ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በፀጥታ ስጋት ምክንያት ሳይካሄድ የቀረው የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ፤ ሐሙስ በአዳማ ከተማ በዝግ ስታዲየም እንዲካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሊግ ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔ ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እንደማይቀበል፣ ጨዋታውንም እንደማያካሄድ አስታውቋል፡፡
በ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአ/ አ ስታዲየም ግንቦት 25 ቀን (እሁድ) ሊካሄድ የነበረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የተሰረዘው ከመንግስት የፀጥታ ኃይል በደረሰ መረጃ የደህንነት ስጋት በስታዲየም እንዳለ በማሳወቁ መሆኑን የገለፀው የሊግ ኮሚቴ፤ “አሁንም የመንግስት የፀጥታ ኃይል የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ባሉበት ጨዋታው መካሄድ የሌለበት መሆኑን በጥብቅ ያስገነዘበ በመሆኑ፣ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በአዳማ በአበበ በቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ያለ ተመልካች ይካሄዳል” ሲል ውሳኔውን አፅድቋል፡፡
እሁድ ዕለት የኹለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንዲቋረጥ ከተደረገበት ሰዓት አንስቶ ውሳኔውን የተቃወመው፣ በደጋፊዎቹ ላይም የፀጥታ ኃይሎች ያደረሱትን ተገቢ ያልሆነ ዕርምጃ በእጅጉ ያወገዘው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ፤ በአዳማ ከተማ ያለ ተመልካች በዝግ ስታዲየም ይካሂድ የሚለውን ውሳኔ ፈፅሞ እንደማይቀበለው፣ጨዋታውንም እንደማያደርግ ጭምር ይፋ አድርጓል፡፡