ሁላችንም የኢትዮጵያ ችግር እንዴት እንደሚፈታ ጭንቀት ይዞን ሀሳብ ለማመንጨት በሀገራችን ጉዳይ ተጠምደን ለሌላ ነገር ጊዜ አጥተናል። ብርቅዬ ምሁራን የኢትዮጵያ እንቆቅልሽ እንዴት እንደሚፈታ የመፍትሄ አሳብ እንደ ዝናብ ዘወትር ያሽጎደጉዳሉ። ያልተፃፈ የለም። ያልተባለ የለም። የኢትዮጵያ ልጆች ችግር ሲፈጥሩ እንዳይፈታ አርገው መቋጠር ይችላሉ። ያንኑ ያህል ደግሞ ውሉ የጠፋበትን እንቆቅልሽ ለመፍታት ብቃትና ብልሃት ያላቸው ብዙ ልጆች ኢትዮጵያ አሏት። በኢትዮጵያ ልጆች እጅ ያለ መፍትኤ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ይተርፋል። ኢትዮጵያ እንዲህ ጥበብና መላን በማፍለቅ የበለፀጉ ልጆች ከቁጥር በላይ ቢኖራትም ያልታወቀላት ሀገር ናት። ይህ ብቻ ሳይሆን እውቀትና ጥበብ ሳይጎድለን እንደ ጎደለን ራሳችንን ቆጥረን፥ ሌላ መፍትሄ ሀሳብ ለማፍለቅ ከመፍጨርጨር ላንዴም ዕረፍት መውሰድ አልቻልንም።
መፍትሄ እንዳናገኝ የያዘን በሽታችን ነው እንጂ፥ ጉዳዩ የጥበብ ማጣት ወይም ከእውቀት መጉደል አይደለም። በበሽታ ተይዛ የተኛችው ኢትዮጵያ ከበሽታዋ የምትፈወስበትን መድሃኒት ምርጫችን ከማድረግ ይልቅ፥ ከአልጋዋ ገና ተነስታ ወደፊት ስለምትሰራው ሥራ ዕቅድ በማውጣት ተጠምደናል።
እግዚኦ! ያሰኛል። ታመናል። ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ታመናል። ፈውስ የሌለው በሚመስል በሽታ ታመናል። በሽታው ሳያንስ አሁን አሁን ደግሞ የቃላት ውጊያና ጫጫታ ጨምረንበታል። የድል አጥቢያ አርበኛው ሠርግና ምላሽ ሆኖለታል። በዚህ ሁሉ ግርግር ውስጥ ዛሬም እንቆቅልሽ የሆነብንን ውስብስብ የኢኮኖሚ፥ የፖለቲካ፥ የዘረኝነት የመሳሰሉትን ችግሮች ለመፍታት እንራወጣለን እንጂ እየሰመጥን እንደሆነ አላስተዋልንም። የነገሩን ክብደት ብናውቅ ነፍስ አድን ዘመቻን እናስቀድም ነበር። ግራ የሚገባው ችግርን ከመፍታት በፊት የህልውና ጥያቄ የሆነው በሽታና ውጊያ ስፍራውን ይለቅ ዘንድ አለመታሰቡ ነው። ስንኖር እኮ ነው ለችግራችን መፍትሄ የምንፈልገው። በሽታችን እየገደለን ባለበት ወቅት ቅድሚያ ለፈውስና ለተኩስ አቁም ክህሎት ቅድሚያ እንስጥ። ከቀን ወደ ቀን፥ በሽታችን ከውጊያው ትኩሳት ጋር ተደምሮ ከሰውነት ማንነት እያወጣን፥ እየጨረሰንና እያጫረሰን ባለበት ሁኔታ፥ ችግር ስለ መፍታት ማውራት ምን ይባላል? አውቀን ሳናውቅ አለቅን።
ለበሽታችን መድሃኒት የሆነው ነገር፥ አንድ ሕፃን የሚያገናዝበው እውነት የሆነው አኳኋን (attitude) ነው። ከዚህ ቀላልና ተራ ከሆነ ነገር ብንጀምር፥ ጥበብ እያለን ጥበብ እንደሌለን ሆነን የምንኖረው አካሄድ ያቆማል። ይህ ትንሽ እውነት ወንድማችንን ከማጥፋት ላይ ፊታችንን አንስተን፤ ሁላችንም ፊታችንን ውስብስብ ወደ ሆነው እንቆቅልሾቻችን ዘወር እንድናደርግ አቅም ይሰጠናል። የዚህ መድሃኒት ፍቱንነቱ በዋነኛነት የሚታየው ከሚያጠፋፋን ከእርስ በርስ ትንቅንቅ መገላገሉ ነው። ይህን ትንሽ ግርድፍ ሀቅ ንቀን፥ ትልቅና ረቂቅ የሆነውን ጥበባችንን የሙጥኝ ካልን፥ እያለን እንደሌለን ሆነን፥ ከድጥ ወደ ማጡ እንዳንዘቅጥ እፈራለሁ። እስቲ ለቅምሻ ያህል አስር አኳኋንን እንመልከትና ልባችንን በዚሁ መንገድ ላይ እናድርግ።
ዐብይ ሲታይ: ዶ/ር ዐብይና የለውጥ ሃይሎች ተመከሩ አኳኋን (attitude) አንድ። ከመስማት ምንጊዜም አትቦዝኑ። ለሚቃወማችሁም ጆሮ አትንፈጉት። በተለይ የአመራር ትኩረታችሁ ፍፁም ፍትሀዊ እንዲሆንና በዚህ ጉዳይ የምትከሰሱበት አውድ እንዳይኖር ከሁሉ በፊት ያለ አድልዎ መሆንን ቅድሚያ ስጡት።
አኳኋን (attitude) ሁለት። ለመስተካከልና ለማስተካከል ዘወትር ፍጠኑ። የሚሰራ ሰው ሁልጊዜ ይሳሳታል። ስለዚህ ምክንያት ሳትሰጡ ለስህተት ሃላፊነትን ውሰዱና በጊዜ አርሙት። ብድራታችሁን ዛሬ ከሚረዳችሁ የኢትዮጵያ አምላክ እና ነገ ከሚነገርላችሁ ታሪክ ጠብቃችሁ፤ ከትላንት በተሻለ ዛሬ ሁልጊዜ በአዲስ መንፈስ ለሥራ በፅናት መነሣትን አታሰልሱ።
ሕዝብ ሲታይ: በመረዳት እንደግፈው እንጂ በጭፍን አንፍረድበት አኳኋን (attitude) ሦስት። እንደ አመፀኛ ዳኛ ፍርደ ገምድል አንፍረድ። ዶ/ር ዐብይ አንድ ሰው ነው። ዐብይ ማለት መንግስት ማለት አይደለም። ዶ/ር ዐብይ ያለበትን ጭንቅና ተግዳሮት አናውቅም። ራሳችንን ከጫማው ውስጥ እናስቀምጥና የተጣደበትን እሳት አግለን ለማንደድ ልባችን አይጨክን። ይህ ሲባል ዶ/ር አብይ ከሕግ በላይ አይነኬ ነው ማለት አይደለም። ሲሳሳት ማረም ሃላፊነታችን ነው። ቁም ነገሩ ስንናገር ሚዛናዊ መሆንና፥ በመልካም መንፈስ እርሱን ለማቅናት ካለን በጎ ፍቃድ የተነሣ፥ ቅንነትን መካከለኛ ማድረግ የሃላፊነታችን ሌላኛው ገፅታ መሆኑን ችላ እንዳንል ያስፈልጋል።
አኳኋን (attitude) አራት። ሁሉንም በልክ እናድርግ። ዶ/ር ዐብይን እስክናመልከው በመውደድ ንጉሥ ማድረግም ሆነ፥ ሩቅ ቆሞ ጣት በመቀሰር ማጣጣል ሁለቱም ጤነኛ አይደሉም። እኛው ክበን፥ እኛው ንደን፥ ስራችን ሁሉ የዕብድ እንዳይመስል እንፍራ።
ጠላት ሲታይ: ከማስተዋል እንዳንጎድል ሁልጊዜ እንንቃ አኳኋን (attitude) አምስት። የጠላትን ሤራ አንሳተው። ሰው ሁሉ ሰልፍ ሲወጣ፥ ዘፋኙ ሲዘፍን፥ ባለ ቅኔው ሲደረድር፥ ሴረኛው ከእኛ ጋር አልዘፈነም። ታዲያ ተንኮለኛው የት ነበር? ተንኮሉንና ሴራውን እንደ ቦንብ በየስፍራው እየቀበረ ነበር። ቀስ በቀስ እየሸረሸረ፥ ዶ/ር ዐብይን ከሚወደው ሕዝብ የሚነጥል ነፋስ በመካከል ይሰድ ነበር። የማይታየው ስውሩ ዕኩይ የሆነው ሤራው ሰምሮለት፥ እርሱ ምክንያት መሆኑ በሕዝብ ዕይታ እንዲሰወር ማድረግ ይሞክራልና እንንቃበት።
አኳኋን (attitude) ስድስት። ለጠላት ሽፋን አንሁንለት። ኑሮ ማሸንፍ አነሳስቶን፥ የሤራ ንግድ ትርፍ አምጥቶልን፥ ሀገር በፈጠራ ተረት እያተራመስን የምናገኘውን ብርና ዝና ተንተርሰን የምንተኛ፥ ህሊናችንን ሸጠናልና ሳይመሽብን ወደ ልባችን ቶሎ እንመለስ። ሳናስተውል ቀርተን፥ የሴረኛው ፊትና ጭንብል ሆነን፥ አጥፊው ህቡዕ ሆኖ እጁ እንዳይታይ መተባበር ይቅርብን። እውነት እንናገር ካልን መኖሪያውን አትርፎበት ጠብ ከሚናገረው፥ ጠብ ጥሞት የሚሰማው ይበልጥ ይገርማል።
አኳኋን (attitude) ሰባት። ጠላት መሆንን እንፀየፈውና እንተወው። እውነተኛው የኢትዮጵያ ጠላት ስጋና ደም ያለው አይደለም። እኛም የኢትዮጵያ ልጆች ነንና ከዚህ እኩይ መንፈስ መጠቀሚያ ከመሆን ራሳችንን እናስመልጥ። በሕዝብ ስም፥ በሕዝብ ላይ ቁማር መጫወት ምንም አይጠቅመንምና ይቅርብን። ከእልከኝነት ራሳችንን ታድገን፥ ለምን የግል ጥቅሜ ተነካ ብለን በሕዝብ ስም የሰይጣን እጅና እግር መሆንን አቁመን፥ ከመሃሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንቀላቀል።
ፈጣሪ ሲታይ: አሁንስ ተስፋችን ማነው? አኳኋን (attitude) ስምንት። ተስፋ ቆርጠን ያንኑ ተስፋ ቢስነት አንዝራ። የኢትዮጵያ አምላክ ስንት ጊዜ በተዐምር ኢትዮጵያን እንደታደገ እንዴት ተዘነጋን? አሁንስ የኢትዮጵያ ተስፋ ፈጣሪ እንደሆነ አናውቅምን? ኢትዮጵያ አምላክ እንደሌላት ምን ያቆዝመናል? የጨለመ የሚመስለው ይበራል። የተበላሸ የሚመስለው ሁሉም ይስተካከላል።
አኳኋን (attitude) ዘጠኝ። ተዉ የተገላቢጦሽ አናድርገው። ቤተ እምነት መንግስትን በሞራል እየመራ ለመንግስት ሆነ ለምድራችን በረከት ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ፥ ዶ/ር ዐብይ ለሁሉም ቤተ እምነት በረከት ሆኖ አረፈው። ይሁንና አሁንስ ለአገር ድነት የማንነሳው እስከ መቼ ነው? ሃይማኖት ሳንለይ ኢትዮጵያዊ ከሆንን፥ ሁሉም የእምነት አባቶች በተቀናጀ መልክ ለኢትዮጵያ ፈውስ ቢያንስ አንድ ላይ ለወር ፆምና ፀሎት ሁሉም በየቤተእምነቱ እንዲያደርግ በምድራችን ላይ ማወጅ ለምን ተሳናቸው? ሰው ከአምላኩ ጋር በጥሞና እና በሱባዔ ልቡን ወደ ፍቅርና ይቅርታ መለስ እንዲያደርግ በር ይከፍቱልን ዘንድ አደራ እንላለን። እንዲህ ቢያደርጉ ወደፊት ለሚካሄደው ብሔራዊ እርቅና መግባባት መንገድ ጠራጊና ፋና ወጊ ይሆናሉ። የሁሉ ችግር ስርና መሠረት የሆነው መንፈሳዊው ነውና ፊት ፊት እየሄዱ እንዲመሩን ፀሎታችን ነው።
አኳኋን (attitude) አስር። ፀሎት በሥራ ይገለጥ። አምላክን ለምነን ስናበቃ፥ የሚያዘንን በስራ ለመግለጥ ለምን አንነሳሳም? ብዙ ሩቅ ሳንሄድ አምላክ አገራችንን እንዲባርክልን እየጠቅነው፥ እርሱ ከሰጠን ገንዘብ አንድ ዶላር በየቀኑ ለደሃ ሕዝባችን ላለመስጠት ለምን ሰንካላ ምክንያት እንደረድራለን?
ኢሜል፥ Z@myEthiopia.com