ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም

ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በአቋማቸው የሚገመገሙበት አሰራር ቀረ

ኢሕአዴግ መንግስት ሆኖ ስልጣን ከጨበጠበት ጊዜ አንስቶ በተካሄዱት አምስት ምርጫዎች ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የገቡ አባላት፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በሚወስዷቸው አቋሞች የተነሳ የሚገመገሙበት አሰራር በ2011 ዓ.ም የፓርላማው ቆይታ ላይ በምንም መልኩ ተግባራዊ ሳይሆን መቅረቱ ተገለፀ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ለገሰ ጫፎ እንደሚሉት ከሆነ የፓርላማ አባላት ቀደም ባሉት ዓመታት “አዋጅ አናፀድቅም” ካሉ በማግስቱ ግምገማ ይካሄድባቸው ነበር፣ በዚህ የተነሳ በሁለተኛው ቀን አዋጁ ወደ ም/ቤት መጥቶ በሙሉ ድምጽ እንዲጸድቅ ይደረጋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ለበርካታ ጊዜያት ያለመከሰስ መብት ይነሳ ሲባል አባላቱ “አናምንበትም” ብለው ተከራክረው ከወጡ በኋላ ግምገማ ተካሂዶባቸው ሳያምኑበት፤ በቀጣዩ ቀን በሙሉ ድምፅ የሚፈለገው ሐሳብ ተግባራዊ የሚሆንበት የወረደ አሰራር በም/ቤቱ ለዘመናት ሲከናወን መቆየቱን ከዋና አፈጉባኤው ገለጻ መረዳት ተችሏል፡፡

“ድምጽ ያልሰጡ፣ የተቃወሙ እና የተለየ ሀሳብ ያራመዱ ሰዎች በግምገማ ተዋክበው፤ ለቀጣይ ምርጫ መቅረብ የሚችሉ ሰዎች ምርጫ ውስጥ እንዳይገቡ ሲደረግ ቆይቷል” ያሉት የተከበሩ አቶ ለገሰ ጫፎ፤ እነዚህ ግለሰቦች ከምክር ቤት ወጥተው የመንግስት ስራ ውስጥ ሲገቡ ብዙ መጉላላትና በደል እንደሚፈፀምባቸውም ይፋ አድርገዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ለይስሙላ በሕዝብ ተወካይነት ከመቀመጣቸው ውጪ ግምገማው ከኑሯቸው ጋር የተገናኘ በመሆኑ ህሊናቸው የሚያዛቸውን ከማድረግ ተገድበው ኖረዋልም ተብሏል፡፡ ይህ አሰራር በ2011 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል:: አባላቱም ህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት የምክር ቤት አባላት ህሊናቸው እንዳዘዛቸው በነፃነት ሲሳተፉ ታይተዋል፡፡

ለእዚህ በቂ ማስረጃ የሚሆነው በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ብቻ ሳይሆን፣ በአብላጫ ድምጽ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ሁኔታ መፈጠሩን እና የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የገለፁት የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ አቶ ለገሰ ጫፎ ወደ ፊትም ይህ ሙሉ ነፃነትን የሚሰጥ አሰራር በፓርላማው እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ኤችአይ.ቪ/ ኤድስ እንዳለባቸው የማያውቁ 12 ሺህ ነዋሪዎች መኖራቸው ተሰማ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው የኤች.አይ.ቪ ኤድስን በተመለከተ በኢትዮጵያ የሚወጡ መረጃዎች በእጅጉ አስደንጋጭ እየሆኑ ናቸው፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 12 ሺህ 200 ሰዎች ከኤች.አይ.ቪ ኤድስ ጋር እንደሚኖሩ ሳያውቁ ይኖራሉ ተብሏል፡፡

ከቻይና መንግስት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ የተበረከተለት “የጥሩነሽ ቤጂንግ” ሆስፒታል አደረግኩት ባለው ጥናት መሰረት መረጃውን ይፋ አድርጓል፡፡

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪጅ ዶክተር ጂብራል አባስ በአገር አቀፍ ደረጃ የኤች አይ ቪ ምጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመው፤ አዲስ አበባ ቫይረሱ ከተስፋፋባቸው ከተሞች ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ እንደምትገኝና ሶስት ነጥብ አራት የሚሆኑት ነዋሪዎቹም በቫይረሱ እንደተያዙ አረጋግጠዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 12 ሺህ 200 ያህሉ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ እንደማያውቁም ናሙና ተወስዶ በጥናት መረጋገጡን ያመላከቱት የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ፤ መንግስት በጉዳዩ ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ካልሰራ ባለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት ቸል የተባለው ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት ዓመታት ውስጥ ለመቆጣጠር ከሚያስችል አሳሳቢ አደጋ ላይ አገሪን ሊጥላት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው ከ17 እስከ 25 ዓመት የሚደርስ በርካታ ወጣቶች በልቅ የወሲብ ግንኙነት፣ አደንዛዥ እጾች መስፋፋትና ወያኔ/ኢህአዴግ በበሽታው ስርጭት ላይ ትኩረት ከመንፈጉ ጋር ተያይዞ ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸው ሲነገር መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

“ኢትዮጵያውያን እስካሁን የብሔር መሪ እንጂ፣ ትክክለኛ የአገር መሪ አላገኘንም”
አቶ ኦባንግ ሜቶ

ኢትዮጵያ በተተበተችበት የዘረኝነት ችግር እየታመሰች፣ ዕድገትንና ሰላሟ እየተሸረሸረ ከመሄዱ ባሻገር፤ አገሪቱ ያለችበት የፖለቲካ ሂደት ከተበላሸ መስመር ውስጥ ለመግባት እየተገደደ መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሚቶ ገለጹ፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛ መንስኤው ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሪ ሕዝቡ በማጣቱ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያኖች የተቋቋመውና ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ሕጋዊ ምዝገባ አካሂዶ የሃገር ቤት ቢሮውን የከፈተው “ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ” ሊ/መንበር አቶ ኦባንግ ሚቶ፤ አሁን በየቦታው “ክልል እንሆናለን” የሚሉ ምንም የማይፈይዱ ጩኸቶች እየበዙ ለመምጣታቸው ዋነኛ መንስኤው ኢትዮጵያዊነት ስሜት በውስጡ ጠብታ ያህል እንኳ የሌለው፣ በመለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው ሕወሓት ለክፉ ቀን ስንቅ እንዲሆነው ከአመታት በፊት የተከለው ሕገ – መንግስት መሆኑን ተናግሯል፡፡

“ወያኔ ኢትዮጵያዊነትን ከማለዳው ነው ማጥፋት የጀመረው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ቢኮሩበት ኖሮ በሕገ መንግስቱ ውስጥ የአገሪቱን አንድነት የሚጠብቁ የተለያዩ ሕጎችን ያስሰቀምጡ” ነበር የሚለው ኦባንግ ሚቶ፤ እነሱ በተንኮል የተሞላ ስራ ሲሰሩ በመኖራቸው ዛሬ ልጆቻችን በአሳዛኝ ሁኔታ በብሔርና በጎጥ ተከፋፍለው መደባደብና መገዳደል ጀምረዋል፤ በማለት እውነታውን በግልፅ አስቀምጦታል፡፡

ጋምቤላን ጨምሮ ሀገሪቱ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እየዋለለች እንደምትገኝ የሚናገሩት የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ፤ በተለይም ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ከመቼውም ጊዜ በላቀ የብሔር ፖለቲካ ከመጠን በላይ መራገቡና ስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ይህንን ሊቆጣጠር አለመቻሉ ችግሩ አድማሱን እንዲያሰፋ ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን አመላክተዋል፡፡

“ኢትዮጵያውያን እስከ ዛሬ ድረስ የብሔር መሪ እንጂ ትክክለኛ የአገር መሪ አላገኘንም፡፡ ይሄ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ መሪዎቻችን ከተወከሉበትና ከመጡበት ብሔር ፖለቲካ ርቀው፣ ለኢትዮጵያ ነው ማሰብና መስራት ያለባቸው፡፡” በማለት የሚናገረው ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ያለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሚቶ፤ “ ከምንም በላይ የአንድ ብሔር የበላይነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መቅረት አለበት፡፡ ከላይ እስከ ታች ያለውን ስልጣን ከአንድ ብሔር በተውጣጡ ሰዎች መያዝ ፈፅሞ መወገድ ይኖርበታል፡፡ ይህ ስሜት አሁን በአገሪቱ ውስጥ እየተንፀባረቀ ነውና” ሲሉ አቋማቸውን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን ለህትመት በበቃችው ግዮን መጽሔት ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይፋ አድርገዋል፡፡

የሱዳን አማፂ መሪ አዲስ አበባ ላይ ተይዘው ሊባረሩ እንደነበር ተሰማ

በሱዳን ለተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለማግኘት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ድርድር አንዱ የሱዳን አማጺ ቡድን መሪን አዲስ አበባ ላይ በቁጥጥር ስር ለማዋል ሙከራ ተደርጎ አንደነበር የሚጠቁሙ ዜናዎች በመውጣት ላይ ናቸው፡፡

ለበርካታ ዓመታት በዳርፉር ዋነኛ አማጺ ቡድን ሆኖ የቆየው “የፍትህና የእኩልነት እንቅስቃሴ” መሪ የሆኑት ጂብሪል ኢብራሂም የተሰኙት ሰው ናቸው ተይዘው ከኢትዮጵያ እንዲባረሩ ሊደረግ የነበረው፡፡

በሱዳን ታጣቂ ቡድኖችና በተቃዋሚዎቹ ጸረ መንግስት እንቅስቃሴ መካከል ድርድር ተካሂዶ፤ በሃገሪቱ ለወራት የዘለቀውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመቆጣጠር ወይም ለመቋጨት ያስችላል ተበሎ የታመነበት ስምምነት በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደርና በተቃዋሚዎች መካከል ስምምነት የተፈፀመው ከቅርብ ቀናት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ትናንት ዕሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሱዳን ፍትህና እኩልነት የተሰኘው ተቃዋሚ ቡድን መሪ የሆኑት ጅብሪል ኢብራሂምን፤ ከበርካታ ባልደረቦቻቸው መሀል ነጥለው በመያዝ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ ወስደዋቸው ነበር፡፡

በጉዳዩ ጣልቃ የገቡት የአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪዎች፣ ድርጊቱ በድርድሩ ላይ መጥፎ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል በመግለፅ የተቃዋሚ መሪውን ከአዲስ አበባ የማባረር ሂደት ሊያስቆሙት እንደቻሉ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ቢቢሲ የተፈጠረውን ክስተት ለማጣራት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ነቢያት ጌታቸውን ቢያናግርም ቃል አቀባዩ ስለ ጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ መናገራቸውንም አስታውቋል፡፡

ቻይና ጉዋንዡ እስር ቤት የምትገኘው ናዝራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረበች

እጽ በማዘዋወር ተጠርጥራ ቻይና ጉዋንዡ እስር ቤት የምትገኘው ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ናዝራዊት አበራ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረቧንና የመጨረሻውም የፍርድ ውሳኔ በቅርብ ይወሰናል በሚል በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ቤተሰቦቿ ገልጸዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አንስቶ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች ጭምር ጉዳዩዋን በቅርበት እየተከታተሉት የምትገኘው ናዝራዊት አበራ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበችው ከአንድ ወር በፊት ነው፡፡

ኢትዮጵያዊቷ በቻይና በእጽ ዝውውር ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር መዋሏ ከተሰማ ግን ስድስት ወራቶች ማለፋቸው አይዘነጋም፡፡ በቻይና ጉዋንዡ እስር ቤት ያለችው ናዝራዊት ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ስትቀርብ፤ 5 . 2 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን በሻምፖ መልክ የተዘጋጀ ኮኬይን የተሰኘ እጽ ማን እንደሰጣትና እንዴት ልትያዝ እንደቻለችም በዝርዝር ተናግራለች፡፡

የቻይና መንግስት ባቆመላት ጠበቃዋ አማካይነት ከአገር ወጥታ እንደማታውቅ የሚያሳይ የጉዞ ታሪክ ማስረጃ፣ ከወንጀል ነፃ ሆና መቆየቷን፣ በትምህርትና ስራዋም ኢንጅነር እንደሆነች የሚያመላክቱ መረጃዎችን አቅርባለች፡፡ ጉዳዩን አስመልክታ አስተያየቷን ለቢቢሲ የገለጸችው እህቷ ቤተልሔም አበራ “የቻይና ሕግ ከባድ ሳይሆን አይቀርም፤ እንዳሰብነው እየሄደ አይደለም፤ ግን ፈፅሞ ተስፋ አንቆርጥም” ብላለች፡፡ ናዝራዊት በድጋሚ ፍርድ ቤት መቼ እንደምትቀርብ ቁርጥ ያለ ቀን ባይታወቅም፤ በቻይና ሕግ መሰረት አንድ ሰው ፍርድ ቤት ከቀረበ ከሀያ ቀናት አሊያም ከወር በኋላ ብይን እንደሚሰጥ መረጃው ያላቸው መሆኑን ቤተሰቦቿ ገልጸዋል፡፡

በእስር ላይ ያላቸውን ናዝራዊትን በአካል ማግኘትና መጎብኘት ባይቻልም እሷ ግን ለቤተሰቦቿ ሁለት ጊዜያት ያህል ደብዳቤ ለመላክ ችላለች፡፡ ናዝራዊት በደብዳቤዋ ላይ “የተሳሳተ ሰው በማመኔ ቤተሰቦቼንም እኔንም ብዙ መስዋዕጥነት አስከፈልኩ፡፡ አይዞአችሁ፤ ወጥቼ አኮራችኋለሁ” የሚል መልዕክትም ማስፈሯን ቢቢሲዘግቧል፡፡  በቻይና ሕግ አንድ ሰው እፅ ሲያዘዋውር ከተገኘ የሞት ፍርድ ውሳኔ እንደሚተላለፍበት ይደነግጋል፡፡

ቦሌ አየር ማረፊያ በታሪኩ ከፍተኛ ነው የተባለ ደንበኞችን አስተናገደ

አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፤ ዓለም አቀፍ ተጓዦችን በማስተናገድ ታሪኩ በአንድ ቀን ውስጥ አስተናግዶ የማየውቀውን ከፍተኛ ቁጥር በማስመዝገብ ታሪክ መስራቱ ተሰማ፡፡

አየር መንገዱ ረቡዕ ሐምሌ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ብቻ 29 ሺህ 528 ዓለም አቀፍ ተጓዦችን በቦሌ አየር ማረፊያ አስተናግዷል፡፡ የፈረንጆቹ ሞቃታማ ወቅት ከሀገር ወደ ሀገር የሚንቀሳቀሱበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል የሚያልፉ ወይም መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ ተጓዦች ቁጥራቸው መጨመር የተፈጠረው ክስተት ዕውን እንዲሆን ምክንያት ሊሆን እንደቻለ እየተነገረ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዝና እና የአውሮፕላኖቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በቦሌ አየር ማረፊያ የዓለም ዓቀፍ ተጓዦች ቁጥር መጨመር ሌላኛው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

ይሄንኑ ክብረወሰን አስመልክቶ አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ረቡዕ ሐምሌ 10 ቀን ብቻ 310 በረራዎችን አስተናግዷል፡፡ በእዚህ በረራዎች ደግሞ 21 ሺህ 28 ተጓዞች መነሻቸውን ከቦሌ አየር መንገድ ማረፊያ ያደረጉ ሲሆን፤ 8 ሺህ 500 የሚሆኑት ደግሞ መዳረሻቸውን ቦሌ አየር ማረፊያ አድርገዋል ብሏል፡፡ መግለጫው ይህ ቁጥር የቦሌ አየር ማረፊያ ደንበኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ነው ሲልም ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡

LEAVE A REPLY