የዜግነት ፖለቲካ፣ ልደቱ እና ብርሃኑ || አቤል ዋበላ

የዜግነት ፖለቲካ፣ ልደቱ እና ብርሃኑ || አቤል ዋበላ

በመጀመሪያ ምርጫ ዘጠና ሰባት ነበር፡፡

መለስ ዜናዊ(ነ.አ.) በስልጣን ላይ ነበር፡፡ እጅግ ከመመካቱ የተነሳ እንከን የለሽ ምርጫ እንደሚያካሄድ ተናገረ፡፡ ፈረንጅም ሀበሻም አመነው፡፡ ዜጎች ዘር ቀለም ሳይለዩ ኢህአዴግን እና የዘር ፖለቲካው ለመጣል ተንቀሳቀሱ፡፡ ብዙ ቅን የሀገር ልጆች ከፊትም ከኋላም ተሰለፉ፡፡ ከፊት የተሰለፉት ጉመቱዎች ሆደ ሰፊው የየዛኔው ዶክተር የአሁኑ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መራው፡፡ ልደቱ የዚህ ስብሰብ አንዱ አንጸባራቂ ኮከብ ነበር፡፡

እኔ ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ ክርክር ምናምን ሰማኹ፡፡ አንዳንድ ኢንተርቪዎችን አነበብኩኝ፡፡ ኢህአዴግ ያደግንበት ሰፈር ቤቶች አፈረሰ፡፡ የቅንጀቱ መሪ ብርሃኑ ነጋ እኛ ሰፈር መጣ፡፡ አይዟችኹ ትንሽ ታገሱ አለ፡፡ ልጆቻቸውን የተማሪ ቤት ዩኒፎርም እና ባንዲራ ያለበሱ እናቶች በዚህ ንግግር ተጽናኑ፡፡ የልደቱ ምክንያታዊ ክርክሮች ኢህአዴግን ክፉኛ አቆሰሉት፡፡ “ልደቱ ለወጣቱ” ተባለ:: በጃ ያስተሰርያል መንፈስ ሁላችንም ተጠመቅን፡፡ ከኢህአዴጋውያን በቀር አንዳች እንኳን የተረፈ አልነበረም፡፡

የጃ ያስተሰርያል መንፈስ የይቅርታ መንፈስ ነበር፡፡ ወደፊት ማየት ነበር፡፡ መሻገር ነበር፡፡ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርኣት መተላለፍ ነበር፡፡ የፖለቲካ ስልጣንን መቆጣጠሪያ ልጓም ማበጀት ነበር፡፡ ዘረኝነት እና እና ኢህአዴግን መቅበር ነበር፡፡ ተስፋው ነጻነት፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት ነበር፡፡

ነበር፡፡

ነ.አ.* ለኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ያለው ጥላቻ ላይ የስልጣን ጥማት ተደምሮበት ያን ሁሉ ተስፋ ቀበረው፡፡ ደም ፈሰሰ፡፡ እኛ መንደር በጥይት ተመተው የሞቱትን እትዬ ዙልፋን ጨምሮ ብዙ ንጹሃን ዜጎች ለሀገር ባለቤትነት ተሰው፡፡ እነ ብርሃኑ፣ እነ ፕሮፍ መስፍን ወደ ወህኒ ሲወርዱ ልደቱ ወደ ፓርላማ ገባ፡፡

ይህ ሂደት ለኔ ብርሃኑ እስከመጨረሻው ደቂቃ ከህዝብ ጋር እንደነበር ምስክር ሆነኝ፡፡ ልደቱም ህዝብን ከድቷል ብዬ ደመደምኩኝ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ልደቱ ሁለት፣ ብርሃኑ አንድ ሌሎች በርካታ ጽሐፊያን ደግሞ ብዙ መጽሐፍት አዘጋጅተዋል፡፡ አብዛኞቹ ጸሐፍት ታሪኩን ከመተረክ ባሻገር ለከሸፈው ዕድል ምክንያቱ ምንድን ነው? የቱ ጋር ነው የተሳሳትነው? ጥፋተኛው ማን ነው? የሚለውን ለመመለስ ሞክረዋል፡፡ ከዚህ ንባቤ በዋናነት የተረዳኹት የኢህአዴግን እብሪት እና ውንብድና ነው፡፡ ከዚያ በመለስ ተስፋው እንዲወለድ ከደከሙት መሀል ብዙዎቹ በመግደሉ ሂደትም ይብዛም ይነስም ሱታፌ እንደነበራቸው ነው፡፡ ልደቱ ግን በዚያ አስጨናቂ ወቅት ከህዝብ ጋር አልነበረም፡፡ ብዙዎች በለጋስነት ከብልሃት እና አስተዋይነት ለማያያዝ ይሞክራሉ፡፡ እኔ ግን እንደ ብዙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ክህደት እለዋለኹ፡፡

ብርሃኑ ከእስር ቤትም ከሀገርም ቤት ወጣ፡፡ ግንቦት ሠባት የሚባል ድርጅት አቆመ፡፡ ሆደ ሰፊው ብርሃኑ ኢህአዴግን በማንኛውም መንገድ ለመጣል መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ኢህአዴግ እንዲወድቅ የጸና ፍላጎት ቢኖረኝም ከማንኛውም መንገዶች አንዱ የትጥቅ ትግል ስለነበር የጉልበት/የኃይል ሰው አይደለኹም ብዬ ስለማምን ከብርሃኑ ጋር ተለያየን፡፡ ነገር ግን ከዚህ በኋላም ቢሆን የብርሃኑ ሀሳቦች አድናቂነቴን አልተውኩም፡፡ የሚሰጣቸውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ትንተናዎች በታላቅ ጉጉት እንደብርቱ ተማሪ ከኢንተርኔት እያደንኩኝ እከታተል ነበር፡፡

በግንቦት ሰባት ከአንዳርጋቸው ጋር መቀናጀታቸው ደግሞ የበለጠ እንዳከብራቸው አድርጎኛል፡፡ ምንም እንኳን የትግል ስልታቸውን ባላምንበትም ለህዝብ እንደመከታ ለጠላት እንደማስፈራሪያ መቀመጣቸውን የሚጠላ አንጀት አልነበረኝም፡፡

ባንድ ወቅት አንድ አሜሪካ አገር የምትኖር ወዳጄን ሌሎች ብርሃኑን የሚያውቁ ሰዎች ከእርሷ ጋር ሲያተዋውቁት ሶሻል ሚዲያ ላይ ያላትን ሱታፌ ሲነግሩት ዞን ዘጠኝ ነች ብሎ መጠየቁን የሰማኹ ዕለት የነበረኝ ደስታ ወደር አልነበረም፡፡ ትንሿ ሙከራ የታላቁ ሰው ጆሮ መድረሷ ታላቅ ፈንጠዝያን ፈጥሮ ነበር፡፡ እዚህ ምስራቅ አፍሪካ፡፡

እኔም የዜግነት ወግ ደርሶኝ እስር ቤት ገባኹ፡፡ ደናቁርቱ የፌደራል ፖሊስ መርማሪዎች (አሁንም ብዙ መሻሻል ያሳዩ አይመስለኝም፡፡) ከነብርሃኑ ድርጅት ጋር ያለንን/ ያለኝን ግንኙነት እንዳወጣ ይወተውቱኝ ጀመር፡፡ በግሌ ምንም አይነት ግንኙነት ስላለነበረኝ የምነግራቸው ነገር አልነበረም፡፡ ከማሰቃየት ተግባሩ እና ንትረኩ በኋላ ወደ ማደሪያ ክፍሌ አስር ቁጥር ስመለስ ግን ውስጤን ደስ ሲለው ይሰማኛል፡፡ የምወዳት ሀገሬን ነጻ ለማውጣት ተስፋዋን ለማለምለም የሚደረግ ጥረት ውስጥ እንዳለኹበት መቆጠሬ እና መደመሬ መጽናኛዬ ነበር፡፡ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵውያን ሲሉ እንደመገረፍ ያለ ደስታ ከወዴት ይገኛል?

አንድ ምሽት አንድ እስረኛ ወደክፍላችን ተጨመረ፡፡ ብቻውን አይደለም የመጣው ከክፉ ዜና ጋር እንጂ፡፡ አንዳርጋቸውን ያዙት፡፡ ከየመን አፍነው አመጡት የሚል መርዶ አቀበለኝ፡፡ ብቻዬን ስለሀገሬ አዘንኩኝ፡፡

ነገሬን ወደፊት ላጠንጥነውና ከኦሎምፒያ ልቀጥለው፡፡ ቦሌ መንገድ፣ ኦሊምፒያ አከባቢ የሚገኘው የአንዳርጋቸው ጽጌ ቤተሰቦች ቤት፡፡ የዐቢይ አሕመድ ያልተጠበቁ እርምጃዎች አንዲን ከእርስ ቤት እንደሚያስወጡ ተስፋ ሰጥቷል፡፡ ወዳጅ ዘመድ አባቡን ለመቀበል ተሰብስቧል፡፡ ሁለት፣ ሦስተ ቀን ሴት ወንዱ ወገቡን ታጥቆ፣ በኮሚቴ ተደራጅቶ ቢጠብቅም አንዳርጋቸው ብቅ አላለም፡፡ ሳሩ እንደተጎዘዘ፣ ግቢው በሰው እንደተሞላ ዶፍ ዝናብ ጀመረ፡፡ አንዲን የያዘችው መኪናም በዚያው ቅጽበት ተከሰተች፡፡ ሰው ኹሉ ራሱን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ አስተባባሪ ተብለው ባጅ የተዘጋጀላቸው ሰዎች ራሳቸው አሰተባባሪ አስፈለጋቸው፡፡ በዝናብ፣ በጩኸት፣ በደስታ ተጸበልን፡፡ መታሰሩ ተስፋዬን እንዳደከመው መፈታቱ ደግሞ የሀገሬ መጻዒ ዕድል ከገባበት ቅርቃር መውጫው ለመድረሱ ምልክት ሆነኝ፡፡

ብርሃኑንም ከእነ ቢሆን(scenarios) ትንታኔው በታላቅ አጀብ ተቀበልነው፡፡ ግንቦት ሠባት አዲስ አበባ ላይ ቢሮ ከፍቶ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ድርጅቱ ራሱን ከትግል ድርጅትነት ወደ መደበኛ የፖለቲካ ፓርቲነት ለመቀየር የተወሰኑ ወራት ወሰዱበት፡፡

በእነዚህ ወራት የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በርካታ የዜጎችን መብት የሚጥስ እርምጃዎች ወሰደ፤ ችግሮችም ተፈጠሩ፡፡ ከችግሮቹ ውስጥ አንዳንዶቹ ከቀድሞው አስተዳደር የወረሳቸው ሲሆኑ የተወሰኑት ደግሞ የተጀመረው የለውጥ ሂደት የወለዳቸው ናቸው፡፡ በአብዛኛው የችግሩ ምንጭ ግን ስርዓቱ ጥገናዊ ለውጥ በማድረግ በተረኛነት መንፈስ መንቀሳቀሱ ነው፡፡ ይህም በሌሎች እኔን መሰል ዜጎች ላይ የሀገር አልባነት ስሜትን ፈጠረ፡፡

በዚህ ወቅት እነብርሃኑ እንደ ድርጅትም እንደ ግለሰብም ግብረ ምላሽ አለመውሰዳቸውን መረዳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ምክንያት እንደደርጅት ያሉባቸው የቤት ስራዎች ፋታ የማይሰጡ መሆናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ከመንግስት ጋር ተደራድረው ወደሀገር ቤት ለመግባት ሲወስኑ ሀገሪቱን ከችግር ሊያወጣት የሚችለው መንገድ ላይ መግባባት ላይ ደርሰው ስለሚሆን በየጊዜው ከሚፈጠሩ ኹነቶች ይልቅ ዋናው ስዕል ላይ ማተኮር መርጠው ይሆናል፡፡

እንደኔ ይህ ራስን ከሁኔታዎች ጋር የማስተካከያ ጊዜ ልክ ኢዜማ ሲመሰረት በይርጋ ያበቃል፡፡ ከዚህ በኋላ መታየት ያለበት እንደማንኛውም የፖለቲካ ማኀበር ለህዝቡ ምን ይዘውለት መጡ የሚለው ይሆናል፡፡ ለኢህአዴግ የማልቸረውን ርኅራኄ ለብርሃኑ ፓርቲ መስጠት አልችልም፡፡

ብርሃኑ በተደጋጋሚ እንደተናገረው በቅርቡ ሰሜን አሜሪካ እንዳስረገጠው ፓርቲያቸው ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ሳይደረግ ወደ ምርጫ እንደሚገባ ነው፡፡ ይህ የሚያከትለውን ችግር የዴሞክራሲን ሰብል በጅብ እርሻ መሆኑን በዝርዝር ገልጫለኹ፡፡(https://www.facebook.com/abelpoly/posts/10219306120905172)
በአንጻሩ ከላይ በዘጠና ሰባት ማግስት የተውነው ልደቱ አያሌው ከህዝባዊው ቅጣት የሚያገግመበት እድል በቀላሉ ያገኘ አይመስልም፡፡ ቲያተረ ፖለቲካ ሲል በሰየመው መጽሐፉ ይህ የመገፋት ስሜት እንዳማረረው ለመገመት የሚያስደፍር ነው፡፡ ፕሮፍ ብርሃኑ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰ ጀምሮ የዶ/ር ዐቢይን መምጣት ተከትሎ የተነቃቁትን ሚዲያዎች በህዝብ ፊት አከራክሩኝ የሚል ልመና ማቅረቡ የዚህ ጥረቱ አካል ይመስለኛል፡፡

ከድሮ ጀምሮ ብዙ ባይባሉም ከግምት ውስጥ የሚገቡ ሰዎች እውነት ከእርሱ ጋር እንዳለች እነ ብርሃኑ በሸር በተንኮል ስሙን በማጥፋት የስብዕና ግድያ(character assassination) እንደፈጸሙበት የሚናገሩ አሉ፡፡ በሌላ ጎን ደግሞ ብዙ ንፁኃን ያስገደለ መሠሪ መሆኑን የሚናገሩ እና የብርሃኑን እስከ ኤርትራ በርሃ ድረስ የወረደ የትግል ገድል የሚተርኩ አሉ፡፡

የኔ ሐሳብ ከሁለቱም ጎራ አይመደብም፡፡ ያደረጉት በጎም ሆነ እኩይ ተግባር ለታሪክ ሚዛን ትተን ዛሬ ለእኛ የሚበጅ ምን በጎ ነገረ ይዘዋል ብለን መጠየቅ ይገባናል ብዬ አምናለኹ፡፡ መመዘንም ያለባቸው በአሁኑ ስራቸው ይመስለኛል፡፡

ለእኔ እንደ አንድ ዜጋ ስመለከተው የቀድሞ ስሙን ለማደስ ከሚያረገው መጋጋጥ በዘለለ ልደቱ የሚያቀርባቸው ሀሳቦች ይወክሉኛል፡፡ በተለይ ሀገሪቱ ያለባትን መዋቅራዊ ችግር በመተንተን መፍሔው መዋቅራዊ ሊሆን እንደሚገባው በጥራት እና በምክንያት መግለጽ ከሚችሉ ፖለቲከኞች መካከል ልደቱ አውራው ነው፡፡

ብርሃኑ በበኩሉ የዜጎችን መብት ለማስከበር የዜጎች የፖለቲካ ማኀበር ቢያቆምም ዜጎች መኖራቸው ተረስቶ በገዛ ሀገራቸው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ያደረጋቸውን ሰነድ ማሻሻያ ጊዜው አሁን አይደለም ይላል፡፡ በሀገሪቱ ሰላም እና ጸጥታ አለመኖሩ ምክንያት ከሆነ አስፈላጊው ጊዜ ተወስዶ መሻሻል አለበት፡፡ ነገር ግን ብርሃኑ ከኢዜማ ምስረታ በፊት ያደርግ እንደነበረው ለዜጎች ዋይታ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ ሳያንስ ራሱን አሁን ባለው መንግስታዊ መዋቅር በማደራጀት ለምርጫ መዘጋጀት ጀምሯል፡፡

ይህ የኢዜማ ፓርቲ አቋም በሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎች ምክንያት ተቀባይነት የለውም፡፡ አንድ መጫወቻ ሕጉ እና ሜዳው ፍትሓዊ ሳይሆን የሚደረግ ምርጫ ነጻ እና ፍትሓዊ አይሆንም፡፡ ሁለተኛ ኢህአዴግ እንደ ግንባር፣ ኦዴፓ እንደ ፓርቲ እስካሁን ባለን ተሞክሮ ኢ-ዴሞክራሲያዊ እና ደፍጣጭ የመሆን አባዜያቸው በቀላሉ የሚለቃቸው አለመሆኑ ነው፡፡ ግንባሩ ዘመኑን በሙሉ ዜጎችን ሲያጠቃ መኖሩ አያጠያይቅም፡፡ ኦዴፓም በዚህ ከፊት በሆነበት አጭር ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ሀፍረት የለሽ እና ስግብግብ እንደሆነ አሳይቷል፡፡ በስልጣን ተዋረድ ወደታች ያለው ደግሞ በእጅጉ የባሰ ነው፡፡

ሦስተኛው ለህዝብ የማይገለጸው እና የኢዜማ መሪዎች ለአንዳንድ ወሳኝ ናቸው ላሏቸው የፓርቲው ደጋፊዎች የነገሩት የሚመስለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በፕሮፌሰሩ መካከል ያለ ስምምነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ስምምነቱ ይኑር አይኑር ወይም እንዲሁ በዓላማ መግባባት የፈጠረው እምነት/መተማመን ይሁን አላውቅም፡፡ ይህም በራሱ በርካታ ችግሮችን ያዘለ ነው፡፡ ይህም ሕገ መንግስቱ እንዳይነካ ለሚፈልጉ ሰዎች ፍትሕን አያደርግም፡፡ It doesn’t do Justice. ሀገር የሚገነባው በእውነት እና በመተማመን ነው እንጂ በሴራ እና በተንኮል አይደለም፡፡ በሌላ መልኩ ምን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም ሀሳብ ቢኖራቸው እርሳቸው ብቻ ቃል ግብተው ለመዋቅራዊ ችግሮች ዋስትና ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በቀላሉ ተሰባሪ ናቸው፡፡ እርሳቸው ሲሰበሩ ሁሉም ነገር ይሰበራል፡፡ እርሳቸው ቢበረቱ ፓርቲያቸው እና ጎጠኛው ልሂቅ ሞብ አደራጅቶ የሚፈልገውን ለማስፈጸም በተጠንቀቅ እንዳለ መዘንጋት የለበትም፡፡

ስለዚህ ሴራ ሴራ ከሚሸተው ፕሮፍ ብርሃኑ እና ፓርቲያቸው ይልቅ እውነትን በምልዐት እና በምክንያታዊነት በማቅረብ ለመዋቅራዊ ለውጥ የሚታገለው ልደቱ አስር እጅ ይሻላል፡፡ በጣም ድቅድቅ ጨለማ እንደሆነ ምን አይነት ተስፋ እንደሌለ ሰው ኹሉ መጥፎ እንደሆነ በጨለምተኝነት ማሰብ ይቻላል፡፡ በንዝሃላልነት ሁሉም ነገር በጎ እንደሆነ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለብን አሁን በመንግስት የተያዘው ዕቅድ በአጭር ጊዜ ሀገሪቱን ገነት እንደሚያደርጋት ማሰብም ይቻላል፡፡ ለሁላችንም ከመቶ ሚሊዮን ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ግን የሚበጀው ምክንያታዊነት ነው፡፡
**  *
*ነ.አ. – ነፍሱን አይማረውና

LEAVE A REPLY