ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም

ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም

የሲዳማ ክልልነት ተመልሷል በሚል ዛሬ በሐዋሳ አደባባዮች ጭፈራ ተጀመረ

ክልሉን የሚያስተዳረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሲዳማ በክልል እንዲዋቀር ያለውን ድጋፍ ገልጿል በሚል በርካታቶች በሐዋሳ በተለያየ መንገድ ደስታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

ከፌደራል መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ በሌለበት ሁኔታ፣ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከረፋዱ ጀምሮ የተለያዩ የደስታ አገላለጽ ድርጊቶች በሐዋሳ በይፋ እየታዩ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የሲዳማ ዘመን መለወጫ “ፍቼ ጨንበላላ” በሚከበርበት “ጉዱማሌ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በርካቶች እየተሰባሰቡ ይገኛሉ፡፡

ከልል የመሆን ጥያቄ የተነሳበት የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ትናንት እሁድ በሐዋሳ ከተማ ተሰብስበው የሲዳማ ክልል በሚመሰረትበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውም ተሰምቷል፡፡

በአንጋፋ የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች በተመራው ስብሰባ በርካታ በማህበረሰቡ ውስጥ ተሰሚነት አላቸው የሚባሉ ታዋቂ ሰዎች ተገኝተውበታል፡፡ ዋና አጀንዳውን ውጥረት በፈጠረው ክልል የመሆን ጥያቄ ላይ ያደረገው የሐምሌ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ስብሰባን በተመለከተ መጀመሪያ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር አለመግባባት ቢከሰትም፤ በስብሰባው መሪዎችና በህግ አስከባሪ አካላቱ መሀል ንግግር ተደርጎ ያለምንም ችግር ስብሰባው ተካሂዷል፡፡

ሐምሌ 11ን መሰረት በማድረግ በዚሁ ዕለት ክልልነትን ማወጅ ወይም ይህንን ውሳኔ ማዘግየት በሚሉት ሀሳቦች ዙሪያ ውይይት ቢደረግም በስብሰባው ላይ ስለተደረሰበት ውሳኔ በግልፅ የተነገረ ነገር እንደሌለ የስብሰባውን ተሳታፊዎች ጠቅሶ የዘገበው ቢቢሲ አንዳንድ ሰዎች የሲዳማ የሐገር ሽማግሌዎች ዞኑን ወደ ክልል የማሸጋገሩ ሂደት እንደታቀደው እንዲካሄድ ወስነዋል የሚል ጭምጭምታ መኖሩን ጠቁሟል፡፡

የሲዳማ ዞን ወደ ክልል እንዲሸጋገር በዞኑ ምክር ቤት ጥያቄ የቀረበው ባለፈው ዓመት ሐምሌ 11 ሲሆን፤ እስካሁን ተግባራዊ ምላሽ ባለመሰጠቱ በዚሁ ዕለት ክልልነትን ለማወጅ እንቅስቃሴ መጀመሩ ነገሮች ወደ አስጊነት ሊቀየሩ ይችላሉ የሚል ግምትን በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል፡፡

ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ በሐዋሳ ከተማ ለሲዳማ ክልልነት ይሁንታ ተሰጥቷል በሚል “ሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት” የሚል ጽሁፍ የሰፈረበትን ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች በከተማዋ አደባባዮችና በመዝናኛ ስፍራዎች ክብ ሰርተው፣ በቡድን በቡድን ሆነው ሲጨፍሩና ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የውሳኔ ቀን በተባለው ሀሙስ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በከተማዋ ምን ሊፈጠር እንደሚቻል ከወዲሁ አመላካች ነው ተብሎለታል፡፡

የታከለ ኡማ አስተዳደር ከ32 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን በ2011 በጀት ዓመት ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ይፋ አድርጓል፡፡ የመስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለም የባለ ስልጣን መ/ቤቱ ሠራተኞች ላስመዘገቡት አመርቂ ውጤት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ካለፈው ዓመት ገቢ በአምስት ቢሊየን የሚበልጠውን የዘንድሮውን የገቢ አሰባሰብ ተከትሎ የከተማው መስተዳድር አስቀድሞ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት ለቀጣይ ዓመት የትምህርት ዘመን ዝግጁ ሆነው እንዲቀርቡ ሶስት መቶ የመንግስት ትምህርት ቤቶች እድሳትን ጀምሯል፡፡

ከትምህርት ጋር በተያያዘ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የአ.አ ከተማ መስተዳድር፤ 6 ሚሊየን ደብተሮችና ሌሎች የትምህርት ግብዓቶችን ከተለያዩ ተቋማትና ባለሃብቶች እስካሁን ድረስ አሰባስቧል፡፡ ቃል በገባው መሰረትም የ600 ሺህ ተማሪዎችን የደንብ ልብስ ወጪ ለመሸፈን ከጨርቃጨርቅ አምራቾችና ታዋቂ ባለሀብቶች ጋር ውይይት እያካሄደም ይገኛል፡፡

በበጀት ዓመቱ 34 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከታክስ ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ 32 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር እስካሁን ገቢ መደረጉን የገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺህሰማ ገብረስላሴ የዘርፉን አገልግሎት ለማዘመን እና ከግብር ከፋዩ ጋር ያለውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት ሊመዘገብ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ዓመታዊ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ዛሬ ተጀመረ

አሜሪካ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ በደረሰችው ስምምነት መሰረት በዛሬው ዕለት ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም የአሜሪካ መከላከያ አባላት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል ጋር በጥምረት ልምምድ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

አንድ ሺኅ የሚሆኑ ወታደራዊና የመንግስት ሓላፊዎች ይሳተፉበታል የተባለው ልምምድ ዋነኛ ዓላማ በሶማሊያ በተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) አባላትን ብቃት ማሳደግ ላይ ያተኮረ እንደሆነም ተሰምቷል፡፡ ልምምዱ የመከላከያ አባላትን ዝግጁነትና አቅም በማሳደግ፣ ሰላምን ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ከመርዳቱ ባሻገር በቀጠናው ሰላም ማስፈንም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተነግሯል፡፡

ለአስራ ስድስት ቀናት በሚቆየው ወታደራዊ ልምምድ ላይ ከብራዚል፣ ብሩንዲ፣ ካናዳ፣ ጅቡቲ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ኬንያ፣ ኔዘርላንድ፣ ዩናይት ኪንግደም ፣ ኡጋንዳ፣ሶማሊያና ሩዋንዳ የተውጣጡ ወታደሮች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የልምምዱን መጀመር አስመልክቶ ከተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያና አሜሪካ በህክምና ዝግጁነት ላይ ያተኮረ ልምምድ እያደረጉ ናቸው፡፡

በዚህ ልምምድ ወታደራዊና መደበኛ የህክምና አባላት የሚሳተፉ ሲሆን፣ የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የሚሰጠውን የህክምና ክትትል አቅም ለማሳደግም ያስችላል ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጠንካራ እርምጃዎችን እንደሚወሰዱ በጨፌ ኦሮሚያ ጉባዔ ገለጹ

መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ በሚገኘው ጨፌ አሮሚያ የክልሉን የ2011 ዓ.ም የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ሽመልስn አብዲሳ የኦሮሚያ ክልልን ሰላም እያደናቀፉ ባሉ አካላት ላይ የህግን የበላይነት ለማረጋገጥ ሲባል ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሆነና ይህንንም መንግስታቸው አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

የመጣውን ለውጥ የሚፃረሩ አካላት ሕብረተሰቡ መካከል ግጭት በመፍጠር፣ ዜጎች ከመኖርያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው ለክልሉ መንግስት ከባድ ፈተና እንደነበርም ም/ርዕሰ መስተዳሩ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በተሰራው ስራ፣ ለ606 ሺኅ ዜጎች በቋሚነት፣ ለ386 ሺኅ ዜጎች በጊዜያዊነት በድምሩ ለ993 ሺኅ ዜጎች የስራ ዕድል እንደ ተፈጠረ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሪፖርታቸው ይፋ አድርገዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከነበረበት 63 ነጥብ 8 በመቶ በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት 66 ነጥብ 13 ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራም በክልሉ 2 ቢሊየን የዛፍ ችግኞች ለመተከል ዕቅድ ተይዞ፣ እስካሁን 661 ነጥብ 8 ሚሊየን የዛፍ ችግኞች ለመተከል ተችሏል፡፡

በትምህርትና በጤና ዘርፍም በክልሉ በርካታ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን የተናገሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በገቢ ረገድ በበጀት ዓመቱ 18.5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ከመደበኛ ገቢ 15 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር፣ ከማዘጋጃ ቤት ገቢ 3 ነጥብ 27 በድምሩ 18 ነጥብ 69 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ፤ ዕቅዱን 101 በመቶ ሊያሳካ እንደቻለ መደበኛ ጉባኤው ላይ ገልፀዋል፡፡

ጨፌ ኦሮሚያ በዚህ ጉባኤው በክልሉ የ70 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ ያፀድቃል ተብሎ ይገመታል፡፡ ሐምሌ 9 ቀን በሚጠናቀቀው ጉባኤ ላይም የተለያዩ መመሪያዎች እና ደንቦች ይፀድቃሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በ2012 በጀት ዓመት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ መንግስታቸው ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ የገለጹት ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ያለውን የፀጥታ ችግር በመፍታት ረገድ አስፈላጊውን ዕርምጃ ሁሉ እንደሚወስዱም አስታውቀዋል፡፡

የሰላም ኖቤል ተሸላሚዋ ማላላና ፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተገናኙ

የሠላም ዘርፍ ኖቤል ተሸላሚዋና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠላም መልዕክተኛ ማላላ የሱፍ ዛይ እና ፕሬዝዳት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተገናኝተው ተወያዩ፡፡

ኢትዮጵያውያን ሴት ተማሪዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመማር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ፕ/ት ሣህለወርቅና ብርቱዋ ወጣት ማላላ በሰፊው መክረዋል፡፡ መንግስት ያለውን የትምህርት ፖሊሲ ሁሉን ዓቀፍ በሆነ መልክ ለማሻሻል የትምህርት ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚታየውን የትምህርት መቋረጥ ለመቀነስ በትምህርትቤት ምገባ መርሃ ግብርና አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት ችግሮችን ለማቃለል መታሰቡን አመላክተዋል፡፡

የሠላም ዘርፍ ኖቤል ተሸላሚና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም መልዕክተኛ ማላላ የሱፍ ዛይ በስሟ የሚጠራው ፋውንዴሽን ለሴት ተማሪዎች ትኩረት ሰጥቶ በዓለም ደረጃ የተለያዩ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውሳ፤ በኢትዮጵያም ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ተመሳሳይ ዕገዛ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች፡፡

ማላላ ፋውንዴሽን እ.ኤ.አ በ2013 በእንግሊዝና በአሜሪካ የተመሰረተ ሲሆን በሊባኖስ፣ ቱርክ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያና ሴራሊዮንን በመሳሰሉት ሀገራት በሴቶች ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ግዙፍ ዓለም ዓቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡

ትናንት በባህር ዳር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሶስት ሰዎች ሞቱ

ትናንትና በባህር ዳር ከተማ አባይ ማዶ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የሶስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡

በተጠቀሰው ስፍራ ባሉ የአካባቢው ሚሊሺያዎችና ሲፈለግ በነበረ በአንድ ግለሰብ መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ነው ችግሩ ሊደርስ የቻለው፡፡ ከዚህ ቀደም ተፈፅሞ ከቆየ ሌላ የግድያ ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥሮ ሲፈለግ ነበር የተባለውን ግለሰብ ሊይዙ ሲከታተሉ በነበሩት ሚሊሺያዎች ላይ ግለሰቡ ተኩስ ከፍቶአል፡፡

እንደሸፈተ ሲወራለት የነበረውን ግለሰብ ሲከታተሉ የቆዩት ሁለት የሚሊሻ አባላት ትናንት ዕሁድ ምሳ ሰዓት አካባቢ ተጠርጣሪው አለበት ወደ ተባለው ቤት ሲያመሩ፣ በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው ሲያልፍ፤ ተፈላጊው ግለሰብ ደግሞ በሌሎች የጸጥታ አባላት ተተኩሶበት ለሞት ተዳርጓል፡፡

በዚህ የተኩስ ልውውጥ የተመቱት ሁለት ሚሊሻዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ፤ ተፈላጊው ግለሰብ በጥይት ከቆሰለ በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ህክምና እየተደረገለት እንዳለ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ ሰኔ አስራ አምስት ቀን በክልሉ ባለስልጣናት ላይ ከተደረገው ግድያ ጋር በተያያዘ በድንጋጤና በጭንቀት ውስጥ የከረመው የባህርዳር ከተማ ነዋሪ፤ ትናንት ዕሁድ በተከሰተው የተኩስ ልውውጥ ዳግም ስጋት ውስጥ ገብቶ ታይቷል፡፡ ስለ ጉዳዩ የክልሉ መንግስትም ሆነ የባህርዳር ከተማ ፖሊስ ይፋዊ ማብራሪያ በፍጥነት አለመስጠቱ ደግሞ የነዋሪውን ድንጋጤ አግዝፎታል ማለት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረው የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ልዩ ስብሰባ ተጠናቀቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ልዩ ስብሰባውን አጠናቀቀ፡፡ ላለፉት አስር ቀናት በሀገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታዎች እንዲሁም አዳዲስ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጉዳይን የተመለከቱ ጥያቄዎች ላይ ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥልቅ ውይይት ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ፤ የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መክሮ አቋም እንደወሰደም ካወጣው መግለጫ መረዳት ተችሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ አስራ አንድ ዞኖች ተደጋግሞ የሚሰማውን ክልላዊ አደረጃጀትን በተመለከተ ዝርዝር ሳይንሳዊ ጥናት ተደርጎ የቀረበ ሲሆን ጊዜ ወስዶ በሳል ውይይት ተካሂዶበት ቀጣይ አቅጣጫን እንዳስቀመጠም ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማስቀጠል፣ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችንና ውጤታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በጽናትና በመርህ ላይ ቆሞ በመታገል ለላቀ ስኬት እንዲበቃ ማዕከላዊ ኮሚቴው በሙሉ መግባባት ላይ በመድረስ ጉባኤውን አጠናቋል፡፡

LEAVE A REPLY