የዛሬ ዐርብ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

የዛሬ ዐርብ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

1. የሙስና ተከሳሹ በረከት ስምዖን ዛሬ ለፍርድ ቤት በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል በተጠቀሱብኝ የወንጀል ድርጊቶች በሙሉ ጥፋተኛ አይደለሁም ብለዋል፡፡ ሌላኛው ተከሳሽ ታደሠ ካሳ ግን ቃላቸውን ለመስጠት አልተዘጋጀሁም ስላሉ ተለዋጭ ቀጠሮ ይያዝልኝ ሲሉ አመልክተው ችሎቱ ለመጭው ሰኞ እንዲቀርቡ አዟል፡፡ ችሎቱ የተከሳሾችን ክስ መቃወሚያም ውድቅ አድርጓል፡፡ ተከሳሾቹ ቀደም ሲል በጥረት ኮርፖሬት ሃላፊ ሳሉ ፈጸሙት የተባለው የሃብት ምዝበራና ብክነት ክስ ተዘግቶ ከእስር እንዲፈቱ ያቀረቡት አቤቱታም ተቀባይነት አለማግኘቱን የአማራ መገናኛ ብዙኻን ዘግቧል፡፡

2. ትናንት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (አዜማ) ጉባዔ ዛሬ ብርሃኑ ነጋን የፓርቲው መሪ አድርጎ መርጧል፡፡ ብርሃኑ ከጠቅላላ ድምት ሰጭዎች ውስጥ የ912ቱን ድምጽ አግኝተው ነው የተመረጡት፡፡ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር የነበሩት አንዷልም አራጌ ደሞ ምክትል መሪ ሆነዋል፡፡ ድርጅታዊ ጉዳዮችን ለሚከታተለው የሥልጣን ቦታ የሽዋስ አሠፋ ሊቀመንበር ሲሆኑ ጫኔ ከበደ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡

3. ንግድ ባንክ ከወለድ ነጻ ለሚያበድረው ብድር የሸሪዐ አማካሪዎችን መርጫለሁ ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ በዚህም መሠረት ጄይላን ከድር (ዶ/ር) የአማካሪ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ፣ ሼክ ሞሐመድ ሐብዲን ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል፡፡ ባንኩ በቅርቡ ከወለደ ነጻ አገልግሎት መጀመሩን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

4. ዐለም ዐቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) በየመን እስር ላይ የሚገኙ 3 ሸህ ስደተኞች እንዲለቀቁ ሰሞኑን መጠየቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ አብዛኛዎቹ ታሳሪ ስደተኞች ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ የጤንነትና ደኅንነት ሁኔታቸው አሳሳቢ ነው፡፡ ታሳሪዎቹ በደቡባዊ የመን በላህጅና ኤደን ከተሞች የታሰሩ ሲሆን በኤድን 2 ሺህ 500 ያህሉ የታጎሩት ስታዲየም ውስጥ ነው፡፡ ከላሃጅ እስረኞች 14ቱ በበሽታ መሞታቸውን ድርጅቱ ገልጾ በቅርቡ ግን 1 ሺህ 400 ያህሉ ስለመፈታታቸው ሪፖርቶች እንደደረሱት ጠቁሟል፡፡ 237 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን በቅርቡ በፍቃደኝነት ለመመለስ መዘጋጀቱንም ገልጧል፡፡

5. የቤንሻንጉል ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት መግለጫ አውጥቷል፡፡ በክልሉ በቅርቡ ለተፈጸመው ማንነት-ተኮር ግድያ ጽንፈኛ ብሄርተኞችንና ድብቅ አጀንዳ አላቸው ያላቸውን አክቲቪስቶች ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ለሕግም እንዲቀርቡ አደርጋለሁ ብሏል፡፡ ጥቂት አክቲቪስቶች መተከል የእኛ ነው በማለት የሚያራምዱት ቅስቀሳም የፌደራል ሥርዓቱን የሚንድ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በወሰን አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ወንጀል ፈጻሚዎች ካልተገቱ የባሰ ችግር እንደሚፈጠርም አስጠንቅቋል፡፡ መግለጫው በወጣበት ሰዓት በክልሉ ግጭቶችንና ግድያዎችን ለማጣራት የተሠማራው አጣሪ ቡድን ገና ምርመራው አላጠናቀቀም፡፡

6. ፍርድ ቤት ፖሊስ የቀድሞው የብሄራዊ ደኅንነት ሃላፊ ጌታቸው አሠፋና ሌሎች 4 የደኅንነት ሠራተኞችን እጃቸውን ይዞ እንዲያቀርብለት ትናንት አዟል፡፡ ሌሎች ተከሳሾች ግን ችሎት ቀርበው የቀረቡባቸውን ክሶች ክደዋል፡፡ ዋስትና መብታቸውም እንዲከበርላቸው የጠየቁ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ግን ተቃውሟል፡፡ ችሎቱ በዚሁ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ግንቦት 8 እንደሚቀመጥ ሸገር ዘግቧል፡፡

LEAVE A REPLY