ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ማስፋፊያ ፕሮጀክት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
ፕሮጀክቱ 270 የህፃናት አልጋ፣ የእናቶችና ህፃናት ህክምና መስጫ ማዕከል፣ በቀን 120 ሲሊንደር ማምረት የሚያስችል የኦክስጅን ማምረቻ ከማካተቱ በተጨማሪ፤ ሲቲ ስካን ማሽንና የመድኃኒት መሸጫን እንደያዘ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን ተናግረዋል፡፡
ሆስፒታሉን በተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የአደጋና ድንገተኛ ህክምና መስጫ ማዕከል፣ የዲያግኖስቲክስ እና አይሲቲ ማዕከል ግንባታ መሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ፕሮግራም ተካሂዷል:: በ400 ሚሊዮን ብር የተገነባው የደሴ ህብረ ህዋስ ዘር ማራቢያ ማዕከልም ሰኔ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዓመታት በፊት ግዙፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክት የተካሄበትና በህክምናው ዘርፍ ኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ወደፊት መራመዷን ያረጋግጣል፣ የተባለለት የወሎ ተርሸሪ አጠቃላይ ሆስፒታል ግንባታ ጉዳይ ከምን እንደደረሰ እስካሁን ድረስ ምንም የታወቀ ነገር የለም፡፡ በወቅቱ በርካታ ገንዘብ የተሰበሰቡለት፣ የወሎ ተርሸሪ ፕሮጀክት አሁን የደረሰበት ደረጃ በግልፅ አለመታወቁ በርካታ ሀገር ወዳዶችንና የከተማዋን ነዋሪ በስፋት እያነጋገረ ይገኛል፡፡