አዲስ አበባን የኮሌራ ክፉኛ ያሰጋታል : ኢቦላ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በቦሌ ኤርፖርት ቁጥጥር...

አዲስ አበባን የኮሌራ ክፉኛ ያሰጋታል : ኢቦላ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በቦሌ ኤርፖርት ቁጥጥር ተጀመረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ አራት ክልሎች 614 ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬተር ዶክተር በየነ ሞገስ የበሽታውን ስርጭት አስመልክተው በዛሬው ዕለት ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መከሰቱን የጠቆሙት ዶ/ር በየነ በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ 614 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን አምስት ወረዳዎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰንዳፋ ከተማ በአጠቃላይ 294 ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በአጠቃላይ 198 የሚሆኑ ሰዎች በኮሌራ ሲያዙ፣ 14 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ህይወታቸው አልፏል።

በሶማሌ ክልል 33 ሰዎች፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል ደግሞ 18 የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ9 ክፍለ ከተሞች 70 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ እንደተያዙ ከመግለጫው መረዳት ተችሏል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አንድ ሰው በበሽታው መያዙ በተደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በሽታውን ለመቆጣጠርም ናሙናዎችን በጥናት በመለየትና በላቦራቶሪ በማረጋገጥ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመድሃኒትና የህክምና ግብዓት አቅርቦት እየተሰራጨ ቢሆንም ሕብረተሰቡም ጤናውን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በአዲስ አበባ ከሃይማኖት ተቋማትና ከአ/አ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ለመጀመር ስምምነት ላይ መደረሱን የጠቆሙት ዶክተር በየነ ሞገስ፤ ከነገው ዕለት ጀምሮ በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከ17 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በሁለት ዙር በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና የኢቦላ ወረርሽ በሁለት የአፍሪካ አገራት መከሰቱን ተከትሎ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ከመግለጫው መረዳት ተችሏል፡፡

በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተጓዦችን የሰውነት ሙቀት መጠን የመለየት ስራ እየተከናወነ ሲሆን፣ በአውሮፕላን ማረፊያው በበሽታው የተያዙ መንገደኞች ቢያጋጥሙ ለይቶ ለማከም የሚያስችል ቦታ ተዘጋጅቷል:: በቦሌ ጨፌ የኢቦላ ለይቶ ማከሚያ ማዕከል ተዘጋጅቶ ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁም ይፋ ተደርጓል፡፡

LEAVE A REPLY