ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ታዋቂው ፖለቲከኛና የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊ/መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር ከተማና እንዲሁም በአዲስ አበባ የተደረገው የባለስልጣናቱ ግድያ አገሪቱ ያለችበትን ችግር በግልፅ ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
ፕ/ር መረራ ጉዲና ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሕዝብ በመንግስት ላይ ቅሬታ ካለው፣ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት እየበደለኝ ነው ካለ፣ አልያም እያገለገለኝ አይደለም ብሎ ካመነ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ትልልቅ ከፍተቶች ከተፈጠሩ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ለማድረግ የሚነሳሳ ኃይልም ሊኖር እንደሚችል ገልፀዋል፡፡
“የሕዝብን ጥያቄ በመፈንቅለ መንግስት እንመልሳለን ብለው የሚነሱ ኃይሎች ለሚያደርሱት ጥፋት በቂ ምክንያት አላቸው ወይስ የላቸውም? የሚለውን መመለስ ያለባቸው ራሳቸው ናቸው” ያሉት ፕ/ር መረራ ጉዲና “በአጠቃላይ ሰሞኑን የተፈፀመው ተግባር በአገሪቱ ውስጥ ችግር መኖሩን በግልፅ ያመላከተ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙበት አንዱ መንገድ ምርጫ እንደሆነ የጠቆሙት ፕ/ር መረራ ጉዲና “ይህ መንግስት አይወክለኝም ለሚሉ ወገኖችም ምርጫ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ብቸኛ መፍትሄውም ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ ነው፡፡” ሲሉ ሀሳባቸውን በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡