ኢትዮጵያ በወያኔ መዳፍ በጨለማ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ለዜጎች ነፃነት በመታገልና ለውጤትም ለማብቃት የኢሳትን ያህል ጉልህ ሚና የተጫወተ የለም ብላጋነንህ ብዬ አላፍርም። ኢሳትን የፀነሱት፣ የደገፉት፣ የተንከባከቡት ግለሰቦች ሆነ ድርጂቶች በስራቸው ሊኮሩ እንጂ ሊወቀሱበት አይገባም። በተለይም ግንባር ላይ ሆነው ጊዜአቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ የቤተሰባቸውንና እንደሌላው የመማርና ሃብት የማፍራት አቅማቸውን ሰውተው በመናኛ ክፍያ የታገሉትን ጋዜጠኞች የአንበሳውን ድርሻ የዕኔ ነው የሚል ካለ ከንቱ ነው። በአመራረጡ ሆነ በአሰራሩ ብዙ የሚታማው ቦርዱም ከነእንከኑ የአቅሙን ሰርቶ እዚህ ማድረሱ ቢያስመሰኘው እንጂ አያስወቅሰውም። ድርጅቶች፣ ግለሰቦች ሆነ ቡድኖች ለኢሳት ያደረጋችሁት ድጋፍ ለአገራችሁ እንዳበረከታችሁት በጎ ነገር መመልከት እንጂ የህዝብ ነው ያላችሁትን ተቋም በእውነትም የህዝብ እንዲሆን ከመትጋት ያለፈ አጀንዳ ሊኖራችሁ አይገባም።
ኢሳት ሲመሰረት ከነበረው አላማ ና አቅም በላይ ህዝባዊ ተቀባይነቱ ገዝፏል። አሁን ያገኘውን ድጋፍና ግዝፈት የሚሸከም ተቋማዊ አቅም ግን አልገነባም።ለዚያ ደግሞ የትግሉ ፍጥነትና መፋፋም ፋታ የነሳው ከመሆኑም በላይ መለወጡን የማይሹ የራሱ አካላትም አሉታዊ ድርሻ አላቸው። የአሁኑ መንገራገጭ በይደር ሲታለፍ የቆዬ ይዋል ይደር እንጂ መምጣቱ የማይቀር ነበር። የማይቀረው ስለመጣ ደግሞ ጣት መጠቋቆም አያስፈልግም። የድርሻ ድርሻችንን አንስተን ወደፊት መሄዱ ይሻላል።
እኒህ ከላይ የጠቀስኳቸው የኢሳት አንጓ አካላት ከነድክመታቸው በመተባበር ለአንድ አላማ ያደረጉት አስተዋፆ ያለችግር ወደፊት የመሄዱ ዋናው ምክንያት የህዝብና የነፃነት ጠላት የሆነው ወያኔ ፊታቸው ስለነበረወደ ልዩነታቸው ሳይሆን ወደ ጠላታቸው ማተኮራቸው የሚገባ ነበር። ተሳክቷልም።
የምሰጠውን ምሳሌ ይዘቱን እንጂ ነውሩንአትውሰዱብኝ። በመንደር ውስጥ ጅብ ሊያጠቃ ሲመጣውሾች ሁሉ በህብረት ጅብን ያባርራሉ። የጥቃታቸውኢላማ ጅብ ከመድረኩ ሲጠፋ በግል መናከሳቸው የታወቀ ነው። የህዝብና የኢሳት ባልደረቦች መሰረታዊጠላት ወያኔም ምሽጉ ገብቶ ሞቱን ይጠብቃል። እናምወደ ትንንሹ ልዩነታችን ገብቶ መነታረኩ የሚጠበቅ ነበር።
ኢሳት የዚህ ሁኔታ ሰለባ መሆኑ የኢትዮጵያን ህዝብ አድምቶታል። ኢሳት በዚህ ሁኔታ የማይዘልቅ መሆኑበቅርብ ለምንከታተለው ግልፅ ነበር። ተመልካቾች እንዳይፈርስ አደብ ገዝተን በሰቀቀን በዝምታ ስንቀመጥና “እባካችሁ በመነጋገር ፍቱት“ እያል ስንወተውት እያንዳንዳቸው ያለፈ ስህተታቸውን ለመሸፈን፣ ከሁሉ የበለጠ አስተዋፆ አድርጌያለሁ በሚልመታበይ ከፍተኛ ግዳይ ሽሚያ ውስጥ በመሆን፣ በተዘዋዋሪም ሚድያውን ለመቆጣጠር፣ እያልን ልንዘረዝረው በምንችለው ማለቂያ የሌለው የግልናየቡድን ፍላጎት ምክንያት ትዕግስት በማጣታቸው እዚህደርሷል። እከሌ ጥፋተኛ ነው ፣ እከሌ ትክክል ነው ማለት አሁን ዋጋ የለውም። ከሁለቱም ወገንና ከቦርዱየሚደረገው መፍጨርጨርም ራስን ንፁህ ለማድረግ እንደ ጲላጦስ እጅ ከመታጠብ የተለየ አይደለም። የሁሉም ስራ በህዝብ ልቦና ውስጥ ተቀምጧል። ወንድሜ ዳዊት ከበደ ወይሳ እንዳለው እንደአባቶቻችን “የሞትነውም እኛ ያለነውም እኛ“ እንበልና ደንጋይ መወራወሩን አቁመን ከልብም ይሁን ለማስመሰል እናገለግላለን ያልነውን ህዝብ በስራችን እንካስ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ኢሳትን ሲረዳ ከሁዋላው ያሉትን ፖለቲከኞች፣ ከውስጡ ያሉትን ጋዜጠኞች በአስተዋፆአቸው ብቻ እየመዘነ እንጂ በትናንት ማንነታቸው አልነበረም። የነገ አካሄዳቸውንም በእለት ተእለት ስራቸው ለመመዘን እንጂ ጭፍን ዋስትና ይዞ አይደለም።
በኢሳት ውስጥ የቀራችሁትም፣ ከኢሳት የወጣችሁትም ከአሁን በኋላ የምትመዘኑት በስራችሁ እንጂ በገባችሁት ቃል አይደለም። ከሁሉ በላይ የህዝቡን የማመዛዘን ክህሎት የሚፈታተን ራስን ንፁህ ለማድረግ የምታደርጉት መሯሯጥ ህዝባቂ ድጋፉን ይቀንስባችሁ እንደሆነ እንጂ አይጨምርላችሁም። ስትከባበሩ ህዝቡን እንዳከበራችሁ ይቆጠራል። ሌላ ላይ ጭቃ የሚወረውር መዳፍ ምን ጊዜም ንፁህ አይሆንም። በህዝቡ ድጋፍያገኛችሁትን ተሰሚነትና ከበሬታ ቁሻሻ ላይ አትጣሉት።
በያላችሁበት ስራችሁን በከበሬታ ከሰራችሁ ህዝቡ ከእናንተ ጋር ነው። ድጋፍ የምታገኙት በድካማችሁ እንጂ በቃል ማሳመር አይሆንም። በርቱ፣ ልቦና ይስጣችሁ።
አክባሪያችሁ