ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነትን በተግባቦትና ህዝብ ግንኙነት ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ፎረም መቋቋሙ ተሰማ፡፡
በቃል ኪዳኑ መሰረት ስርዓተ ምግብ እና ጤናን በማሻሻል ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃ የሚገኘውን የመቀንጨር ችግር ለመቅረፍ እንደሚረዳ ተገልጿል:: ስምምነቱ በ2022 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚደረገውን ሐገራዊ ጥረት በተግባቦት እና ህዝብ ግንኙነት ስራዎች ለማገዝ ያለመ ስምምነት ነው ተብሏል።
የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት በተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በቅንጅት እየተሰራበት መሆኑን አስረድተዋል:: የቃል ኪዳኑን ግብ ከዳር ለማድረስ፣ በምግብና በስርዓተ ምግብ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ጭምር የተግባቦትና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመቀንጨር ችግር በሀገር ደረጃ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስና የባህሪ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ጠንካራ የተግባቦት ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ መከወን እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡