝቅተኛ ነው የሚሆነው። ለዴሞክራሲ ግንባታ ደግሞ እጅግ አስፈላጊው ነገር የለውጡ ሀይልና የለውጡን ሂደት ቅቡልነት (ሌጅትመሲ) ማዳበር እንጂ የዜጎችን ድምጽ ማዳመጥን ወደጎን ትቶ የፈለጉትን ውሳኔ ማስተላላፍ አይደለም።
በዚህ አኳይ ከፖለቲካም አንጻር ይሁን ዜጎች በፖለቲካ ምህዳሩ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከማበተረታታት ወይም ዜጎች በሽግግሩ ትክክለኛነት ለይ ያላቸውን እምነት ከማዳበር አኳያ መደረግ የሚገባው ባለአደራ ምክር ቤትንና መሰል ድርጅቶች ማበረታታትና መደገፍ እንጂ እንቅፋት መሆንከቶውንም አይደለም።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ እንዳሉትም ማሰታወስ የሚገባው ለዴሞክራሲ ግንባታ በዋናነት የሚያሰፈልገው ጠንካራ ሰዎች ሳይሆን ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ነው (“Africa does not need strong men. It needs strong institutions” ። እነዚህ ነጻና ሞጋች ተቋማት እንዲያብቡ የሚያበረታታ ድባብ ከሌለ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር እንዘጭ እንቦጭ ማለቱ የማይቀር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም የሚጠቅም አይደለም።
ስለዚህ ምን ይደረግ
ይህን ፈተና በበጎ መንገድ በመፍታት ታላቁ ድርሻ የመንግስት ሲሆን ሌሎችም ቢሆኑ ሊጫወቱት የሚገባው ሚና ከፍተኛ ነው። በዚህ አኳያ፦
ሚያዝያ 25፣ 2011 (ሜይ 3፣ 2019)
ethioandenet@bell.net