የዛሬ ሐሙስ ዐበይት ዜናዎች- ዋዜማ

የዛሬ ሐሙስ ዐበይት ዜናዎች- ዋዜማ

1. ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች ከውጭ ያለ ቀረጥ እንዲገቡ ተፈቅዳል፡፡ ቀረጡ የተነሳው ለግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች፣ ለመስኖ ልማት መሳሪያዎችና ለእንስሳት መኖ ልማትና ምርት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጅዎችና መሳሪያዎች ነው፡፡ የቀረጥ ማሻሻያው የተደረገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከግብርና ሚንስቴር ጋር በመተባበር ለገንዘብ ሚንስቴር ባቀረበው የማሻሻያ ሃሳብ መሠረት ነው፡፡ ቀረጡ መነሳቱ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ይጠበቃል፡፡

2. በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በግጭቶች ሳቢያ ትምህርታቸውን ያልተከታተሉ ተማሪዎች ለዘንድሮው ብሄራዊና ክልላዊ መልቀቂያ ፈተናዎች ዝግጁ አይደሉም፡፡ ሸገር የዞኑን ትምህርት ቢሮ ጠቅሶ እንደዘገበው ከታሕሳስ ጀምሮ በ6 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በ103 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ 7 ሺህ ያህል ተማሪዎች ለፈተና አልተዘጋጁም፡፡ ዛሬም ድረስ 40 የ8ኛ ክፍል፣ 5 ደሞ የ10ኛና 12ኛ ፈተና የሚያስፈትኑ ትምህርት ቤቶች ዝግ ናቸው፡፡ ፈተናዎቹ ግንቦት መጨረሻና ሰኔ መጀመሪያ ነው የሚሰጡት፡፡

3. አርበኞች ግንቦት 7 እና ሌሎች 6 የፖለቲካ ድርጅቶች ራሳቸውን አፍርሰው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ ጉባዔ ሲካሄድ ውሏል፡፡ በጉባዔው 1 ሺህ 200 በድምጽ የሚሳፉ ጉባዔተኞች ተገኝተዋል፡፡ ጉባዔው በዛሬው ውሎው በፓርቲው ስያሜ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ አወቃቀር እና አርማ ላይ ይወስናል፡፡ የፓርቲውን አመራሮች የሚያስመርጥ ኮሚቴም ይስይማል፡፡ አዲሱ ፓርቲ የቀድሞ አርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎችን እንዲያቋቁም ጉባዔው ዛሬ በድምጽ ብልጫ መወሰኑንና ሃላፊነቱም ለቀድሞው የግንባሩ ዋና ጸሃፊ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደተሰጠ የአማራ መገናኛ ብዙኻን ዘግቧል፡፡

4. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ግጭት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 62 ደርሷል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ ለትራንስፖርት ዝግ የነበሩት መንገዶች የአሶሳ-ግልገል በለስ፣ የግለገል በለስ- ማምቡክ፣ የግልገል በለስ-ፓዌ-ጃዊ-ማንኩሽ እና ሌሎች መንገዶች ተከፍተዋል፡፡ ከእኒህ መካከል 12ቱ ከጃዊ ወረዳ ግጭት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን ኢዜአ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነር መሃመድ ሐምደኒልን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

5. ሦስት የተከዜ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬትን ጠቅሶ DW ዘግቧል፡ የኮርፖሬቱ ኮምንኬሽን ዳይሬክተር ተርባይኖቹ ለረጅም ጊዜ በመለዋወጫ ዕጥረት ሳቢያ ሃይል ማመንጨት አቁመው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አራተኛው ተርባይንም በቅርቡ ሃይል ማመንጨት ይጀምራል ብለዋል፡፡ በጠቅላላው አራት ተርባይኖች ያሉት ተከዜ ሃይል ማመንጫ ባሁኑ ሰዓት 225 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያመነጭ የኮርፖሬቱ መረጃ ይጠቁማል፡፡

6. የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ለተነደፈው “ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት” 500 ሚሊዮን ብር ለግሻለሁ ብሏል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው ጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ለባለሃብቶችና ዜጎች ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል መሆኑን ባንኩ ባሰራጨው መግለጫ ጠቅሷል፡፡ በተያያዘ ዜና የገንዘብ ማሰባሰቢያው ራት ግብዣ ፕሮግራም በቀጣዩ ግንቦት 11 እንደሚካሄድ ፎርቹን አስነብቧል፡፡

LEAVE A REPLY