ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አባት የአቶ አሕመድ ዓሊ አስከሬን ትናንት ማምሻውን ከመኖሪያ ከተማቸው በሻሻ ገብቷል፡፡ “አባፊጣ“ በተሰኘ ቅጽል ስም የሚጠሩት የአቶ አሕመድ አስከሬን አስራ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ገደማ በሻሻ ሲደርስ፣ በርካታ የከተማው ነዋሪ ሀዘኑን በመግለጽ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡
ያጋጠማቸውን ሕመም በጅማ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል በሕክምና ሲከታተሉ የቆዩት “አባፊጣ” ትናንት እኩለ ቀን በኋላ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው፡፡
ከግንቦት 29 ጀምሮ ለ12 ቀናት በሆስፒታሉ የጽኑ ህሙማን ክፍል ህክምና ሲደረግላቸው የቆዩት አቶ አሕመድ በአዲስ አበባ በሌላ የህክምና ተቋም ቆይተው ሲመለሱ ነበር ጅማ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የገቡት፡፡ “በፊትም እኛ ጋር ሲታከሙ ነበር። ከዚያ ወደ አዲስ አበባ ሄደው በሌላ የህክምና ተቋም ሲታከሙ ነበር። ከዛ ተመልሰው ሲመጡ የዕድሜም ነገር ስላለ ከእርሱ ጋር ሁኔታቸው ተባብሶ ነበር” ሲሉ የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ኢሳስ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
የአቶ አህመድ ዓሊ “አባፊጣ” አስከሬን ከጅማ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ሲሸኝ፣ በርከት ያሉ የከተማይቱ ነዋሪዎች በመኪና አጅበውታል። አስክሬናቸው ከጅማ ከተማ 63 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ወዳለው የመኖሪያ ከተማቸው በሻሻ ሲደርስም፣ የከተማይቱ በርካታ ነዋሪ በሀዘንና በልቅሶ እንደተቀበለው ለማወቅ ተችሏል፡፡