ቅዱስ ሲኖዶስ በደቡብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት ኃላፊ ብፁዕ አባ ያዕቆብን ከስራ አገደ

ቅዱስ ሲኖዶስ በደቡብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት ኃላፊ ብፁዕ አባ ያዕቆብን ከስራ አገደ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለሁለት ሳምንታት ስብሰባ የተቀመጠው ቅዱስ ሲኖዶስ ብፁዕ አባ ያዕቆብን ከደቡብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት አግዷል፡፡ በደቡብ አፍሪቃ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር መፈራረስ፣ ለምእመናን መከፋፈልና ነፍስ መጥፋት፣ ለሀብት ብክነትና ምዝበራ ተጠያቂ ናቸው የተባሉት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አባ ያዕቆብ፣ እስከ መጪው ጥቅምት ምልአተ ጉባኤ ወደ ሀገረ ስብከቱ እንዳይሔዱ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰሞነኛ ጉባዔው አግዷል፡፡

በሊቀ ጳጳሱ ላይ እገዱ የተላለፈው ቅዱስ ሲኖዶ፣ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ የቀትር በፊት ውሎው ላይ ነው በአጣሪ ኮሚቴው በቀረበለት ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ ነው፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ከሀገረ ስብከቱ ታግደው የተመለሱት ሊቀ ጳጳሱ፣ የቀደመ ጥፋታቸውን ከማረም ይልቅ ብልሽታቸው እየተባባሰ እንደ ሄደ ተገልጿል:: ጳጳሱ ይቀጥሉ ቢባል የምእመናኑ መከፋፈል፤ የሰርጎ ገቦች ጣልቃ ገብነት እየከፋ በመሄዱ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ፣ ለምልአተ ጉባኤው አባላት ባሠራጩትና በንባብ ባሰሙት ምላሽ፣ የሪፖርቱን ግኝቶች በሙሉ አስተባብለዋል፡፡ በቃል በሰጡትም ማብራሪያ፣ ቀደም ሲል በድረ ገጽ ከተብጠለጠሉበት ያልተለየ ሪፖርት እንደኾነ በመጥቀስ ክሱን አጣጥለዋል:: “በጎ ሥራዬ አልታየልኝም፤” በማለት አከናወንኩ ያሏቸውን ተግባራትም በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡

“በኀጢአት ከማንም አልበልጥም፤ በጽድቅም ከማንም አልበልጥም” በማለት ጉዳያቸው ከታየላቸው አባቶች ተለይተው፣ ከሀገረ ስብከቱ መዛወር እንደማይፈልጉ መልእክት ያስተላለፉበትን የሚመስል አስተያየትም አክለዋል፡፡

በስብሰባው ሥነ ሥርዓት መሠረት የልዑካኑን ሪፖርትና የሊቀ ጳጳሱን ምላሽ በቅደም ተከተል ጉባኤው አድምጧል:: ብፁዕ አባ ያዕቆብ በውጭ እንዲቆዩ በማድረግ በተካሄደው ውይይት የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ በአሉታዊ ነገሮች ላይ ያተኮረና የተሠሩ ሥራዎችን ያላካተተ ሪፖርት ነው በሚል ሊቀ ጳጳሱን ደግፈው በረጅሙ የተናገሩ እንዳሉ ኹሉ፣ “ሀገረ ስብከቱ በኹሉም ነገር ተጎድቷል፤ በአግባቡ አልተዋቀረም፤ ሕጉ ተጠብቆ ሳይኾን በዘፈቀደና በሊቀ ጳጳሱ ውሳኔ ብቻ ነው እየተሠራ ያለው” በማለት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያሰሙት የቆዩትን እውነታ ማንጸባረቁን የተናገሩ ብፁዓን አባቶችም ነበሩ፡፡

ከሪፖርቱና ውይይቱ በመነሣት፣ ሊቀ ጳጳሱ በሀገረ ስብከቱ መቀጠል እንደሌለባቸው አጠቃላይ መግባባት መፈጠሩን ለመረዳት ተችሏል:: የሚበዙት አባቶች አስተያየት፣ “ከጅምሩ ያጠፉት ነገር ስላለ የሚያስቀጥላቸው አይደለም፤ መዳን አይችሉም፤” የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል በሪፖርቱ አሉታዊው ነገር አመዝኗል፤ አንድ አቅጣጫ ብቻ ነው፤ እዚያው ተመልሰው እየሠሩ ይጠየቁ፤ ጉዳያቸውን ይከታተሉ፤ በሚሉ አባቶች ግፊት ውሳኔው ለጊዜው ወደ እግድ ተለውጧል፡፡

LEAVE A REPLY