ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ጉራራ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ በመስጊድ ቦታ ምክንያት በእስልምና ዕምነት ተከታዮች መሐል ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ በሰውና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ደርሷል፡፡
በተጠቀሰው አካባቢ ያለ የሙስሊም መቃብርን በጥበቃነት ተቀጥሮ ላለፉት 24 ዓመታት የሠራው አቶ መኸዲ ሸፋ፤ ከተለያዩ ስፍራዎች የሚመጡ ሰዎች ባዶ የመንግስት ቦታ ላይ ወረራ ባደረጉበት ወቅት፣ እርሱም ከሚጠብቀው መቃብር አጠገብ የተወሰነ መሬት ከልሎ በመያዝ ለ23 ዓመታት ቤት ሰርቶ ኖሯል፡፡
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከመቃብሩ አጠገብ በተሰራው መስጊድ አማካይነት፣ ከግለሰቡ የተወሰነ ቦታ ተቆርሶ ለመስጊዱ ከመሰጠቱ ባሻገር፤ አቶ መኸዲ ለያዘው መሬት ህጋዊ ካርታ አግኝቶ ኑሮውን ሲገፋ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ተባለው ስፍራ በብዛት የሰፈሩ የስልጤ ማህበረሰብ ተወላጆች፤ “ቦታውን ለመስጊዱ እንፈልገዋለን፣ ለቀህ ውጣ” በማለት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ክርክር ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
ጉዳዩ በፍ/ቤት በተያዘበትና ውሳኔው ወደ ግለሰቡ እያደላ በመጣበት ወቅት፤ እነዚህ የተደራጁ አካላት አርብ በጁምአ ፅዳት ፕሮግራም፣ የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ጣራ ላይ በመውጣት ጣራውን ሙሉ በሙሉ በመገነጣጠል፣ ቤቱን ከማፈራረስ በተጨማሪ፤ አቶ መኸዲ ሽፋን በገጀራ፣ በዱላና በድንጋይ ክፉኛ ደብድበውታል፡፡
በአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም በፀጥታ ኃይሎች ትብብር ሕይወቱ መትረፍ የቻለውና የሶስት ልጆች አባት የሆነው አቶ መኸዲ ሽፋ በተደረገለት ሕክምና ሕይወቱ ቢተርፍም፣ ጥቃቱን ያደረሱት ወገኖች አስቀድመው በፀጥታ አደፍራሽነት ክስ በመመስረታቸው በአሁኑ ሰዓት ሾላ በሚገኘው የካ/ክ/ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ መሆኑን በስፍራው የተገኘው ሪፖርተራችን ዘግቧል፡፡