ሊያነቧችው የሚገቡ የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች

ሊያነቧችው የሚገቡ የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች

በአፍሪካ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በኢተዮጰያ እንዲከፈት በዋሽንግተን ምክክር ተደረገ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ኂሩት ወልደማርያም በተገኙበት ኢትዮጵያ ውስጥ በአፍሪካ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ እንዲከፈት ለማድረግ፣ በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ትናንት ሰኔ2ቀን 2011ዓ.ም ምክክር ተደረገ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ስለአፍሪካ ተራማጅ ሀሳቦች የሚፈልቁበት፣ አፍሪካዊነት የሚቀነቀንበት እና የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ታስቦ የሚቋቋም ነው:: ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ እንዲመሰረት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ኂሩት ወልደማሪያምና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋና ለዳያስፖራ ተወካዮች ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲውን ተግባራዊ ለማድረግ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ዜናው አመላክቷል:: ይህም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ፣ በምርምር እና ባካበቱት ልምድ ለአገራቸው አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ለቀረበላቸው ጥሪ ተግባራዊ ማሳያ ዕድልና የፈጠረ ነው ብሏል፡፡

በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምድር ባቡርና ኤልፓ ውዝግብ ውስጥ ገቡ

የተጠናቀቁ የባቡር ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ለማስገባት የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር ችግር እየፈጠረበት መሆኑን የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡

ምድር ባቡር ስራዎቼን በአግባቡ ባጠናቅቅም ሙሉ ለሙሉ ፕሮጀክቴ የተሳካ እንዳይሆን የኤሌክትሪክ ኃይል እክል ፈጥሮብኛል ማለቱን ተከትሎ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ “ኮርፖሬሽኑ ለመሠረተ ልማት የሚያስፈልገውን ክፍያ ባለመፈጸሙ የተፈጠረ ችግር መሆኑ ይታወቅልኝ” ብሏል፡፡

ግንባታቸው ከ97 በመቶ በላይ የደረሱት የአዋሽ ኮምቦልቻ፣ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት እየተጠናቀቀ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ፣ የሙከራ ጉዞ ለማድረግ አለመቻሉን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ ደረጃ ገለጻ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራው ይህ የባቡር ፕሮጀክት 392 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ነው:: መስመሩ ባለ አንድ ነጠላ ሀዲድ እና 1ነጥብ 435 ሜ. ስታንዳርድ ጌጅ ስፋት ያለው ፕሮጀክት ሥራውን ሙሉ ለሙሉ እያጠናቀቀ ይገኛል:: ባቡሮችን ሞክሮና ርክክብ አድርጎ ወደሥራ ለማስገባት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር በፕሮጀክቱ ላይ ችግር መፍጠሩን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባለ ኮከብ ሆቴሎች ባለሙያዎችን የመቅጠር ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ነው

በከፍተኛ ደረጃ አዲስ አበባን ጨምሮ የዘመናዊ ሆቴሎች ግንባታ ቢስፋፋም፣ በአገራችን የሚገኙ ባለኮከብ ሆቴሎች በዘርፉ የሰለጠኑ ምሩቃንን ቀጥሮ የማሰራት ፍላጎታቸው በጣም አነስተኛ መሆኑ ተነገረ::

የኢትዮጵያ የሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በአገራችን ያሉትና ከባለ አንድ እስከ ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዓለምአቀፍ ሆቴሎች በዘርፉ የሰለጠኑ የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎችን ቀጥረው ከማሰራት ይልቅ ምንም ከሙያው ጋር ዕውቀት የሌላቸው ሰዎችን መጠቀም እንደሚሹ አስታውቀዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ባስጠናው ጥናት እንዳረጋገጠው ከሆነ አገሪቱ ከባለ አንድ እስከ ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሆቴሎች ውስጥ በሥራ ላይ ከተሰማሩት ሠራተኞቻቸው መካከል በዘርፉ የሰለጠኑት 23 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ ዘርፉ በፍጥነት ሊያድግ የሚችልበትን ዕድል ሊያቀጭጨው ይችላል ተብሏል፡፡ የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽኖች እንዲዋሃዱ ተጠየቀ፣ በግል ት/ቤቶች ጥራት ላይም ውይይት ተጀምሯል፡፡

የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽኖች እንዲዋሃዱና ለአንድ ዓላማ እንዲሰሩ ጥያቄ መቅረቡ ተሰማ፡፡ 

የተለያየ የአሰሪ ኮንፌዴሬሽን ሆኖ መሥራት አስቸጋሪ እንደሚሆንና በተለያየ ኮንፌዴሬሽን የሚነሳው ጉዳይም የተበታተነ ስለሚሆን የሠራተኛው ተወካይ የሚሰጠው ምላሽ ለሕዝብም ሆነ ለኮንፌዴሬሽኖች አጥጋቢ እንደማይሆን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር ተናገሩ፡፡ ትልቅ ሥራ መሥራት የሚቻለው በአንድነትና በመተባበር ብቻ ነው ብለዋልየኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት፡፡

በሌላ ዜና በግል ትምህርት ቤቶች ያለውን ትምህርት አሰጣጥና ጥራት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ መንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡

በኤድቬት አዲስ አማካይነት ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የግል ት/ቤቶች ኤግዚቢሽን ላይ የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው በመስራት የትምህርት ጥራት እንዲመጣ መስራት እንዳለባቸው ተግልጿል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ በግል ትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን የትምህርት አሰጣጥና ጥራት ደረጃ ለማወቅ አላማ ያደረገ ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱ ጠቀሜታ አለው ተብሏል፡፡

አ/አ ፖሊስ፣ ኦሮሚያ ፖሊስና ፌደራል ፖሊስ በጋራ የሚሰሩበትን ዕቅድ ነደፉ

በኢንጅነር ታከለ ኡማ ሰብሳቢነት የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የኦሮሚያ ፖሊስ ተወካዮች በአዲስ አበባ ከተማ እየታዩ ያሉ የወንጀል ድርጊቶችን ለመካላከል ዛሬ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡

ተሰብሳቢዎቹ በዚሁ ጊዜ በጋራ ግብረ ሃይል በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በጥናት ላይ የተመሰረተ የወንጀል መከላከል እርምጃ ለመውስድ የሚያስችል ስልት ለመንደፍና በቅንጅት ወደ እርምጃ ለመግባት ተስማምተዋል ነው የተባለው።

በጊዜያዊው ከንቲባ የሚመራው ግብረ ሃይሉ በተለይ በከተማዋ እየሰፋ የመጣውን የሞተር ሳይክል ቅሚያና ሌሎች በተናጠልና በቡድን የሚፈፀሙ የተደራጁ ወንጀሎችን በመቅጨት የከተማውን ነዋሪ ደህንነት የማረጋገጥ ሃላፊነት እንደተሰጠው ተነግሯል፡፡

በአዲስ አበቤ ብዙም ተደማጭነት ማግኘት ያቃታቸው ታከለ ኡማ ከወንጀል መከላከል ጋር
እየወሰዱ ያሉት ዕርምጃ የሚደገፍ መሆኑን አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል:: በሌላ በኩል በኦነግ አቀባበል ጋር በቄሮ ስም በከተማዋ መንገዶች ላይ ቀለም ሲቀባና በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካድረሰ ቡድን ነጥሎ ወደ ጦላይ እንዲላክ ትልቁን ሚና የተጫወተው የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕግን በአግባቡ ያስከብራል ማለት አዳጋች እንደሆነ አስተያየት የሚሰጡ አልታጡም፡፡

 

LEAVE A REPLY