እንኳን ደስ አላችሁ:-
የቀድሞ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የአርበኞች ግንቦት 7፣ እንዲሁም የኢዴፓ ፣ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባላትና ሌሎችም ስብስቦች ባደረጉት የውሕደት ሂደት የተመሰረተው የኢትዮጵያውያን ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰኘው ይህ ፓርቲ ማህበራዊ ፍትህና ዜግነትን መሰረት ያደረገ ፓርቲ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
በማህበራዊ ፍትህ (ሶሻል ዴሞክራሲያዊ) ፍልስፍና መርሆዎች ላይ የተመሰረተ የፖሊቲካ ድርጅት (ፓርቲ) በሁሉም ዘርፎች የመንግስትን ስልጣን በምርጫ ተወዳድሮና አሸንፎ እነዚህን ፓሊሲዎች ተግባራዊ ለማድረግና ሕዝብን በማገልገል ዓላማና ግብ የተመሰረተ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለውጤታማ የጋራ አሰራርና ተግባቦት በአገራችን የፖለቲካ መድረክ ላይ አሁን የሚገኙ በጣም በርካታ ድርጅቶች በመሸጋሸግ እውነተኛ አማራጭ የሆኑና ልዩ ልዩ የፍልስፍናና የፕሮግራማቲክ መሰረትን በመያዝ የሃሳብ፣ የፓሊሲ አማራጮች ፣ የፓለቲካ ፍልስፍና ስፔክትረም ማለትም ግራ ዘመም (left, ዴሞክራሲያዊ ሶሻሊስት) ፣ ቀኝ ዘመም (right) ፣ ከመሃል ወደግራ (left of center) መሃል ወደ ቀኝ (right of center)፣ መሃል (centrist) ፣ ለዘብተኛ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (liberal democracy) ፣ ወግ አጥባቂ (Conservative) ሕገ መንግስታዊ ዘውዳዊ (constitutional monarchy)፣ ወዘተ ሲሟሉ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት የሚደረገውን ሂደት ከሚያጠናክሩት አምዶች አንዱ ይሆናል። እነዚህን መሰል ልዩ ልዩ የፓለቲካ ፍልስፍና/የርዕዮት/የፕሮግራማቲክ/ሃሳብ አመራጮችን ለህዝብ የሚያቀርቡ ጠንካራና ተፎካካሪ ፓርቲዎች መመስረታቸውና መጠናከራቸው ወሳኝ ነው፡፡
የፖሊቲካ ፓርቲዎችን ቁጥር አስመልከቶ በአገራችን በአሁኑ ወቅት ካሉት እጅግ የበዙ ፓርቲዎች ተሸጋሽገው ከ 5- 8 ያልበለጡ እንዲሆኑ ሁሉም የፓለቲካ ሃይሎች በያስቡበትና ሂደቱን ቢጀምሩ ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ምስረታና ጥልቀት ትልቅ ፍይዳ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። በዘርና በብሔር የተደራጁም ሃይሎች ገዥው ፓርቲንም ጨምሮ በሃሳብ፣ በፍልስፍና፣ በራዕይና፣ የአገሪቱን መሰረታዊ ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች ባገናዘበ መልኩ ሁሉንም ብሔሮችና ዜጎችን ወደሚያቅፍና አግላይ ባሕርያትን ወደሚጸየፍ አገራዊ የዜግነት ፓርቲ መሸጋገር ቢችሉ የአገራችንና የሕዝባችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የለመለመና በሁሉም ዘርፍ የሚገለጽ ዲሞክራሲን፣ ፍትህን፣ ዕድገትና ብልጽግናን ለማስፈን ከባድ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
ከባድ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች በአገራችን ኢትዮጵያ የተደቀኑበት ይህ የለውጥ ወቅት እልህ አስጨራሽ በመሆኑ ትዕግስትንና አስተዋይነትን ከመሪዎች የሚጠይቅ ጊዜ ነው። የተመረጡት የኢዜማ ፓርቲ መሪዎች በአገሪቱ እንዲሰፍን ያስቀመጡትን ሃቀኛ ዲሞክራሲ በውስጠ ድርጅት እንቅስቃሴዎች ጥልቀት እንዲኖረው እንደሚያደርጉ፣ እኛ ብቻ እናውቃለን ከሚል የኢትዮጵያ የፓለቲካ ባህልን ከተጣባ አባዜ የተላቀቁና ፣ እንመራዋለን የሚሉት ሕዝብም ጥቅሞቹንና ለህይወቱ የሚበጀውን እንዲሚያውቅ የሚረዱ፣ የእውቀት አድማስ በብዛትም በአይነትም በሰፋበትና በጠለቀበት በዚህ ዘመን በእያንዳንዱ የእውቀት ዘርፍም በአለማችን ጂንየስ የሚባሉ ግለሰቦችም እንኳን ሳይቀሩ በሁሉም ጉዳይ ከፍተኛው የእውቀት አድማስ ላይ በደረሱበት ዘርፍ እንኳን ሁሉን አቃፊና ጥልቀት ያለው እውቀት ሊኖራቸው እንደማይችል የታወቀ ነው ፡፡ ስለዚህም በፖለቲካ ዘርፍ የተሰማሩ መሪዎች ትህትናን ለመላበስ የሚጥሩ እንደሚሆኑ እምነቴ ነው፡፡በየደረጃው ያሉ የፓርቲ አመራሮች እነሱ ከሚከተሉት ፖሊሲም ለየት ያለና የማይፈልጉትንም ሃሳብ እንኳን ቢሆን በጥሞና ለማዳመጥ የሚችሉ፣ እነሱ የሚፈልጉትን ክብርና እውቅና ለሌላውም የሚሰጡ፣ ጠንካራ ስነምግባርና የሞራል ልዕልና ያላቸው፣ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ከግል ፍላጎትና ዝና ያስቀደሙ፣ ትችትን የማይፈሩ፣ ስህተቶችንም ለመቀበልና ለማረም ወኔው ያላቸው፣ ከሁሉም በላይ ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ እንደሚሆኑ ተስፋ አለኝ።
በፓርቲው ምስረታ የተመረጣችሁ የኢትዮጵያውያን ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪዎች- ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አንዱአለም አራጌ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ዶ/ር ከበደ ጫኔ፣ እንዲሁም በጉባኤው በየደረጃው የተመረጣችሁ የአመራር አካላት በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ ትግላችሁና እንቅስቃሴያችሁ የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።