የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ (ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)
በአንድ አካባቢ ዕዮብ እና ስብሃት የተባሉ – እጅጉን የሚዋደዱ ታዋቂ ወጣት ምሁራን ስለሀገራቸውና ሕዝባቸው ቀን ከለሊት ሲወጡና ሲወርዱ የሥራቸውን ሂደት ከውጤታማነት አንጻር ሲመለከቱት እጅጉን ያነሰና እዚ ግባ የማይባል እየኾነባቸው ግራ ቢጋቡ እርስ በራሳቸው መወያየትና ሰፊ ጊዜ መውሰድን ልማድ ማድረግን አንድ ከጭንቀት የማረፊያ መንገድ አድርገው መጠቀም ከጀመሩ እጅግ በርካታ ጊዜያትን ማሳለፍ ከመጀመራቸው የተነሣ ዓመታት ተቆጥሮ ወጣትነታቸው ወደ ጎልማሳነት መለወጡን እንኳንስ እነሱ የአካባቢው ማሕበረሰብ የሚያውቀው የአደባባይ እውነታ ነው፡፡
የአካባቢው ማሕበረሰብ ከትምህርት ገና ተመርቀው እንደመጡ በየጊዜው እየሰበሰቡ እነሱ በቀላሉ መረዳት ያልቻሉትን ነገር ግን ለነሱ እጅጉን የቀለለ ኹለንተናዊ ሕብረተሰብን የማነጽ ተግባርን ያከናውኑ እንደነበር “አንደበተ ርቱዓን” እያለ ዛሬም ድረስ ይገልጻቸዋል፡፡
ምሁራኑ ማሕበረሰባቸውን ለመለወጥ እጅጉን የደከሙ፣ ብዙ ዋጋ የከፈሉና እስከመታሰር ድረስ የደረሰ ኹለንተናዊ መስዋዕትነት የከፈሉ ቢኾንም በጊዜ ብዛት የፈተናው ጫና ስለበዛባቸው ዛሬ ዛሬ ኹሉን ነገር እርግፍ አድርገው ትተው ለብቻቸው ካልኾነ በቀር ፈጽመው ከሌላ ሰው ጋር ስለማሕበረሰብ የማያነሱ ዝምተኞች በመኾን ይታወቃሉ፡፡
ብዙዎች የሀሳብ ምክር ሲፈልጉ ግን ተሯሩጠው የሚሄዱት – ምስጢራቸውን የሚያጋሯቸው ለነሱ መኾኑን ብዙዎች ያውቃሉ፡፡ ሁለቱም ሳያገቡና ሳይወልዱ – ከሥራ ውጭ ምን እንደሚያደርጉ – ማንም ሳያውቅ በጋራ በደስታ ይኖራሉ፡፡
እንደልማዳቸው ሲወያዩ አቶ አዕምሮ የተባሉ በአካባቢው ማሕበረሰብ ዘንድ በዝምተኛና በብቸኝነታቸው የሚታወቁ አረጋዊ የባሕል ሕክምና አዋቂ ወደቤታቸው ዘልቀው ሲገቡ ጨዋታቸውን አቋርጠው – ከመቀመጫቸው በመነሣት ሰላምታ ሰጥተው በመቀመጥ ዝም ዝም ሲሉ፡-
አቶ አዕምሮ፡ “ምነው ልጆች ጨዋታችሁን ቀጥሉ እንጂ?” አሉ፡፡
ስብሃት፡ “አባቴ – ዝም ብለን ስለራሳችን ነበር – ስንወያይ የነበረው፡፡”
አቶ አዕምሮ፡ “ስለምናችሁ?”
ስብሃት፡ “ስለሕይወት ውጣ ውረዳችን – ስለፍሬ አልባ የዓመታት ከንቱ ድካማችን – እኔ “ወድቀናል! – የተማርነው ለዚህ አልነበረም – ማሕበረሰብን የማይለውጥ ማሕበረሰባዊ ዕውቀት ትርጉም አልባ ነው!” ስል እሱ “እኛ የቻልነውን ሞክረናል – ለኹሉ ጊዜ አለው እና ትክክለኛው ጊዜ ይሄ ላይኾን ይችላል፡፡” እየተባባልን ነበር፡፡” በአድናቆት ፊታቸውን አብርቶ – ከፍና ዝቅ እያደረጉ የሚከታተሉት
አቶ አዕምሮ፡ “እድለኞች ናችሁ – ” ሲሉ
ስብሃት፡ አቋጧቸው “አባቴ – በምን?”
አቶ አዕምሮ፡ “ሰው እንኳንስ ስለሌላውና ስለመጻኢ ዕድሉ ይቅርና ስለራሱ እንኳ በማያስብበት ጊዜ – ስለሌላው ማሰብና መጨነቅ ታላቅ ጸጋ ነው፡፡”
ስብሃት፡ “ፍሬ አልባ ጸጋ!”
አቶ አዕምሮ፡ “ልጄ ለምን ፍሬ አልባ አልክ?”
ስብሃት፡ “ማሕበረሰብን ከውድቀት መታደግ ያልቻለ ጸጋ ስለኾነ!”
አቶ አዕምሮ፡ “ልጄ እናንተ እኮ አዋቂዎች ናችሁ፡፡”
ስብሃት፡ “አባቴ አዋቂዎች መኾናችንን ብዙዎች ይነግሩናል – ነገር ግን ዕውቀቱን አይሹም! ብዙዎች እውነተኞች መኾናችንን ብዙዎች ያምናሉ – ነገር ግን ዕውነትን አይከተሉም! እኛ ጋር ሕብረተሰብን የሚጠቅም ብዙ ነገር እንዳለ – ብዙዎች ያውቃሉ – እንኳንስ ብዙዎች ጠላት ያደረጉንም እንደእጅ መዳፋቸው በርግጠኝነት ይመሰክራሉ፡፡ ነገር ግን – – – ”
አቶ አዕምሮ፡ “ግን?”
ስብሃት፡ “ግን ፍሬ አላፈራንም! ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ አላደረግንም! ማወቅን ወደ ተግባር – ማመንን ወደ መታመን ለውጠን የሕብረተሰቡን አኗኗር አለወጥንም፡፡ – ” እንባ እያቀረረ “ሕብረተሰቡን ከውሾች መታደግ አልቻልንም፡፡ እውነትን ይዘን የሃሰተኞች መጫወቻ ሲኾን ዝም አልን! ትንሽ አዋቂዎች ሳለን የአደባባይ አላዋቂዎች መጫወቻ ሲኾን ከዳር ኾነን ተመለከትን! ሲሸጡት ዝም – ሲያታልሉት ዝም – ያልኾነውን ኾነ – የኾነውን አልኾነም ብለው በገሃድ ክደው ለከሃዲዎች አሳልፈው ሲሰጡት – ዝም” እንባው እየወረደ መሬት መሬት እየተመለከተ “ባሪያዎች ለላቀ ባርነት አሳልፈው ሲሰጡት – ዝም! – ያልታረሙ አንደበቶች ማሕበረሰብን ዋጋ ሲያስከፍሉት – ዝም! ባርነት እንደነጻነት – ዝቅጠት እንደክብረት – ወርደት እንደከፍታ – መሰይጠን እንደመሠልጠን ሲደሰኮር – ዝም!”
ዕዮብ፡ “ስብሃትዪ የቻልነውን ሞከረናል – ምንችለውን አድርገናል፡፡”
ስብሃት፡ “ለምን ነበር – የሞከርነውና ያደረግነው?”
ዕዮብ፡ “ውጤት ለማምጣት!”
ስብሃት፡ “ምን ውጤት አስገኘን?” – ዕዮብ አንገቱን ደፍቶ ዝም አለ፡፡ አቶ አዕምሮ ጺማቸውን እየነካኩ አትኩረው እያፈራረቁ ሁለቱን ይመለከታሉ፡፡ “ዕዮባ ራሳችንን እናታል ካላልን በቀር ቢያንስ የምንፈልገው ውጤት እንዳልመጣ – ማንም ያውቃል፡፡ ጥረታችንንስ ያቆምነው – ለዛ አይደል? አላዋቂዎች፣ አስመሳዮችና ሴረኞች በማሕበረሰቡ ላይ እንዲሠለጥኑበት የፈቀድነው – እኛ አይደለን?”
ዕዮብ፡ “እኛ ምን ሥልጣን ኖሮን ነው የምንፈቅድለት? – ሕብረተሰቡ አይደለ እንዴ – በራሱ ላይ እንዲሠለጥኑበት የፈቀደው?”
ስብሃት፡ “እኛ ላይ አልሠለጠኑም? እነሱን ሸሽተን – እነሱ ሲናገሩ እኛ ዝምታን አልመረጥንም? እነሱ ልታይ ልታይ ሲሉ – እኛ ላለመታየት አልተደበቅንም?”
አቶ አዕምሮ፡ “ሕብረተሰቡ እኮ ስለማያውቅ ነው!”
ስብሃት፡ “ምኑን ነው የማያውቀው አባቴ? ሕብረተሰቡ እኛ ጋር እውነት እንዳለ አያውቅም? እኛ እሱን ልንጠቅመው እንደምንችልስ አይገምትም? አስመሳዩ፣ ሴረኛውና ውሸታሙ ማን እንደኾነስ አያውቅምን?”
ዕዮብ፡ “ሕብረተሰቡ በደንብ ያውቃል፡፡ ሌባ ማን እንደኾነ በደንብ ያውቃል ነገር ግን ከሌባው ጋር ራሱ አብሮ መታየት፣ መብላት፣ መጠጣትና መጋባትን ይሻል፡፡ ቡና ቤት የምትሰራ ሴት ደንበኞቿን ታውቃለች፡፡ ነገር ግን የምትፈልገውን እስካገኘች ድረስ ስለሌላው ምናገባኝ ትላለች፡፡ የናትና ያባቷን ቤት ዘርፈው ለሌላ ባዕድ አሳልፈው ሲሰጡት ዝም ብላ ግፈኞቹ እሷ ጋር ሲመጡ እያስመሰለች ትቀበላለች፡፡ የራሷን ገንዘብ እጅጉን አሳንሰው ሲሰጧት አመስግና ትቀበላለች እንጂ የሷ መኾኑን አትገነዘብም፡፡”
አቶ አዕምሮ፡ “ልጆቼ ይህ ሃይማኖተኛና በፈጣሪ የተወደደ ሕብረተሰብ ምን ነካው?”
ስብሃት፡ “የአደባባይ አስመሳይነትን፣ ቅጥፈትን፣ ሃሰተኛነትና ሴረኛነትን የሚሸከም ሃይማኖተኛ አለን? ሃይማኖተኛነት ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለነጻነት፣ ለሃቅ፣ ለእኩልነትና ለህብረት መቆም አይደለምን? ሃይማኖተኛነት ድንበር መሻገር አይደለምን? ድንበር የማይሻገር ሀሳብ ያለው – እንደምን ድንበር የሚሻገር ዕምነት አለው ሊባል ይችላል? ዕውን ፈጣሪ ሃሰተኛ፣ አስመሳይ፣ ሴረኛነትና ፍሬ ከርስኪ የሃሜት ቋት የኾነ ወዳጅ አለውን?”
ዕዮብ፡ “ኹለንተናዊ መስዋዕትነት የማይከፍልና መክፈሉ በተግባር ያልተገለጠ ሃይማኖተኛነት እንደምን ያለ-ነው? በዕውነትና በሃሰት፣ በግልጽነትና በአስመሳይነት፣ በነጻነትና በባርነት መሐከል ድንበር ማበጀት ያልቻለ የፈጣሪ ወዳጅ እንደምን ያለ-ነው?”
ስብሃት፡ “ሃይማኖተኛነት ከፈጣሪ ጋር መኾን አይደለምን?”
አቶ አዕምሮ፡ “በትክክል!”
ስብሃት፡ “ከፈጣሪ ጋር መኾን ኹሉን ፈተና ለማሳለፍ ያስችል የለምን? የጥንተ ጠላት ባሪያና ገረድ አለመኾን አይደለምን?”
አቶ አዕምሮ፡ “በትክክል!”
ስብሃት፡ “ታድያ ዕውን ማሕበረሰቡ በፈጣሪ የሚወደድ ተግባር እያደረገ ነው?”
አቶ አዕምሮ፡ “ፈጽሞ!”
ስብሃት፡ “የሚከተላቸው፣ የሚያጨበጭብላቸውና የሚያደንቃቸው የጥንተ ጠላት ባሪያዎችና ገረዶች አይደሉምን? ፈጣሪ የሚጠየፋቸው ተግባራት በማሕበረሰቡ ላይ አልሠለጠኑምን? የትንቢት መፈጸሚያና ትንቢት ፈጻሚ አልተበራከተምን? ክፉ መንፈስ የሠለጠነባቸው በአደባባይ ክብርና ሞገስን አላገኙምን? የፈጣሪ ወገን በቁጥር እጅጉን አንሰው – የጥንተ ጠላት ግብረ አበሮች በቁጥር አልበረከቱምን? በዲሞክራሲ ስም እነሱ አልሠለጠኑምን?”
ዕዮብ፡ “ሃይማኖተኛ ነንና ነበርን! ፈጣሪ ይወደን ነበርና ይወደናል! የሚሉ ጽንሰ ሀሳቦች የተምታቱብን ይመስለኛል፡፡”
አቶ አዕምሮ፡ “ማወቅ ስቃይ – መረዳትስ መከራ ነው!” ብለው ከመቀመጫቸው ሲነሱ
ስብሃት፡ “ዕውነት ነው አባቴ! አውቆ ምንም አለማድረግ አለመቻል እጅጉን ስቃይ ነው! መረዳትና መገንዘብ ያለ መፍትሔ ባለቤትነት እጅጉን የላቀ መከራ ነው!”
ዕዮብ፡ “ዕውነት ብለዋል አባቴ! በዓለም ፍሬ ይዘው መዝራት አለመቻል! ዘርቶ በመትጋት የፍሬ ባለቤት ለመኾን አለመታደል! መስራት እየቻሉ አለመስራት – ማድረግ እየቻሉ አለማድረግ ስቃይ – ከስቃይም ተወዳዳሪ የሌለው ስቃይ ነው፡፡”
አቶ አዕምሮ፡ “እሱ ራሱ ይርዳችሁ! ሸክሙን እሱ ራሱ ያቅልላችሁ! ፈጣሪ የልቦናችሁን መሻትና ስቃይ ከዋጋ ይቁጠርላችሁ!” ብለው ወደ በራፉ ሲያመሩ ተከትለው ሸኟቸው፡፡
ዕውን ማወቅ ያለ ተግባር ምን ይረባል? ዕውነትስ ያለ ዕውነተኛነት – ዕምነትስ ያለ ታማኝነት ትርጉም ይኖረው ይኾን? ፋይዳ በሌለው ትርጉም አልባ ፍሬ ከርስኪ ጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች በሠለጠኑበት – መሠልጠንና መሰይጠን በተምታታበት ማሕበረሰብ – የወሬ ቅኝ ግዛት ውስጥ በዘቀጠ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ – ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላልን? እንደማይቻል 100% እርግጠኞች ብንኾንም ማንሣት ካለማንሣት፤ ተስፋ ማድረግ ተስፋ ካለማድረግ በእጅጉ ይሻላል የሚለውን በሙሉ ልብ በማመንና በማወቅ – በተግባር ይገለጽ ዘንድ አነሣን፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከልወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!
ቸር እንሰንብት!