የአዲስ አበባ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማድረግም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርግ ማዕቀብ እንደተጣለበት ተገለጸ
የአዲስ አበባ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማድረግም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርግ ማዕቀብ ተጥሎበታል ሲል የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራ ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ ገለጸ። “የሕሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ” በሚል ባልደራስ መግለጫ አውጥቷል::
በትናትናው ዕለት ሲሰጥ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫው፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርግ ማዕቀብ ተጥሎበታል ብሏል፡፡ “ኢትዮጵያ ዛሬ የሕሊና እስረኞች ያሉባት ሃገር ሆናለች ያለው የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ የሕወሓት አገዛዝ ከተገረሰሰ ከአንድ አመት በኋላ በርካቶች በሕሊና እስረኝነት ወደ እስር እንዲጋዙ ተደርጓል ብሏል::
የባላደራው ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ኤልያስ ገብሩና የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል። ከእነዚህ እስረኞች በአብዛኞቹ ላይ ፖሊስ በባህርዳር ከተፈጸመው ችግር ጋር ንክኪ አላቸው በሚል በኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በአዲሱ አመራርም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተወገዘው የሽብር ህግ ክስ መስርቶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ።” ሲል ተቃውሞውን በግልጽ አስቀምጧል፡፡
“በባህር ዳርም ሆነ በአዲስ አበባ የተከሰቱት ችግሮች መጀመሪያቸውም ሆነ መጨረሻቸው ኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረ ልዩነት መሆኑ እየታወቀ በባላደራው አባላት ላይም ሆነ በሌሎች ላይ እየተወሰደ ያለው የእስር ርምጃ አሳዛኝ ነው፣ አንቀበለውምም” ያለው ባላደራው ም/ቤት – በዕለቱ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ባልታወቁ ቡድኖች በተቀናጀ እንቅስቃሴ አማካይነት እንዲቋረጥ መደረጉ ተገልጿል፡፡
በባልደራሱ የባለአደራው ቢሮ አካባቢ ሽብር በመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችን ሲያስተባብሩ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች በተለያዩ ጊዜያት (የቅርብ ቀናትን ጨምሮ) ከከንቲባ ታከለ ኡማ ጋር የተነሷቸው ፎቶዎችና የቅርብ ግንኙነታቸውን የሚያሳዩ ጽሁፎች ከትናንትና ምሽት ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየወጡ መገኘታቸው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡
የአብኑ አቶ ክርስቲያን ታደለ በድጋሚ ዛሬ በአዲስ አበባ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታሰረ
የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ከሌሎች አመራሮች ጋር በመሆን ዛሬ ሐምሌ 4/2011 ዓ.ም የታሰሩ አባላቶችን ጥየቃ አዲስ አበባ በሚገኘው 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በሄዱበት ወቅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ክርስቲያን ታደለ ተለይቶ በቦታው በነበሩ ደህንነቶች ታስሯል፡፡
ሰሞኑን ከታሰሩ የአብን አባላት በተጨማሪ ትላንት እና ዛሬ በርካታ የአብን አመራርና አባላት በአዲስ መልክ እየታፈሱ መሆኑ ታውቋል፡፡ አቶ ክርስቲያን በተመሳሳይ ስሞኑን ታሰሮ መለቀቁ ይታወቃል::
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች መታሰር እንዳሳሰበው ገለጸ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ መንበሩ ከመጡ ወዲህ በሚዲያ ነጻነት ድንቅ እምርታ እየታየ የነበረ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁኔታዎች ተቀልብሰው ጋዜጠኞች አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲል አምንስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።
ዓለም ዓቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄም በተመሳሳይ ባወጣው መግለጫ ለአንድ አመት አንድም ጋዜጠኛ በእስር የሌለባት ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ የፕሬስ ነፃነት ደረጃም (ወርልድ ፕሬስ ፍሪደም ኢንዴክስ) መሰረት አርባኛ ሆና ነበር አውስቷል፡፡
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁኔታዎች ወደነበሩበት መለወጣቸው አሳሳቢ ሆኗል” የሚለው አምንስቲ በነዚህ ሳምንታት በአዲስ መልኩ ጋዜጠኞችን የማሸማቀቅና የማሰር ዘመቻ እንዳለ ገልጾ ከሁለት ቀን በፊት የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የተቋሙንና የሰራዊቱን ስም እያጠፉ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ክስ ሊመሰርት መዘጋጀቱንም ኮንኗል፡፡
ዳይሬክተር ጆዋን ናንዩኪ ይህ በአዲስ መልኩ የተጀመረው ጋዜጠኞችን የማሰር ዘመቻ የታየውን የፕሬስ ነፃነት ወደ ኋላ የሚመልስ እርምጃ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የታሰሩ ጋዜጠኞችን በቶሎ ይፍታ፤ ክሳቸውም አሁኑኑ ውደቅ ይደረግ ሲሉ የአምነስቲን አቋም ይፋ አድርገዋል፡፡
በሜድሮክ የተገነባው የኢትዮጵያ ትምህርትና ጥናት ተቋም ማዕከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመረቀ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ትምህርትና ጥናት ተቋም በመሆን የሚያገለግል ህንፃ ግንባታው ተጠናቆ በዛሬው ዕለት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ርክክብ ተፈጽሟል።
ማዕከሉ 116 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን የግንባታው ሙሉ ወጪም በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት ሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን የተሸፈነ ነው። ማዕከሉ ቤተ መጻህፍት፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ቢሮዋች፣ የኤግዚቢሽን ማሳያና የመጻህፍት ክምችት ክፍልና ሌሎች በርካታ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ክፍሎችን እንዲይዝ ተደርጎ እንደተገነባ በምረቃው ስነ ስርአት ወቅት ተገልጿል።
ቻይና በኢትዮጵያ ረዥሙን ድልድይ ልትገነባ ነው
ኢትዮጵያ 49 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ረዥም ድልድይ ልትገነባ መሆኗን ፌስ ቱ ፌስ አፍሪካ በድረገፁ አስነበበ፡፡ ግንባታውም በቻይናው ሲሲሲሲ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የሚከናወን ሲሆን ኩባንያው የድልድዩን ግንባታና ዲዛይን በሚመለከት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የስምምነት ፊርማ መፈጸማቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
በባህርዳር አካባቢ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ድልድይ በ3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ዕቅድ ተይዞለታል፡፡ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ድልድይ 21.5 ሜትር ስፋትና ሶስት መስመሮችን የሚይዝ ሲሆን ይህም የብስክሌት፣ የመኪና መስተላለፊያና የእግረኛ መንገድን የሚያካትት እንደሆነ በዘገባው ሰፍሯል፡፡
የፕሮጀክቱ ወጪ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ስለመሆኑም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ የባህርዳሩ አባይ ድልድይ ከተጠናቀቀ በኋላ በኢትዮጵያ ረዥሙ ድልድይ እንደሚሆን የታወቀ ሲሆን ጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም ለትራፊክ ክፍት የሆነውን 319 ሜትር ርዝመት ያለውን የባሽሎ ወንዝ ድልድይ በርዝመት እንደሚበልጥ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የቻናው ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሲሲሲ በሃገሪቱ የሚገነቡ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የሚያከናውን ሲሆን በዚህም የኮምቦልቻን ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በሃገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የአዲስ-አዳማ ፈጣን መንገድ፣ ቦሌ አካባቢ የሚገኘውን የአፍሪካ ጎዳና መንገድ፣ የመኢሶ-ጅቡቲ ባቡር መንገድ ብሎም በአዲስ አበባ የቦሌ አለም አቀፍ አየር መንገድ ማስፋፊያ ግንባታዎችን እያከናወነ የሚገኝ ታላቅ ተቋም መሆኑን ዘገባው አመላክቷል፡፡በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ኩባንያው አራት በሂደት ላይ ያሉ ታላላቅ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ነፃ የት/ቤት ዩኒፎርም ለ600 ሺህ ተማሪዎች በቀጣይ ወር መሰጠት ይጀመራል
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግሥት ት/ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ ከ600.000 (ከስድስት መቶ ሺኅ) በላይ ተማሪዎች የት/ቤት ደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) በራሱ ወጪ አሰፍቶ ለማደል በዝግጅት ላይ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማምጣት ከያዛቸው ታላላቅ እቅዶቹ መካከል አንዱ እንደሆነ የተነገረለትን ያህል ለተማሪዎች የት/ቤት ዩኒፎርም አሰፍቶ በነፃ የማደል ዕቅድ እውን ለማድረግ ከወራት በፊት ጀምሮ በስፋት ሲንቀሳቀስበት እንደቆየ በገለፀበት መግለጫው እንደተመለከተው ለተማሪዎች ተስማሚ የሆኑትን የደንብ ልብሶች ለማቅረብ ፋሽን ዲዛይነሮችን ያሳተፈ ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
“በፋሽን ዲዛይነሮቹ በቀረቡ የተማሪዎች ዩኒፎርም አይነቶችና ጥራት ላይ የተማሪ ወላጆች፣ መምህራን፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችና ተማሪዎች ራሳቸው ሀሳብ እንዲሰጡበት ተደርጓል” ያለው የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት ቁጥራቸው 400 (አራት መቶ) በሚጠጉ በከተማዋ በሚገኙ ት/ቤቶች ለሚማሩት ከ600 ሺኅ በላይ ለሚሆኑት የመንግሥት ት/ቤት ተማሪዎች ከደንብ ልብስ በተጨማሪ ደብተርና ሌሎች ለትምህርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በነፃ የማደል ዕቅድ መያዙን አስታውቋል፡፤
‹‹ይህ የተደረገው የተማሪ ቤተሰቦችን ሸክም ለመቀነስና ችግራቸውን ለመጋራት ›› በማሰብ እንደሆነ የገለፀው የከንቲባው ጽ/ቤት ‹‹ የተማሪዎችን ወጪ መሸፈን የትምህርት ሥርዓቱን እንደሚያግዝ፣ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመገንባትና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እንደሚረዳ ›› እምነት ማሳደሩን በሰጠው መግለጫ አመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በይፋ ያስጀመሩት ይህ ፕሮግራም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሥራው ተጠናቆ ለመጪው የትምህርት ዝግጁ እንዲሆን የታሰበ ሲሆን ከዩኒፎርሙ በተጓዳኝ ለተማሪዎቹ በነፃ ለመስጠት ለታሰበው የ7 ሚሊዮን ደብተር ልገሳም በበጎ ፈቃደኞች ርብርብ እንዲሁም በባለሀብቶችና ድርጅቶች ልገሳ ግማሽ ያህሉ (3.5 ሚሊዮን ደብተር) ተገኝቷል፡፡ በቀጣይ ሳምንትም ቀሪዎቹን ደብተሮች በማሰባሰብ ለተማሪዎች የማዳረሱ ሥራ ይጀመራል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያና የአሜሪካ ወታደራዊ ልምምድ ሰኞ ይጀመራል!
ኢትዮጵያና ልዕለ ኃያሏ ሰሜን አሜሪካ የጋራ ወታደራዊ ልምምዳቸውን የፊታችን ሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ እንደሚጀምሩ ተገለፀ፡፡
አዲስ አበባ ከሚገኘው ከአሜሪካ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የአሜሪካ ጦር ሀይል ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በጥምረት የሚያከናወኑት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለ17 ቀናት እንዲካሄድ ዕቅድ ተይዟል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአባላቱን ዝግጁነትና አቅም በማሳደግ የቀጠናውን ሰላም ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ እንዲሆንና የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በብቃት እንዲወጣ ለማስቻል ታስቦ በተዘጋጀው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ 1 ሺኅ አንድ መቶ የሰራዊቱ አባላትና የመንግሥት ሃላፊዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
በሶማሊያ የተሰማራውን የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሀይል (አሚሶም) አባላትን አቅም ማሳደግ ላይ ባተኮረው በዚሁ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ከብራዚል፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጅቡቲ፣ ኬኒያ፣ ብሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ የተውጣጡ ወታደሮችም ተሳታፊ እንደሚሆኑበት ያገኘበው መረጃ አመልክቷል፡፡