1. ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ 4 የምርጫ ቦርድ አመራር አባላትን ይሾማል፡፡ ካፒታል እንደዘገበው ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲስ ተሹዋሚዎችነ የሚመርጥ አንድ ኮሚቴ አዋቅረዋል፡፡ በአዲሱ የምርጫ ቦርድ አዋጅ መሠረት የቦርዱ የመጀመሪያ ሥራ ሕጋዊ መስፈርቶችን ላሟሉ ፖለቲካ ድርጅቶች የዕውቅና ምስክር ወረቀት መስጠት እንደሚሆን የቦርዱን ኮምኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሸመልስን ጠቅሶ ዘግቧል- ጋዜጣው፡፡
2. የቀድሞው የደህንነት ሀላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት አዟል በሚል የተሰራጨው ዘገባ ትክክል እንዳልሆነ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ። ጠቅላይ አቃቤ ህግ በማህበራዊ ገፁ እንደገለፀው ፍርድ ቤት አቶ ጌታቸው አሰፋና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መጥሪያ እንዲሰጣቸው ይህንንም ፖሊስ እንዲያስፈፅም እንጂ ተይዘው ይታሰሩ የሚል ትዕዛዝ አላስተላለፈም። ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባለፈው ሳምንት ይህን የተሳሳተ መረጃ በማውጣቱ ይቅርታ ጠይቋል።
3. በበረከት ስምዖን አና ታደሠ ካሳ ከሰ ላይ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ከግንቦት 21 ጀምሮ እንዲያሰማ ፍርድ ቤት ማዘዙን የአማራ መገናኛ ብዙኻን ዘግቧል፡፡ ባለፈው ዐርብ ቃላቸውን ያላሰሙትን ታደሠ ካሳ ቃልም ዛሬ ሰምቷል፡፡ ተከሳሹም የተከሰስኩባቸውን ወንጀሎች አልፈጸምኩም ብለዋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ግን ወንጀሉን ለመፈጸማቸው በርካታ ምስክሮች አሉኝ ብሏል፡፡ ተከሳሾቹ በበኩላቸው እስካሁን ጠበቃ ማቆም እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ ችሎቱም ከጣዩ ቀጠሮ በፊት ጠበቃ እንዲያቆሙ አዞ ለጠቦቆቻቸው ጥበቃ እንዲደረግላቸው አዟል፡፡
4. 5 የፖለቲካ ደርጅቶች በመጭው ሐሙስ እንደሚዋሃዱ መግለጻቸውን ሸገር ዘግቧል፡፡ ድርጅቶቹ ቱሣ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ፣ የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረትና ደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ቅንጅት ናቸው፡፡ በጋራ የሚመሰርቱት ውህድ ፓርቲ ደሞ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንደሚሰኝ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል ለውህደት የተስማሙት 8 ድርጅቶች ሲሆኑ 3ቱ ቀድመው ራሳቸውን አግልለዋል፡፡
5. አማራ ክልል ከላይ እስከ ታች መሠረታዊ የአመራር ለውጥ ላደርግ ነው ብሏል፡፡ የአማራ መገናኛ ብዙኻን እንደዘገበው ርዕሰ መስተዳድሩ አምባቸው መኮንን ካሁን በፊት የተደረጉ የአመራር መተካካቶች ሁነኛ ለውጥ እንዳላመጡ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ብቃት የሌላቸው በርካታ አመራሮች ስላሉ መተካካቱ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ይሆናል፤ ለሀገሪቱም ለውጥ ያመጣል ተብሏል፡፡ ከለውጡ መጀመር ወዲህ በክልሉ የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ተቀዛቅዟል፤ የሠራተኞች ግዴለሽነትም ይስተዋላል፡፡ ክልሉ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ተከታታይ ሕዝባዊ ውይይቶች ካካሄደ በኋላ ነው፡፡
6. የእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤት 2ኛ የልዑል አለማየሁ አጽም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ እንደማይፈልጉ ተነግሯል፡፡ ይህንኑም ለንደን ለሚገኘው የአትዮጵያ ኢምባሲ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ደይሊ ሜል ዘግቧል፡፡ የንግስቲቷ ምክንያት የልዑሉ አጽም ሲነሳ በመቃብር ቦታው ሌሎች ተጠጋግተው ያሉ የሙታን አጽሞች ይረበሻሉ የሚል ነው፡፡ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻዉል የንግስቲቱ ምላሽ ተገቢ አለመሆኑንና እንደገና እንዲያጤኑት ለደይሊ ሜል በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል። የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስለ ጉዳዩ አስተያየት ተጠይቆ አልሰጠም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አጽሙ እንዲመለስለት ለ12 ዐመታት ሲጠይቅ ነበር፡፡
7. ፌደራል ፖሊስ ቅዳሜና ዕሁድ ባካሄደው ዘመቻ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩና ወንጀል ሊፈጸምባቸው የነበሩ ተሸከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጧል፡፡ በልደታ፣ ንፋስ ስልክ፣ ላፍቶና ቦሌ ባደረገው ድንገተኛ አሰሳ ከ260 በላይ ሕገ ወጥ ተሸከርካሪዎች እንደተያዙም ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ ግለሰቦቹ በሕገ ወጥ መሳሪያና መድሃኒት ዝውውር፣ ቅሚያና ዝርፊያ ሲሳተፉ የነበሩ ናቸው፡፡ በሸሻ ቤቶች 600 ግለሰቦች፣ ግማሸ ኪሎ ሐሽሽና ከ2 ሺህ 500 በላይ ሺሻ ዕቃዎች ተይዘዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከ250 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጭ ሕንጻዎችን ተከራይተው ነው ወንጀሎቹን ሲፈጽሙ የነበሩት፡፡ ምን ያህል ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ግን አልተገለጸም፡፡