ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የግዕዝ ቋንቋ የክርስትና ሀይማኖትን ተቀበለ እንጂ፣ የክርስትና ሀይማኖት የግዕዝ ቋንቋን እንዳልተቀበለ ተገለጸ:: ከክርስትና እምነት በፊት ግዕዝ የኢትዮጵያ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር ጥናቶች አመላክተዋል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ በሚገኘው አምስተኛው አገር አቀፍ የግዕዝ ጉባኤ “ግዕዝና ስነፈውስ”፣ “ግዕዝና ለፈውስ የሚደረግ ፀሎት”፣ “ግዕዝና የባህል መድሀኒት”፣ “ፀበልና ማየ ፀሎት” “በግዕዝ ባህል ወፊዚክስ” የሚሉና ተያያዥ የሆኑ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በእነዚህ ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ እንደተጠቀሰው ግዕዝ የመድኃኒት እና የህክምና ፅሁፎች የተከማቹበት፣ የፈውስ ጥበቦችና የመድሀኒት ቅመማና አጠቃቀም ጥበብም የተከማቸበት ቢሆንም፤ በልሳነ ግዕዝ ውስጥ ያለውን የፈውስ ጥበብ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም ተብሏል፡፡
የግዕዝ ሀብቶቻችንን ከኢትዮጵያ ወደ ሀገራቸው ዘርፈው የወሰዱ የተለያዩ ሀገራት ከእኛ የበለጠ በሀብቶቹ እንደተጠቀሙባቸውም በጉባኤው ተብራርቷል:: ቋንቋውን ከእምነት ጋር የማያያዝ ጉዳይን በተመለከተ፤ግዕዝ ክርስትናን ተቀበለ እንጂ ክርስትና ግዕዝን አልተቀበለም:: ከክርስትና እምነት በፊት ግዕዝ የሀገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር ጠናቶቹ ይፋ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የግዕዝ ቋንቋን ከመጥፋት እንደታደገች ያሳየው ጥናት፣ በግዕዝ ቀደምት እውቀት የተፃፈ ቢሆንም የቋንቋው አዋቂዎች ግን ጥበቡን በተለያዩ መንገዶች ምስጢራዊ ስሞችን እየሰጡ ጭምር፤ ሚስጥሩ እንዳይታወቅ አድርገዋቸዋልም ብሏል።
የግዕዝ ሀብቶችን ለመጠቀምና ጥልቅ የሆነውን የእውቀት ክምችት ለመመርመር እያረጁ ያሉትን የግዕዝ መፅሀፍት መጠበቅና የብራና ፅሁፎችን ዲጂታላይዝ ማድረግ እንደመፍትሄ ቀርበዋል:: የግዕዝ ቋንቋ ትምህርትን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት መስክ እንዲሰጥ የተጀመረው ስራ አበረታች ቢሆንም፤ ትምህርቱን ያልጀመሩ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲጀምሩ ማድረግ ቋንቋውን ለማሳደግ አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑ ተመልክቷል።