ጣሊያን በኢትዮጵያ የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ የማገዝ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች
ኢትዮጵያ ውስጥ በቀጣይ የሚካሄደውን ምርጫ የጣልያን መንግስት ለመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ተገለጽ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በዛሬው ዕለት ከጣልያን ምክትል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኢማኑኤል ሲ ዴል ሪ ጋር ተገኛኝተው ተወያይተዋል።
በውይይቱ የሚቀጥለውን ምርጫ አስመልክቶ በጣልያን መንግስት እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መካከል ሊኖር ስለሚችለው ትብብር ዙሪያ መክረዋል፡፡
ሚኒስትሯ የጣልያን መንግስት ከሚቀጥለው ሀገራዊ ምርጫ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ለመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የገለጹ ሲሆን፣ በተያዘም የአክሱም ሐውልትን ለመጎብኘትና የእድሳቱን ዝርዝር አሠራርን ለመምከር የመጣው ልዑክ በዛሬው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል።
ከጎዴ ወደ ጅግጅጋ ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ አደጋ የአምስት ሰዎች ሕይወት አለፈ
ከጎዴ ወደ ጅግጅጋ ሲጓዝ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ አደጋ የአምስት ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡ ሕይወታቸው ካለፈው አምስት ሰዎች በተጨማሪ 23 ሰዎች ላይም ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የሶማሌ ክልል ፖሊስ አስታውቋል። ተሽከርካሪው 28 መንገደኞችን አሳፍሮ ይጓዝ እንደነበርም ነው ፖሊስ የገለጸው።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ክፍል የተሽከርካሪ አደጋ ምርመራ ቡድን መሪ ኢንስፔክተር አህመድ ኑር ፣ አደጋው ትናንት ጠዋት ሰኔ13 ቀ በግምት 12፡30 ሰዓት አካባቢ እንደደረሰ፣ ተሽከርካሪው 28 ሰዎችን አሳፍሮ ከጎዴ ወደ ጅግጅጋ ከተማ በመጓዝ ላይ እንዳለ መገልበጡን ተናግረዋል፡፡
ተሽከርካሪው በጠመዝማዛ መንገድ በፍጥነት በመጓዝ ላይ እያለ ድንገት ከመንገድ በመውጣቱ አደጋው የደረሰ ሲሆን፣ተጎጅዎቹ በጅግጅጋና በጎዴ ሆስፒታሎች የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑም ታውቋል፡፡
ም/ጠ/ሚ/ር_አቶ_ደመቀ_መኮንንና አገልጋይ ዮናታን ተገናኝተው ተወያዩ
የኢፌዲሪ ም/ጠ/ሚ/ር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ለአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ እና ባለቤቱ ዶኢ እምሩ አቀባበል በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አነጋግረዋቸዋል፡፡
ከፊታችን ሐምሌ 8/2011 በሐዋሳ ከተማ ለሶስተኛ ጊዜ ፣ለሰላሳ ሺ(30.000) ወጣቶች በሚሰጠው” የመልካም ወጣት” ስልጠና መርሃ ግብር ዙርያ ጥሩ ቆይታ እና ውይይት እንዳደረጉ ነው የወጡት ዜናዎች የሚያመላክቱት፡፡
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉና ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በውይይታቸው ላይ በሃገራዊ የለውጥ ጉዞ፣ ግብረገባዊ ስብእና የሰነቀ እና ህብረ ዘርፋዊ ሽግግርን የሚያረጋግጥ ክህሎትን የታጠቀ ወጣት ትውልድ መገንባት ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም በ”እሽሩሩ የስልጠና ማዕከል” በተሰሩ ስራዎች፤ ሊሰሩ በታሰቡ እቅዶች ላይ የነበረው ውይይት መልካም እና የተሰካለትም ነው ተብሏል፡፡
“ በዚህ ተምሳሌታዊ ተልእኮ ባነገበ ጅምር ጥረት አማካይነት አገሪቱ እልፍ ዮናታኖችን ትሻለች” ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን ለወጣቱ ትውልድ የለውጥ አምሮት እና ለዮናታን ትውልድ ተሸጋሪ ራዕይ ስኬት መንግስት ተገቢውን ድጋፍ በቅርበት ያደርጋል ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡
ድምጻዊ ኤሌሞ አሊ ከ37 አመት በኋላ ወደ አገሩ ተመለሰ
በአሮምኛ ዘፈኖቹ በማሕበረሰቡ ዘንድ በእጅጉ የሚታወቀው አርቲስት ኤሌሞ አሊ ከ37 አመት የስደት ሕይወት በኋላ ወደ አገሩ ተመልሷል።
በ1974 ዓም ኢትዮጰያ ውስጥ በነበረው ፖለቲካ ችግር አገሩን ለቆ ለመውጣት የተገደደው ድምጻዊ ኤሌሞ ዓሊ፣ በ1983 የተደረገውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ተመልሶ ቢመጣም የወያኔን ስርዓት በመቃወም ዳግመኛ አገሩን ለቆ ለመሄድ መገደዱን ዛሬ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተደረገለት አቀባበል ላይ ለነበሩ ጋዜጠኞች ተናግሯል።
በ አሜሪካ፣ ጣሊያንና ካናዳ እንዲሁም በሳዑዲ አረቢያ በስደት የኖረው አርቲስት ኤሌሞ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ያለው ለውጥ በእጅጉ ስላስደሰተው ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን አስታውቋል፡፡
በድምጻዊ ኤሌሞ ዓሊ አቀባበል ስነ ስርዓት ላይ የኦ.ዴ.ፓ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ታዬ ደንዳ፣ “እንደ ኤሌሞ ያሉ አርቲስቶች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የሚደረገው ለኦሮሞ ህዝብ ትግል በነበራቸው አስተዋጾ ነው። በቀጣይ አርቲስቶች ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዟር በስራዎቻቸው ሊያግዙን ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኮካ ኮላ ፋብሪካ በ2 ቢሊየን ብር አራተኛ የፋብሪካ ግንባታውን በይፋ አስጀመረ
የግዙፉ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒ አካል የሆነው የኮካ ኮላ ፋብሪካ፣ በኢትዮጵያ አራተኛና ትልቅ ፋብሪካውን በሰበታ ከተማ ለመክፈት፣ በ2 ቢሊየን ብር የግንባታ ፕሮጀክቱን በይፋ አስጀመረ፡፡
ካምፓኒው ከሰበታ ከተማ በተረከበው 14 ነጥብ ሦስት ሄክታር መሬት ላይ፣ በኢትዮጵያ ትልቁን የኮካ ኮላ ፋብሪካ ለመክፈት የግንባታ ሥራው መጀመሩን ባበሰረበት ፕሮግራም ግንባታው በሁለት ምዕራፍ እንደሚጠናቀቅ ጠቁሟል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ የፕላስቲክ መጠጦች ፋብሪካ ግንባታ የሚከናወን ሲሆን፤ በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የጠርሙስ መጠጦች ፋብሪካ የሚገነባ ይሆናል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በ2 ቢሊየን ብር ሲገነቡ ለአንድ ሺ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሏል፡፡