ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያፍነው መንግስት ብቻ ነው? || በመስከረም አበራ

ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያፍነው መንግስት ብቻ ነው? || በመስከረም አበራ

ሃገራችን ለረዥም ዘመናት በተፈራራቂ አምባገነኖች ክርን ስትደቆስ በመኖሯ ሳቢያ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት እጅጉን ተጎድቶ ኖሯል፡፡ በነዚህ አምባገነን መንግስታት ዘመን መናገር ከተቻለም የሚቻለው እነሱኑ ከነአፋኝ ማንነታቸው ለማወደስ ነው፡፡ በተቀረ እውነቱን ለመናገር ከሆነ ሃሳብን መግለፅ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡አምባገነኖቹ ገዥዎቻችን አፈናን የሚያስኬዱበት መጠን፣ተችዋቻቸውን ለማሳደድ የሚሄዱበት ርቀት ብዙ ሲባልበት የኖረ ስለሆነ ያንን መደጋገም የዚህ ፅሁፍ አላማ አይደለም፡፡የዚህ ፅሁፍ አላማ በሃገራችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተግዳሮት የሚመጣው ከመንግስት ብቻ እንዳልሆነ ከየሁት እና ካጋጠመኝ ተነስቼ ማሳየት ነው፡፡

በሃገራችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ከመንግስት ብቻ የሚመጣ ተግዳሮት እንደሆነ በሰፊው ይታመናል፡፡ይህ የሆነው መንግስት እስርቤት ስላለው የማይፈልገውን ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎችን ወደእስር ቤት ሲያጉር ስለሚታይ ነው፡፡ነገር ግን እስርቤት የሌላቸው፣እንደ አምባገነኑ መንግስት የፖለቲካ ስልጣን ያልያዙ አፋኞች በሃገራችን ሞልተዋል፡፡ እነዚህ አፋኞች ምናልባትም ከእነሱ የበለጠ ጉልበት ባለው አምባገነን መንግስት “ሃሳብን ስለመግለፅ መብት ሲታገሉ” ሲታሰሩ ሲፈቱ  የምናያቸው፣መንግስትን በአፋኝነቱ ሲያብለጠለጥሉ የኖሩ  የሚዲያ ሰዎች፣የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ሃሳቡን በመግለፁ፣ጋዜጣ በማሳተሙ መንግስት ያሰረው ሁሉ ሃሳብን የመግለፅ መብት የሚያከብር፣ከአፋኙ መንግስት የሚሻል ነው ማለት አይደለም፡፡በኢትዮጵያ ፕሬስ ውስጥ በአምደኝነት በተሳተፍኩባቸው ዘመናት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አፋኙ ህወሃት መራሹ መንግስት ብቻ እንዳልሆነ በደምብ ተረድቻለሁ፡፡ስለዚህ በሃገራችን ሃሳብን በነፃነት ስለመግለፅ መብት መከበር ምክክሮች እና ውይይቶች ሲደረጉ ራሱ ታፈንኩ የሚለው የግሉ ሚዲያ የታቀፋቸው የአፋኝነት ዝንባሌዎቹን በተመለከ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ይህ ሲደረግ ግን አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡

ከሰሞኑ በሃገራችን UNISCO ባዘጋጀው በዓል ላይም ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በማፈኑ ረገድ ከመንግስት ባሻገር ድርሻ ያላቸው አካላት ጉዳይም ተነስቶ እንደተመከረበት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ብቸኛው አፋኝ መንግስትን ብቻ አድርጎ ማቅረቡ ደግሞ ግማሽ እውነት ስለሆነ ለችግሩ ምሉዕ መፍትሄ አያመጣምና በሁሉም የአፋኝነት ድርሻ፣ዝንባሌ እና ጉልበት ባላቸው አካላት ዙሪያ መነጋገሩ ጠቃሚ ነው፡፡ስለሆነም እኔ በግሌ ያስተዋልኳቸውን፣ሃሳብን በነፃነት ከመግፅ አኳያ ከግሉ ሚዲያ ተዋናዮች በኩል የሚመጡ ተዳሮቶች ናቸው ብየ ያሰብኳቸውን ላንሳ፡፡የማነሳቸው ሃሳቦች በሁሉም የግል ሚዲያዎች ይታያሉ ማለት ላይሆን ይችላል፡፡

በግለሰቦች ባለቤትንት በሚታተሙ ህትመቶች ሁኔታ የጋዜጣው ባለቤት ህወሃት በሃገሪቱ ላይ ነግሶ የሚያደርገውን አፈና ለማድረግ የሚሞክረው፣በጋዜጣው/መፅሄቱ ገፆች ላይ ይገዛ ይነዳ ዘንድ የሰሌን ዘውድ በእጆቹ ሰርቶ ለራሱ የደፋ አምባገነን ሲሆን በጋዜጣው ኤዲትርነት ወይም በሌላ ስም የተቀጠሩ ሰራተኞቹ ደግሞ የኑሮ ነገር ሆኖባቸው፣ባለቤቱ የጠላውን ሰውም ሆነ ሃሳብ የሚጠሉ፣ባለቤቱ የወደደወን ብቻ የሚወዱ “በእርስዎ መጀን” የሚሉ ሲሆኑ  ያጋጥማል፡፡እነዚህ የጋዜጣ ባለቤቶች ከእነርሱ የባሰው የህወሃት መንግስት አንድ ሁለት ጊዜ እስር ቤት ስለወሰዳቸው ብቻ  በቅኑ የሃገራችን ህዝብ ዘንድ የሃሳብን መግለፅ ነፃነት አርበኛ ተብለው ቁጭ ብለዋል፡፡ በተግባር ግን እስር ቤት እና ጠመንጃ ስላለው “የወርቅ” ዘውድ የደፋው አምባገነን የሚያሳድዳቸው “ባለሰሌን ዘውድ” አምባገነኖች የሆኑም አሉበት፡፡

እነዚህ ባለ ግል ፕሬስ ጋዜጠኞች አምባገነንነታቸው በምን ይገለፃል ከተባለ የመጀመሪያ ሆኖ የሚመጣው በገዛ ጋዜጣቸው ስማቸው ተጠቅሶ እንዲተቹ ፈፅሞ የማይፈቅዱ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የእነሱ ወዳጅ የሆነ ሰው ጭምር በጋዜጣቸው እንዲተች የማይፈልጉ፣ ይህንንም በግልፅ የሚናገሩ መሆናቸው ነው፡፡የጋዜጣውን ባለቤት ስም ጠቅሶ በእግረ መንገድም እንኳን ቢሆን መተቸት ንጉስ እንደ መድፈር ተቆጥሮ “ከባለ ሰሌን ዘውዱ” አምባገነን ጋር ወደ መረረ ጠብ የሚከት ነገር ሆኖ “የተደነገገባቸው” የግል የፕሬስ ውጤቶች አሉ፡፡

ከጋዜጣው ባለቤት በመቀጠል አይተቹም የሚባሉት የጋዜጣው ባለቤት ወዳጆች ደግሞ ለጋዜጣው/መፅሄቱ መቸብቸብ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ አላቸው ተብለው የሚገመቱ፣ወይ አንዳች እርጥብ ነገር ይዘው ከጋዜጣው/መፅሄቱ ባለቤት ጋር አንድ ምንጣፍ ላይ አብረው የሚውሉ ስለሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ በግሌ ያጋጠመኝን ባነሳ በአንድ የፕሬስ ውጤት ላይ ልክ ያልመሰለኝን ነገር የፃፈ አምደኛን ለመተቸት ፅሁፍ አዘጋጅቼ ስልክ “በዚህ ጋዜጣ ላይ እንቶኔን መተቸት አይቻልም” ተብየ አውቃለሁ፡፡ እኔም ነገሩ በጣም ስላስደነገጠኝ “እንዲህ ከሆነ እናንተ ግለሰቡ አይተችም እንዳላችሁኝ ጠቅሼ ለሌላ ጋዜጣ እልከዋለሁ” ብየ ፈርጠም በማለቴ “የመጀመሪያውን ክፍል ብቻ እናስተናግዳን” ተብየ በዚሁ ወደእዛ ሚዲያ ሳልመለስ ቀርቻለሁ፡፡ ነገሩ በጣም ስለከነከኝ፣የአንድ ጋዜጣው ሰራተኛ ሰው ሃሳብ ሊሆንም ይችላል በሚል ለጋዜጣው ባለቤት ጉዳዩን አስመልክቼ ለላኩት መልዕክት መልስ ላገኝ አልቻልኩም፡፡

ሌላው በጣም የገረመኝ አጋጣሚ ደግሞ ራሳቸው ባለቤት ባልሆኑበት ጋዜጣ ላይ ጭምር ለመተቸት የማይደፈሩ፣እጅግ አስፈሪ አምባገነን የጋዜጣ ባለቤቶች እንዳሉ ያወቅኩበት አጋጣሚ ነው፡፡ይህ አጋጣሚ በአንድ መለስተኛ ስርጭት ባላት ጋዜጣ አምደኛ ሆኜ በምፅፍበት ወቅት የተከሰተ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከብዙው ፅሁፌ ውስጥ በአንድ አንቀፅ ላይ አንድ  የሌላ ጋዜጣ ባለቤት በጋዜጣው ከፃፈው እና በወቅቱ ብዙ ሰው እውነት ብሎ ከወሰደው ነገር ጋር ያለኝን ልዩነት ገለፅኩ፡፡ፅሁፌን ያነበበው የጋዜጣው ባለቤት ፅሁፉን ወደማተሚያ ቤት ከመላኩ በፊት ደወለልኝ፡፡

ሃሳቤን በመግለፅ ነፃነቴ ላይ ያለኝን ጠንካራ አቋም በደንብ ስለሚያውቅ “እባክሽ ይቅርታ አድርጊልኝ፤ ከፅሁፍሽ አንድ አንቀፅ ላወጣ ነው” አለኝ፡፡”ምን ክፋት አገኘህበት? የተሳሳትኩት ነገር አለ? ማለቴ ከጥሬ ሃቅ አንፃር ልክ ያልሆነ ነገር አገኘህበት?” አልኩት፡፡ “አይደለም እንቶኔን ስሙን አንስተሽ ሃሳቡን አልቀበልም ብለሽ ያቀረብሽው ማስረጃ ስህተት ባይሆንም ለእኔ ግን ጥሩ አይደለም፤ለጋዜጣውም ህልውና ላይ ችግር ይመጣብኛል” አለኝ፡፡ “እኔ የምትለው ነገር ምንም አልገባኝም፤ እንዲህ ስለተፃፈ ከጋዜጣው ህልውና ጋር ምን አገናኘው? አንተስ እሱን ይህን ያህል የምትፈራው ለምንድን ነው? የሚያሳትምልህ እሱ ነው እንዴ?” አልኩት፡፡ “አያሳትምልኝም፤ ግን ነገሩ ብዙ ነው፣በስልክ የሚሆን አይደለም ስንገናኝ እነግርሻለሁ አሁን ቅር ሳይልሽ ሃሳቡን እንዳወጣው ፍቀጅልኝ” አለኝ፡፡ “አሁን እየጠየቅከኝ ለያው ነገር ልክ እንዳለሆነ ግን ታምናለህ? እሽ ብልህ እንኳን ይሄን አምነህ መሆን አለበት” አልኩኝ የልጁ አቀራረብ ቢያሸንፈኝም ነገሩ እያስቆጣኝ፡፡ “አዎ! ልክ አለመሆኑ ምንም አያጠያይቅ፡፡አንች አስተማሪ ስለሆንሽ እንዲህ ያለውን ነገር ላታውቂ ትችያለሽ:: እኛ አለቃችን ብዙ ነው፤ፕሬሱ ላይ ያለው ችግር መንግስት በፕሬሱ ላይ ከሚያደርገው አይተናነስም፤ሁሉንም ስትመጭ እናወራለን” ብሎኝ ስልኩን ዘጋ፡፡

ስንገናኝ የነገረኝ ነገር የግሉ ፕሬስ ተግዳሮት የመለስ ዜናዊ ክንድ ብቻ እንዳልሆነ ያረጋገጠልኝ ነገር ነው፡፡ እንደነገረኝ ከሆነ በሃገሪቱ የግል ፕሬስ ሽያጭ እና ስርጭት ላይ ሰፊ እጅ ያላቸው የተወሰኑ ስመጥር የጋዜጣ/መፅሄት ባለቤቶት የሆኑ ጋዜጠኞች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የጋዜጣ/መፅሄት አከፋፋዮችን በእጃቸው አድርገው ከእነሱ ጋዜጣ እና መፅሄት ቀጥሎ የማንን መፅሄት ስርጭት እንደሚያሳልጡ እና የነማንን ጋዜጣ ስርጭት እንደሚያከስሙ ይነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ የእነሱ ስም ተጠርቶ የተተቸበትን ጋዜጣ፣ከእነርሱ ጋር በሆነ ጉዳይ የተቀያየመ ሰው የሚያሳትመውን የህትመት ውጤት ወይም ከእነርሱ ጋዜጣ በይዘቱ የተሻለ እና ውሎ አድሮ የእነርሱን ጋዜጣ ሽያጭ የሚገዳደር የመሰላቸውን  የህትመት ውጤት ስርጭት አዳክመው ከገበያ እንዲወጣ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በተለይ አዳዲስ የህትመት ውጤቶችን ለመጀመር ከነዚህ ጋዜጠኞች እና አከፋፋዮች ጋር መልካም ግንኙነት መመስረት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ለዚህ ነው እንደማትወጅ ባውቅም ፅሁፍሽን ቆርጬ እንዳወጣ እንድትፈቅጅልኝ በጣም ያስቸገርኩሽ” ሲል ያስጨነቀውን ነገር አጫወተኝ፡፡

በጣም ገረመኝ፣መቀበልም አቃተኝ፡፡በተለይ ይህን ያደርጋል የተባለው ጋዜጠኛ ከሩቁ ያለው ምስል እንዲህ የወረደ ስላልሆነ፣ እኔም ከሩቅ ከሚያውቁት መሃል ስለሆንኩ የተነገረኝን እንደወረደ መቀበል አቃተኝ፡፡ የሚነግረኝ ሰው በአንድ በኩል የኔን ፅሁፍ ቆርጦ ለማውጣት በሌላ በኩል እኔንም ላለማስቆጣት የተጨነቀውን መጨነቅ አይሉት መርበትበት ሳስብ ደግሞ ነገሩ እውነትነት አያጣውም የሚል ነገር አስቤ በዝምታ መገረም ጀመርኩ፡፡በሃሳቤ መሃል አንድ ጥያቄ መጣልኝ፡፡ “አከፋፋዮቹ ግን ከያንዳንዱ ጋዜጣ ገንዘብ ያገኛሉ አይደል?” አልኩት “አዎ” አለኝ፡፡”ታዲያ በነዚህ አምባገነን ጋዜጠኞች ታዘው የጋዜጦችን ስርጭት ሲያግዱ ራሳቸውስ አይጎዱም ወይ?” አልኩት፡፡

“ይህ እንደ አፈናው አላማ ይወሰናል፡፡አታሰራጩ የሚሏቸው ጋዜጠኞች ስርጭቱ እንዲገታ የሚፈልጉት ጋዜጣ ከእነሱ ጋዜጣ የሚበልጥ ይዘት ያለው ስለመሰላቸው ከሆነ ጋዜጣው ተዳክሞ ከገበያ ሲወጣ የእነርሱ ጋዜጣ ኮፒ ይጨምራል፡፡ስለዚህ አከፋፋዮቹ ዞሮ ዞሮ ከከልካቹ ጋዜጠኞች ጋዜጦች ኮፒ ማደግ ገንዘቡን ያገኙታል፡፡የአፈናው አላማ ስለነሱ መጥፎ የፃፈን ወይም ሲፃፍ ዝም ብሎ ያሳተመ የጋዜጣ ባለቤትን ለመጉዳት ከሆነ ደግሞ እነዚህ ጋዜጠኞች የተሻለ ስርጭት ያለው ጋዜጣ/መፅሄት ስለሚኖራቸው ኪሳራውን እስከመሸፈን ሊሄዱ ይችላሉ፡፡” ሲል በጣም ያስደነገጠኝን  ነገር አጫወተኝ፡፡

ይህን ጉዳይ ከሰማሁበት ቀን ጀምሮ ነገሩ  ምናልባት የአንድ ጋዜጠኛ መረዳት ሊሆን ይችላል ወይስ በእውነት ያለ ነገር ነው የሚለውን ለማጣራት በግሉ ፕሬስ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በምገናኝበት ጊዜ ጉዳዩን ማንሳቴ አልቀረም፡፡ የጠየቅኳቸው ሁሉ ሰዎች ያረጋገጡልኝ ነገር የህትመት ውጤቶች ስርጭት ጉዳይ ከአከፋፋዮች እና በመስኩ ስም ካገኙ የጋዜጣ ባለቤት ጋዜጠኞች በጎ ፈቃድ ጋር የተያያዘ ነገር እንዳለው ነው፡፡ስለዚህ ስለ መናገር ነፃነት መብት መከበር ሲታሰብ ከመንግስት አንባገነንነት በተጨማሪ የነዚህ እና ሌሎች እኔ ያላነሳኋቸው ተግዳሮቶች አንፃርም ማየቱ ተገቢ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ከመንግስት እጅ ውጭ ባለው ተግዳሮት ዙሪያ ሳይንሳዊ ጥናት ቢደረግ ተጨማሪ ግኝትም አይጠፉም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጥናቶችን አድርጎ መፍትሄ ማስቀመጡ ለመናገር ነፃነት መብት መከበር አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

ከህትመት ሚዲያው አለፍ ስንል ሃሳብን በነፃነት የመግለፅን መብት አስመልክቶ ተግዳሮት የማያጣው የብሮድካስት ሚዲያው ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ ሁኔታ ስለብሮድካስት ሚዲያው የማነሳው ሃሳብ በሃገራችን መንግስት የሚተዳደሩ  እና በሌላ ሃገር መንግስት ስር ያሉ እንደ ቪኦኤ እና የጀርመን ድምፅ (DW) ያሉ ሚዲያዎችን አይጨምርም፡፡ከነዚህ ሚዲያዎች ውጭ ያሉ  በቦርድ የሚተዳደሩም ሆኑ በሌላ መንገድ የሚሰሩ የብሮድካስት ሚዲያዎች  እንደ ፕሬሱ ሁሉ የግለሰቦች ረዥም እጅ ጫና ሚኖርባቸው ሚዲያዎች ቢኖሩም በእኔ ግላዊ ግምገማ የተሻለ የሃሳብ ብዝሃነት የሚያቀርቡ እና በገለልተኝነቱም ጥሩ የሚባል አቋም ያላቸው ሚዲያዎችም አይጠፉም፡፡ በግሌ ዋዜማ ራዲዮ የሃሳብ ብዝሃነት በማቅረብ፣ተዓማኒ ዜናዎችን በመስራት፣የፖለቲከዊ ሁኔታዎችን እና የግለሰብ ጋዜጠኞችን ግላዊ የአቋም ለውጥ እየተከተሉ የማይዋልሉ ጠንካራ ትንታኔዎችን በማቅረብም ሆነ በገለልተኝነቱ በኩል ጥሩ የሚባል ሚዲያ ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ይህ ሚዲያ ወደ ቴሌቭዝን/ሬዲዮ አድጎ አብዛኛው ህዝብ የሚከታተለው ቢሆን መልካም ነበር፡፡

ሌላው የብሮካስት ሚዲያ ኢሳት ነው፡፡ኢሳት ህወሃትን በመታገሉ በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረገ ሚዲያ ቢሆንም ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የፓርቲ ንብረትንነትም ስለማያጣው በገለልተኝነቱ በኩል አፍ ሞልቶ የሚያናገር ነገር የለውም፡፡ይህ ገለልተኝነት የሚያንሰው የኢሳት ተፈጥሮ አምባገነኖችን ለመታገል አማራጭ ያልነበረው ነገር ነው ቢባል እንኳን አሁን ህወሃት ከወረደ በኋላ አንፃራዊ የመናገር ነፃነት እየታየ ነው በሚባልበት ወቅት ሊቀር የሚገባው ነገር ነው፡፡ከገለልተኝነቱ በተጓዳኝ የሃሳብ ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድም ኢሳት የሚያንሰው ነገር ብዙ ነው፡፡ኢሳት ሲመሰረት የህወሃትን አምባገነንነት ለመታገል ተብሎ መመስረቱ ህወሃትን የተካን ሁሉ ብፁዕ አድርጎ ማቅረብ ማለት እንዳልሆነ ሁሉም የሚዲያው አባላት አና አካላት የተረዱ አይመስልም፡፡በመሆኑም  ህወሃትን ለተካው የዶ/ር አብይ መንግስት ሆደ ቡቡነት ከማሳየት አልፎ ጥብቅና የሚሞክረው ነገር የሚያሳዩ ጋዜጠኞቹን ወደ መስመር ማስገባቱ አልሆን ብሎታል፡፡

እነዚህ በአብይ መንግስት ላይ የማጠና ሆድ ያላቸው የኢሳት ጋዜጠኞች  በተለያዩ ቦታዎች ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ወይም ሚዲያው ሲመሰረት ጀምሮ የቆዩ በመሆናቸው ከበድ ያለ እጅ ሳይኖራቸው አልቀረም፡፡ይህ ደግሞ የሃሳብ ብዝሃነትን ለማፈን ለፈለገ ሰው አስቻይ ሁኔታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ እዚህ ላይ ነገሩን ለማስተካከል መስራት የሚችለው ጣቢያው ይመራበታል የሚባለው ቦርድ እና የጣቢያው ማኔጅመንት ነው፡፡እነዚህ አካላት ኢሳት ብዙ ሃሳብ የሚስተናገድበት፣የኤዲቶሪያል ነፃነነት ያለው ሚዲያ እንጅ ማንም በለጥ እና ከበድ ያለ እጅ እንዳይኖረው የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው፡፡የኤዲቶሪያል ነፃነት ባለበት ሚዲያ ደግሞ ጋዜጠኞች የኤዲቶሪያል ሃፊዎቻቸውን ሳይፈሩ፣ሳይሸማቀቁ የሃሳብ ብዝሃነት ያለውን ፕሮግራም ሰርተው ያቀርባሉ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ለአድማጭ ገዝፎ የሚታይ ሚዲያውን የሚገዛው አንድ ሃሳብ አይኖርም ማለት ነው፡፡ኢሳት ግን ቀደም ካሉ ዘመናት ጀምሮ እስከ ዛሬ አንድ ገዝፎ የሚታይ ሃሳብ አንግቦ የሚራመድ ሚዲያ ነው- በፊት ህወሃትን መቃወም አሁን ደግሞ የአብይ መንግስት በትችት እንዳይደናቀፍ ዘብ መቆም አይነት ነገር፡፡

የአብይን መንግስት በትችት እንዳይደናቀፍ ዘብ የመቆሙ የኢሳት አካሄድ በሁሉም የኢሳት ጋዜጠኞች የሚቀነቀን ባይሆንም በጣቢያው ላይ ከበድ ያለ እጅ እና ሻል ያለ ስልጣን  ባላቸው ጋዜጠኞች የሚዘመር መሆኑ የጣቢያውን ገለልተኝነት ከመጉዳቱም በላይ ከህዝብ ጋርም ሊያራርቀው እየሞከረ ነው፡፡ይህ ነገር ህወሃት “ልማታዊ ጋዜጠኛ” ከሚለው ጋር መሳ የሚሆን “የቲም ለማ ለውጥ ጥበቃ ጋዜጠኞች” የሚባል ዘይቤ እንዳያመጣብን ያሰጋል፡፡የኢሳት የቲም ለማ ለውጥ ጥበቃ ጋዜጠኞች ዝንባሌ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን መጋፋቱም አልቀረም፡፡

በቅርቡ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ  ከጋዜጠኛ ቴድሮስ ፀጋየ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ እንዳታቀርብ በኢሳት ኤዲቶሪያል ቦርድ መወሰኑ እና የኢሳት ቦርድም ሆነ ማኔጅመንት ከህዝብ በሰፊው ተቃውሞ የገጠመውን  ይህንን ውሳኔ ማፅናቱ ህዝብ የማክበር ምልክት አይደለም፡፡የህዝብን ድምፅ ችላ ማለት የአምባገነንነት ጅማሬ ነው፡፡በተጨማሪም ይህ ነገር የኢሳት ቦርድም ሆነ ስራ አስፈፃሚ ለመናገር ነፃነት ያለውን አቋም ያስገመገመበት፣ትዝብት ላይም የወደቀበት ክስተት ነው፡፡ ሁለቱ ጋዜጠኞች ያደረጉት ውይይት እንዳይቀርብ የተደረገበትን ምክንያት ለጋዜጠኛ ርዕዮት አሳውቀናል ከማለት በዘለለ ምንም አሳማኝ ነገር ለህዝብ ማቅረብ ያልቻለው የኢሳት የኢዲቶሪያል ቦርድ እቃወመዋሁ እያለ ሲያብጠለጥለው የኖረውን የአፋኙን የህወሃት መልክ እንደማያጣ ለህዝብ አሳይቷል፡፡

ፕሮግራሙ ለህዝብ እንዳይቀርብ የተደረገበት ምክንያት በግልፅ ለህዝብ እስካልተነገረ ድረስ ጉዳዩ ጋዜጠኛ ቴድሮስ የጠ/ሚ አብይን መንግስት ከመተቸቱ ጋር ተያይዞ የመጣ ጉዳይም ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ቴድሮስ አብይን ሲተች እንደ ሲሳይ አጌና ያሉ የኢሳት ጋዜጠኞችንም አብሮ መተቸቱ በኢሳት ሚዲያ ላለመስተናገዱ ምክንያት እንዳልሆነስ አጋጁ የኢዲቶሪያል ቦርድ እንዴት ማሳመን ይችላል? “ኢሳት አፈና አያውቅም” ብሎ መግለጫ  ማውጣት እና አፋኝ አለመሆንን በተግባር አንድ ሁለት ብሎ ማስረዳት ይለያያሉ፡፡በበኩሌ የኢሳት ኤዲቶሪያል ቦርድ ያገደውን ፕሮግራም ያገደበትን ምክንያት ዘርዝሮ እስካላሳመነኝ ድረስ ነገሩን ከአፈና ሌላ ስም ልሰጠው አልችልም፡፡

ይህ ማለት ደግሞ ኢሳት ውስጥ በስመ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ለራሳቸው የዳንቴል ዘውድ ሰርተው የደፉ ጥቃቅን እና አነስተኛ አምባገነኖች አሉ ማለት ነው ወደሚል ጥርጣሬ ይመራል፡፡ይህን የአምባገነንነት ዝንባሌ ሃይ ማለት ያልቻለው የኢሳት ማኔጅመነትም ሆነ ቦርድ የአምባገነንነቱ ተጋሪ ነው፡፡ኢሳትን ከሚመሩ የቦርድ አባላትም ሆነ የኤዲቶሪያል ቦርድ አባላት ከሆኑ ግለሰቦች ውስጥ ለወትሮው አፈና ሊያደርጉ ቀርቶ እነሱ በተገኙበት መድረክ አፈና ይኖራል ተብሎ የማይሰቡ ሰዎች መኖራቸው አምባገነንን የተቃወመ ሁሉ ራሱ አፋኝ አይሆንም ማለት እንዳልሆነ፤አፋኙም መንግስት ብቻ እንዳልሆነ አሳይቷል፡፡

LEAVE A REPLY