‹‹ግድያውን ብ/ጄ አሳምነው ጽጌ ብቻውን መርቶታል ማለት ከባድ ነው›› አቶ አምሳል ጌትነት...

‹‹ግድያውን ብ/ጄ አሳምነው ጽጌ ብቻውን መርቶታል ማለት ከባድ ነው›› አቶ አምሳል ጌትነት ከበደ (ኢንጂነር)፣ የቀድሞ ፖለቲከኛ

አቶ አምሳል ጌትነት ከበደ (ኢንጂነር) ተወልደው ያደጉት በቀድሞ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ጋይንት አውራጃ ታች ጋይንት ወረዳ፣ የታች ጋይንት ዓርብ ገበያ ከተማ ውስጥ በ1950 ዓ.ም. ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ ተምረው፣ ወደ ጎንደር በመሄድ በደብረ ታቦር ከተማ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንደጨረሱ፣ የቀድሞ ክቡር ዘበኛ ባልደረባ የነበሩት አጎታቸው፣ ጄኔራል ታደሰ ብሩ ጎንደር ጋይንት ለጉብኝት በሄዱት ወቅት በድብቅ ይዘዋቸው ወደ አዲስ አበባ አመጧቸው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ቀጥለው በ1967 ዓ.ም. በሚያጠናቅቁበት ወቅት፣ የመንግሥት ለውጥ ተደረገ፡፡ የንጉሡ አገዛዝ ተወግዶ ደርግ ሥልጣኑን ያዘ፡፡ አቶ አምሳልም የዕድገት በኅብረት ዘመቻ ዘመቱ፡፡ የሁለተኛና የሦስተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የመኢሶን አባላት አብረዋቸው ስለነበሩ እሳቸውም ይደግፉዋቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ለሁለት ዓመት የመኢሶን አባል ሆነው ከቆዩ በኋላ፣ በ1969 ዓ.ም. የኢሕአፓ አባል ሆነው አሠላለፋቸውን በመቀየር ሲታገሉ መቆየታቸውን፣ በኋላም ከእስራት በኋላ እስከ 1979 ዓ.ም. ድረስ በቀድሞው ሕንፃ ኮንስትራክሽን ውስጥ ሲሠሩ ቆይተው፣ በ1980 ዓ.ም. የራሳቸውን ድርጅት ‹‹ጉና ኮንስትራክሽን›› ድርጅት አቋቁመው በመሥራት ላይ እያሉ፣ ኢሕአዴግ የደርግን መንግሥት አሸንፎ በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን ያዘ፡፡ በሥራቸው ላይ የተፈጠረ ችግሩ ባለመኖሩ እስከ 1986 ዓ.ም. ድረስ የሠሩ ቢሆንም፣ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ሆነው የተሾሙት በክልሉ ያልተወለዱ ‹‹አማራ ነን›› ባዮች አስተዳደር በመቃወማቸው በአመራሮቹ አለመወደዳቸውን፣ በመሆኑም እሳቸውን ምክንያት ፈጥሮ ለማሰር በወቅቱ አቶ ታምራት ላይኔ ተመራጭ እንደሆኑ፣ ድርጅታቸው ‹‹ጉና ኮንስትራክሽን›› ከአቶ ታምራት ጋር እንደመሠረቱና አላስፈላጊ ሥራ ይሠራሉ በማለት እንዲታሰሩ ደብዳቤ በመጻፍና በአቶ መለስ ዜናዊ ፊርማ ወጪ በማድረግ፣ በወቅቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ ለነበሩት አቶ ክንፈ ገብረ መድኅን እንደደረሳቸው ያስታውሳሉ፡፡ ከአቶ ክንፈ ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለነበራቸው፣ የተጻፈባቸውን የእስር ደብዳቤ አሳይተዋቸው ከሚታሰሩ ከአገር ቢወጡ እንደሚሻል ሲነግሯቸው፣ በወቅቱ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረታቸውንና ሀብታቸውን ትተው ወደ እንግሊዝ አገር መሄዳቸውንና ከዚያም ወደ አሜሪካ ማምራታቸውንም ይናገራሉ፡፡ ይኼ ሁሉ የሆነው በ1989 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከአሥር ዓመታት የአሜሪካ ቆይታቸው በኋላ በ1999 ዓ.ም. በቅርቡ የተገደሉት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ወደ አሜሪካ ሄደው ካገኟቸውና ያለውን በደል ሁሉ ከተነጋገሩ በኋላ፣ ወደ አገራቸው ተመልሰው ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ አሳምነዋቸው መመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡ አምባቸው (ዶ/ር) የሥጋ ዘመዳቸውና አብሮ አደግ ጓደኛቸው ጭምር እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ አምሳል፣ በተለይ አምባቸው (ዶ/ር) ከፍተኛ አመራር ከሆኑ በኋላ ልዩ ግንኙነት እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ አቶ አምሳል ስለአምባቸው (ዶ/ር) እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ድንገተኛ ግድያና በአጠቃላይ የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከታምሩ ጽጌ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡    

ሪፖርተር፡- የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት በመሆን አራት ወራት እንኳን ሳያገለግሉ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሌሎች ሁለት አመራሮች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ውስጥ ከተገደሉት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ጋር ዝምድና እንዳለዎት፣ ከዝምድናም ባለፈ የጠበቀ ጓደኝነትና መቀራረብ ስለነበራችሁ እርስዎ በስደት ከሚገኙበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ስለነገሩኝ፣ እስቲ የእርሳቸውንና የእርስዎን ግንኙነትና በቅርቡ በድንገት ስለተፈጠረው ችግር ይንገሩን?

አቶ አምሳል፡- አመሰግናለሁ፡፡ ሦስቱንም ሟቾች አውቃቸዋለሁ፡ አምባቸው (ዶ/ር)፣ አቶ እዘዝና አቶ ምግባሩ በጣም ጠንካራ፣ የመርህ ሰውና ለክልላቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ሊጠቅሙ የሚችሉ ሐሳበ ጠንካራና የሚያምኑበትን ነገር የማይለቁ ቆራጥ አመራሮች ነበሩ፡፡ አስተዋይና ገና ብዙ መሥራትና ሊያድጉ የሚችሉ ልጆች ነበሩ፡፡ የአገርና የወገን ፍቅራቸው ጠንካራ ነበር፡፡ እኔን አሳምነው ወደ አገሬ እንድገባ ያደረጉኝ አምባቸው (ዶ/ር) እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ናቸው፡፡ የእኛ አካባቢ (ጋይንት) ለከተማ በጣም ርቀት ያለው በመሆኑ ብዙም የተማረ አይወጣበትም፡፡ በተለይ እኔ በነበርኩበት በ1970 ዓ.ም. አልፎ አልፎ ካልሆነ እምብዛም የተማረ የለም ነበር፡፡ አምባቸው ግን በጣም የሚገርምና አስደናቂ ችሎታ ያለው ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ስለኢትዮጵያ የነበረው ህልም እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ብሩህ አዕምሮ የነበረው አመራር ነበር፡፡ እኔን ለማሳመንና ወደ አገር ቤት ለመመለስ ከአቶ ዮሐንስ ጋር አሜሪካ በመጡበት ጊዜ ጥሩ ኑሮና ሥራ እንዳለኝ ከተመለከቱ በኋላ አምባቸው፣ ‹‹ጥሩ ኑሮ ትኖራለህ፡፡ ገቢህም ቆንጆ ነው፡፡ ባደገና ንፁህ አገርም እየኖርክ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ይኼ ሁሉ ሀብትና ምቾት ከሕዝብህ ጋርና ከኢትዮጵያ ጋር ቢሆን ደስ ይል ነበር፡፡ ከአገርህ ርቀህ የምታፈራው ሀብትና የምታገኘው ምቾት ከንቱ ነው፡፡ ወደ አገርህ መግባት አለብህ፤›› ብሎ እንድመለስ ያደረገኝ ወጣት አመራር ነበር፡፡ ይኼ የሚያሳየው ምን ያህል የአገር ፍቅር እንደነበረው ነው፡፡ እኔ ወደ አገሬ ገብቼ አንድ ጠጠር ብወረውር ብዙ ጥቅም እንዳለው፣ ኢትዮጵያ የተማረ የሰው ችግር ብቻ ሳይሆን ያለባት የአገር ፍቅር ያለው ሰው ማጣቷ መሆኑን ጭምር በመንገር እንድመለስ አድርጎኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አምባቸው (ዶ/ር) ግላዊ ባህሪያቸው እንዴት ነበር? ቁጡና ቀጥተኛ ናቸው ይባላል፡፡

አቶ አምሳል፡- አምባቸው ቀልደኛና ተጫዋች ነው፡፡ የሚናደድበት ጊዜ ከደቂቃዎች አያልፍም፡፡ እሱም አንዳንድ ጊዜ ድንገት የሚያናድደው ነገር ሲያጋጥመው እንጂ፣ ሁሉን ነገር የሚያየው በትዕግሥት ነው፡፡ ከሰዎች ጋር መግባባቱ፣ ቀልዱና ሳቁ ጥርስ አያስገጥምም፡፡ የአቋም ሰው በመሆኑ ለሚወስደው ዕርምጃ ስለማያመነታና ፊት ለፊት በመሆኑ ‹‹ቀጥ ያለ ነው›› የሚሉት ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለቱ የክልሉ አመራሮች አምባቸው (ዶ/ር) እና አቶ ዮሐንስ አሜሪካ ድረስ መጥተው ወደ አገርዎ እንዲመለሱ ያቀረቡልዎትን ማሳመኛ ተቀብለው ተመለሱ? ወይስ ምላሽዎ ምን ነበር?

አቶ አምሳል፡- እኔማ ስላሳመኑኝ መጣሁ፡፡ የሚገርመው ነገር እኔ እንደመጣሁ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ከአመራርነት እንዲነሳ ተደረገ፡ አምባቸውም ለሦስተኛ ዲግሪ ወደ እንግሊዝ ሄደ፡፡ የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር አምባቸው ወደ እንግሊዝ ዶክትሬቱን ሊማር የሄደው ክልሉ ሊከፍልለት ተስማምቶ ቢሆንም፣ እነ አቶ በረከት ስምዖን ክፍያው እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሰጥተው ተቋረጠ፡፡

ሪፖርተር፡- አቶ በረከት ስምዖን የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣን ነበሩ፡፡ ክልሉ ደግሞ የራሱን ውሳኔ በራሱ የሚወስንበት ሕገ መንግሥትና ሥርዓት አለው፡፡ እንዴት በእሳቸው ሥልጣን ለአምባቸው (ዶ/ር) የተወሰነው የትምህርት ቤት ክፍያ ሊቋረጥ ይችላል?

አቶ አምሳል፡- በወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ነበሩ፡፡ እሳቸው ለይስሙላ ፕሬዚዳንት ይሁኑ እንጂ፣ ክልሉ ይመራ የነበረው በአቶ በረከትና በአቶ አዲሱ ለገሠ ነበር፡፡ አቶ አያሌው በጣም ጥሩ ሰው ቢሆኑም፣ አድርጉ የተባሉትን ስለሚያደርጉ ለአምባቸው የተሰጠውን የስኮላርሽፕ ክፍያ እንዲያቋርጡ ሲታዘዙ አቋረጡ፡፡ አምባቸው በማያውቀው አገር ክፍያ ሲቋረጥበት የሚበላው፣ የሚጠጣውና የሚኖርበት ሁሉ ይቆማል ማለት ነው፡፡ የሚኖረው ነፃ ነገር አየሩ ብቻ ነው፡፡ ለጊዜውም ቢሆን የሚረዳው ዘመድም አልነበረም፡፡ በወቅቱ ግራ ሲገባው እኔ ጋ ደወለልኝና የሆነውን ሁሉ ነገረኝ፡፡ ወደ አገር ቤት ሊመለስ መሆኑን ሲነግረኝ የተቻለውን ሁሉ አድርገን ትምህርቱን መቀጠል እንዳለበት ተማምነን እያለ፣ ውሳኔውን የሰሙ የብአዴን ካድሬዎች ተሰብስበው ‹‹ከደመወዛችን እየተቆረጠ ስኮላርሽፑን መቀጠል አለበት›› ብለው ውሳኔ አሳለፉ፡፡ የካድሬዎቹ ውሳኔ ስላስደነገጣቸውና ስላስፈራቸው እነ አቶ በረከት አቋርጠውት የነበረው ክፍያ እንዲቀጥል አደረጉ፡፡ አምባቸው ተምሮ ከመጣ በኋላም ተለያየ ነገር በማድረግ እነ አቶ በረከት የበታችነት ስሜት እንዲሰማው ሲያደርጉት ኖረዋል፡፡ ጊዜው ሲደርስና የእሱም ጥንካሬ እየቀጠለ መጥቶ የክልሉ ሕዝብና አመራሮችም ስለእሱ በማወቃቸው፣ የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበርና የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመርጦ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አምባቸው (ዶ/ር) ተሹመው በቆዩበት አጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ አደጋ ይደርስባቸዋል ብለው አስበው ያውቃሉ?

አቶ አምሳል፡- አምባቸው እንዲህ በአጭር ጊዜና ባልተጠበቀ ሁኔታ ይገደላል ወይም ይሞታል ብዬ አልገመትኩም፡፡ ይሁንና የብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ሁኔታ ግን አይጥመኝም ነበር፡፡ አምባቸውን፣ እዘዝን ወይም ምግባሩን ይገድላቸዋል የሚል ጥርጣሬ አልነበረኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ያልጣመዎት ታዲያ ምንድነው?

አቶ አምሳል፡- ከትግራይ ክልል ጋር የሚያደርገው ትንኮሳ፣ ያልሆነ ውጊያና ከጎረቤት ጋር ለመክፈት የሚያደርገው የጀብደኝነት እንቅስቃሴ አይመቸኝም ነበር፡፡ ይኼንን የምለውም እኛ ኢትዮጵያ አንድ ነች ብለን ማመን አለብን የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር ትገናኙ ነበር?

አቶ አምሳል፡- አዎ እንገናኝ ነበር፡፡ ይኼንን ትንኮሳህን አቁም፡፡ በተለይ በስልክ፣ ‹‹ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?›› ብዬ እንዲያቆም እመክረው ነበር፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ዓመት ለአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለመመረጥ ፈልጎ፣ ‹‹አንተ ሁሉንም ስለምታውቅ ንገርልኝ፣ አሳምንልኝ፤›› በማለት ለምኖና የሚያውቀውን ሰው ሁሉ ጠይቆ መመረጡን ስለማውቅ እመክረው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ሁሉንም የክልሉን ባለሥልጣናት ያውቋቸዋል እንዴ?

አቶ አምሳል፡- አዎ አውቃቸዋለሁ፡፡ አንዳንዶቹ አብረን በኢሕአፓ ውስጥ የነበርን ነን፡፡ በኋላም ወደ አመራርነት የመጡትን ወጣቶቹንና ታዳጊዎቹንም አውቃቸዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚያ ምን አደረጉ? አግባብተው አሳመኑላቸው?

አቶ አምሳል፡- አንዳንዶቹን አባላት ሳነጋግራቸው፣ ‹‹ያላግባብ በሕወሓት አመራሮች ተገፍቶ የታሰረ ነው፣ ሊያገለግል ይችላል…›› ሲሉኝ የእኔ ጥያቄ የነበረው ታዲያ፣ ለምን ወደነበረበት አገር መከላከያ ተመልሶ በእስር ላይ በቆየበት ጊዜ ያለፈው የማዕረግ ዕድገት ተሰጥቶት እንዲያገለግል አይደረግም የሚል ነበር፡፡ የእሱ ፍላጎት ግን ወደ መከላከያ ሠራዊቱ መመለስ ሳይሆን፣ የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆኖ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል መሆኑን በመናገር ወደ መከላከያ ሠራዊት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞና ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እንዲገቡ ሐሳብ ማቅረቡን ነገሩኝ፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራና ኮሎኔል ደመቀ፣ ‹‹አሳምነው የፖለቲካ ሰው ስለሆነ እሱ ማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ቢገባ ጥሩ ነው፤›› የሚል አስተያየት ሰጡ፡፡ በሕዝብ ዘንድም የሚታወቅ በመሆኑ አባላቱ ተነጋግረው እንዲመረጥ በመስማማታቸው ተመረጠ፡፡ ለተወሰነ ጊዜም ጥሩ ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ በተለይ ጎንደር ውስጥ ግማሽ ጎኑ ትግሬ ግማሽ ጎኑ ጎንደሬ ሆኖ ያልተጋባና ያልተዋለደ የለም፡፡ የማይረባ የዘረኝነት ፖለቲካ ደቅነውብን ነው እንጂ ሁለቱም ልዩነት የላቸውም፡፡ በእነዚህ ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ዘንግቶ ለትንኮሳ መዘጋጀት ትክክል አይደለም፡፡ አሳምነው ይኼንን ሲያደርግ እቃወመው ነበር፡፡ በሚሰጣቸው መግለጫዎችና በየመድረኩ በሚያደርጋቸው ንግግሮች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እመክረው ነበር፡፡ የአማራ ሕዝብ ታጋሽ ነው፡፡ ማንኛውንም ነገር ችሎና ታግሶ የመኖር ብቃትና ልምድ አለው፡፡ የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት አስፈላጊ በመሆኑ በመንደርና በጎጥ ላይ ማነጣጠሩን እንዲተው በተደጋጋሚ እመክረው ነበር፡፡ የአማራ ሕዝብ በደሙ ውስጥ ያለው ኢትጵያዊነት ነው፡፡ አማራ፣ አማራ እያለ የሚያስተላልፈውን ዋልታ ረገጥ አካሄድ እንዲያቆምና ኢትዮጵያዊነትን መሠረት እንዲያደርግ ተመክሮ አንዳንድ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎቹ ቀንሶ ነበር፡፡ ግን ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ፡፡

ሪፖርተር፡- የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች ግድያ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ ግድያው በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው እንደተቀነባበረና እንደተፈጸመ የፌዴራል ከፍተኛ ባለሥልጣናት (ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ) ጭምር ቢናገሩም፣ ግድያ በእሳቸው እንዳልተፈጸመ የተለያዩ ትንታኔዎችንና መላምቶችን የሚያስቀምጡ አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ አምሳል፡- እኔ አንድ የማውቀውን ነገር ልንገርህ፡፡ ‹‹የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው›› ተብሎ በዕለቱ በፌስቡክ በጉልህ ወጥቶ ነበር፡፡ እንዳነበብኩት ወዲያውኑ ወደ ቅርብ የሥራው ባልደረባው አቶ ዮሐንስ ቧያለው ዘንድ ብደወልምና አጭር ጽሑፍ ብልክም ምላሽ በማጣቴ፣ ለአምባቸው ቅርብ ናቸው ላልኳቸው ብደውልም ምላሽ አጣሁኝ፡፡ የክልሉ ተወላጅ ለሆኑት ለፌዴራል ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ብደውልም ምላሽ አላገኘሁም፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዘንድ ብደውልም ምላሽ አጣሁኝ፡፡ ለካስ አቶ ደመቀም ያሉት አሜሪካ መሆኑን ያወቅኩት ቆይቼ ነው፡፡ በመጨረሻ የሁሉም ስልክ እንቢ ሲለኝ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጋ ደወልኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የክልሉ የፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው መሆናቸውን ያውቃሉ፡፡ የግድያ ሙከራ የተፈጸመውም በአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ላይ መሆኑን እንዳነበቡና የቅርብ የሥራ ባልደረቦቻቸው ስልክ አልነሳ ሲልዎት፣ ወደ ፌዴራል ባለሥልጣናት ከመደወል ይልቅ ለምን ወዲያውኑ ለክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አልደወሉም?

አቶ አምሳል፡- ለእሱም ደወልኩ እኮ፡፡ ከምሽቱ 1፡58 ሰዓት ላይ ስደውልለት አነሳልኝ፡፡ ‹‹አሳምነው ምንድነው የምሰማው?›› ብዬ ጮህኩበት፡፡ ‹‹አይ ኢንጂነር ተመታታን፤›› አለኝ፡፡ ምን? ተመታታን? ምንድነው የምታወራው? ንገረኝ እንጂ ስለው፣ ‹‹እያረጋጋሁ ነውና እደውልልሃለሁ፤›› ብሎ ስልኩን ዘጋ፡፡ ይኼ ንግግር በቴሌ የሚረጋገጥ ስለሆነ ነው እየነገርኩህ ያለሁት፡፡ እስከ ምሽቱ 4፡15 ሰዓት ድረስ ስደውል ስልኩ ተይዟል ይላል፡፡ መጨረሻ ላይ አምባቸው መሞቱን አረጋገጥኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ አምባቸውን (ዶ/ር) የገደሉት እነ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ናቸው እያሉ ነው?  

አቶ አምሳል፡- በወቅቱ በቦታው የተደረገውን እያንዳንዱን ሒደት አላውቅም፡፡ ሌላውን የማውቀው እንደ ሕዝቡ ነው፡፡ እኔ የማውቀው ግን ከራሱ አንደበት፣ ‹‹ተመታታን፤›› ያለኝኝ ነው፡፡ መመታታት ጥፊ አይደለም፡፡ መመታታት በጥይት ነው፡፡ መሞቱንም አውቄያለሁ፡፡ ‹‹እንዴት ተመታቱ?›› መርማሪ ይዞታል፡፡ ‹‹ተመታታን፤›› ሲለኝ ግን የራሴን ትንተና ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ምንድነው የሠሩት ትንተና?

አቶ አምሳል፡- በራሱ ይግደል? ወይም ሰው ያስገድል? ትዕዛዝ ሰጥቶ ያስገድል? እንዴት ያቀናጀው? ምንም የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ በግድያው ላይ ግን እሱ እንዳለበት የሚያጠራጥረን ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ ላይ የተፈጠረው አደጋ ድንገተኛ ነው፡፡ ክልሉን በብቃት እንደሚመሩ እምነት የተጣለባቸውና በክልሉ ሕዝብም ከፍተኛ ድጋፍ እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ከፍተኛ አመራሮችን በድንገት ማጣት፣ በክልሉ ላይ ችግር ወይም የአመራር ክፍተት ይፈጠራል ብለው ያምናሉ?

አቶ አምሳል፡- መደባበቅ ካላስፈለገ በስተቀር አዎ፡፡ የአምባቸውን ጫማ የሚሞላ ሰው ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ምናልባት ያንን ክፍተት በመሙላት ሊያስተካከል የሚችለው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይመስለኛል (ቃለ መጠይቁ በተደረገላቸው ጊዜ አሁን ዕጩ ሆነው ስለቀረቡት አመራሮች የተባለ ነገር አልነበረም)፡፡ አቶ ገዱ አቅም ያላቸውና ክልሉን ለመምራት እንዲችሉ ተደርገው የተፈጠሩ ሰው ናቸው፣ ስለማውቅ ነው፡፡ አቶ ገዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ብዙ ቢባልም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳዩት ብቃት ብዙ እንዲባልላቸው እያደረገ ነው፡፡ ለነገሩ የአማራን ሕዝብ መምራት የቻለ ሰው፣ ኢትዮጵያን መራ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ክልሉን በተፈለገው ፍጥነት ለማስተካከል ለእኔ የሚታየኝና መሆንም ያለበት ገዱ አንዳርጋቸው ብቻ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደሚሉት አቶ ገዱ ክልሉን ለመምራት ብቃት ያላቸው ቢሆንም፣ በራሳቸው ፈቃድ ከክልሉ ፕሬዚዳንትነት የለቀቁት በክልሉ አመራሮችና በሕዝቡ ጫና መሆኑ ተነግሯል፡፡ በዚህ ሁኔታ እሳቸውም ሆኑ የክልሉ አመራርና ሕዝብ ሊቀበላቸው ይችላል ብለው ያስባሉ?

አቶ አምሳል፡- እኔ ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ ከፖለቲካ ነፃ አይደለሁም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ከፖለቲካ ውጪ አይደለም፡፡ እኔ ደግሞ ገና ከ19ኛ ዓመቴ ጀምሮ ፖለቲካ በውስጤ አለ፡፡ አንዴ ንድፈ ሐሳቡ ውስጥህ ገብቶ ከሰረፀ በኋላ ቁስ አካላዊ ኃይል ይሆናል፡፡ ይኼ በመሆኑም እኔ እንኳን የአገሬን የአሜሪካን ሕግና ሕገ መንግሥት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ የአቶ ገዱ የመምራት ብቃትም ሆነ የፖለቲካ ብቃት አልተሸረሸረም፡፡ አማራን አንድ አድርጎ መምራት የሚችል ጠንካራ ሰው እንዳይኖር የሚፈልግና የአማራ ጠላት የሆነ እኩይ ተግባር ያለው የሚቀሰቅሰው ቀሽም የፖለቲካ ተግባር ካልሆነ በስተቀር፣ አቶ ገዱ የክልሉን ህልውና ለማስጠበቅ ተቀዳሚ ሰው ናቸው፡፡ አቶ ገዱ ተጠራጣሪ በመሆናቸው ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጋር ሳይስማሙ ቀርተው ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ጄኔራሉ ሳይቀድማቸው ክልሉን የለቀቁት፡፡ አምባቸው የዋህና ቅን ልቦናው ስለሚያበዛ ሕይወቱን ሊያጣ ችሏል፡፡ በአቶ ገዱ ላይ ብዙ ተብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ላይም ብዙ ተብሎ ነበር፡፡ ያልሠሩትን ሥራ ሠሩ ሲባል፣ ቻይና ታጋሽ በመሆናቸው ወይም ‹‹አልሠራሁም›› ብለው መድረክ ላይ ወጥተው ቢናገሩ ሊጠፉ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ ጊዜን ጠበቁ፡፡ ጊዜው ሲደርስ ግን ሕዝቡ እውነቱን አወቀ፡፡ አቶ ደመቀ ያሉበት ሥልጣን ወደኋላ የሚመለሱበት ባይሆንም አቶ ገዱ ግን ያሉበት ሥልጣን ከክልሉ ስለማይበልጥ ወይም አማራ ክልል ማለት ኢትዮጵያ ማለት ስለሆነና አማራ ክልል ፈረሰ ማለት ኢትዮጵያ ፈረሰች ማለት ስለሆነ፣ ወይም አማራ ክልል ጠነከረ ማለት ኢትዮጵያ ጠነከረች ማለት ስለሆነ፣ አቶ ገዱ ወደ ክልል ተመልሰው ክልሉን የመምራትና የማረጋጋት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አቶ መለስ በአንድ ወቅት፣ ‹‹ኦሮሞን ብትፍቀው ኦነግ ነው፤›› ከሚሉ ይልቅ፣ ‹‹አማራን ብትፍቀው ኢትዮጵያ ነው፤›› ቢሉ የተሻለ አባባል ሆኖ ግኝቼዋለሁ፡፡ ምክንያቱም የአማራ ጥንካሬ የኢትዮጵያ ጥንካሬ፣ ወይም የአማራ አንድነት የኢትዮጵያ አንድነት፣ ወይም የአማራ ውድቀት ኢትዮጵያ ውድቀት መሆኑን ሊታወቅና ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በመሆኑም አቶ ገዱ ከአርሶ አደሩም ሆነ ከምሁሩ ጋር ተስማምተው ክልሉን መምራት የሚችሉ የወቅቱ ፖለቲካኛ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አቶ ገዱ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው በሚመሩበት ወቅት በተለያዩ ክልሎች ወይም አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉ፣ ንብረታቸውን ሲነጠቁና እንግልትና ሥቃይ ሲደርስባቸው የወሰዱት ዕርምጃ ወይም ያደረጉት ድጋፍም ሆነ አስተዋጽኦ ስለሌለ፣ የክልሉን ሕዝብ ማስተዳደርና መምራት አይችሉም የሚሉትን በሚመለከት እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ አምሳል፡- እውነቱን ለመናገር ‹‹አቶ ገዱ ሥልጣን የነበራቸው መቼ ነበር?›› ብለን ብናወራ ከአንድ ዓመት ወዲህ በ2010 ዓ.ም. ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነው፡፡ በዚህ አገር ለውጥ የተገኘው እነ አቶ ገዱና አቶ ደመቀ ዓብይን ተባብረው ወደ ሥልጣን ካመጧቸው በኋላ ነው፡፡ በሕወሓት የሥልጣን ዘመን እንኳን ክልልና አገር መምራት ቀርቶ ሲተነፍሱ እንኳን አስፈቅደው የሚተነፍሱ ነው የሚመስለኝ፡፡ ሰው እየተሰደደ መኖር አይፈልግም፡፡ እየተሰደቡና ‹‹‹አገር ሻጭ›› እየተባሉ አቶ ደመቀ ፀጥ ያሉት ለምንድነው? ምንም ማድረግ ስለማይችሉ እንጂ፣ ልበ ደንዳናና ደፋር ፖለቲከኛ መሆናቸውን በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ ያላወቀና እውነታውን ያልተረዳ የለም፡፡ ሁሉም ነገር በአንድ ብሔር ተይዞ በነበረበት ወቅት ምንም ማድረግ የማይችሉ አመራሮችን፣ ‹‹ለምን ዝም አሉ? ይኼንን ለምን ፈረሙ? ለምን በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን አለቀቁም?›› የሚለው ዋጋ አልነበረውም፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ማን ምን እንደሆነና ለአማራ ሕዝብ ያላቸውን ሁሉ በማሳየት ላይ መሆናቸውን መመልከት በቂ ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ በመላ አገሪቱ የተቀበረው ፈንጂ እዚያና እዚህ እየፈነዳ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ራስ ምታት፣ ለኢትዮጵያም መከራ የሆነውን መመልከት በቂ ነው፡፡ ሁሉንም የአማራ ክልል አመራሮች መውቀስ የሚቻለው ከአንድ ዓመት በኋላ ያደረጉት ወይም የፈጸሙት ጥፋት ካለ ብቻ ይመስኛል፡፡ ምክንያቱም በ27 ዓመታት ውስጥ ሙሉ ሥልጣን አልነበራቸውምና፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለውን የፌዴራል አመራር ወደ ሥልጣን ያመጡት በአቶ ገዱ የሚመራው የአማራ ክልል አመራርና በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኦሮሚያ ክልል አመራር ወይም ‹‹ኦሮማራ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የለውጥ ቡድን መሆኑ ይነገራል፡፡ ነገር ግን የሁለቱ ክልሎች አመራሮች አሁን የሚታየውን ለውጥ ያመጡ ቢሆንም፣ የአማራ ክልል አመራሮች ግን ቀደም ብሎ ለነበረው የኢሕአዴግ አመራር ያደርጉ እንደነበረው የኦዴፓ ተከታይ ሆነዋል እንጂ፣ ለክልላቸው ያመጡት ለውጥ እንደሌለ የሚነገረውን እንዴት ያዩታል?

አቶ አምሳል፡- በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም በጡረታም ሆነ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ‹‹ክልሉን እንወክላለን›› ይሉ የነበሩ የኢሕአዴግ አመራሮች፣ አሁንም ቢሆን አርፈው የሚቀመጡ አይመስለኝም፡፡ የሞተ ፈረስ ጋላቢዎች ናቸው፡፡ መናፍቃን በመሆናቸው የቀድሞ አመራር የሚመለስ ይመስላቸዋል፡፡ አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን፣ የኢትጵያን ሕዝብ ከዚህ በኋላ ‹‹በካርድ›› ያልተመረጠ መሪ ማንም ቢፈልግ ሊመራው አይችልም፡፡ የሰው አስተሳሰብ ተለውጧል፡፡ ነገር ግን የዓብይ አመራር ወደ ሥራ ከገባ በኋላ እንኳን አቶ በረከት ስምዖን ትግራይ ክልል ሄደው ምን ይሠሩ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ሌሎቹ ቀደም ብለው በለዘብተኝነት እንደሚያደርጉት ፀጥ ብለው ምን እያደረጉ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ አሁን መጠየቅ ያለብህ የቀድሞ ብአዴን (አዴፓ) መዋቅር ውስጥ የነበረው አመራር ተነቅሎ አልቋል? የሚለውን ነው፡፡ ምን ያህል ፀድቷል? ለእነ አምባቸው መሞትስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ይታወቃል? የክልሉና የፌዴራል የምርመራ ቡድን የታሪክ ተወቃሽ ስለሚሆን ነገ አጣርቶ እውነቱን ለሕዝብ ይፋ ሲያደርግ ከሚረጋገጥ በስተቀር፣ አሁን ጠንቅቆ ማወቅ አይቻልም፡፡ በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው፣ የአማራ ክልል አመራሮችን ገዳይ በማጣራት ላይ የሚገኘው የምርመራ ቡድን ምክንያቱንና ውጤቱን ለሕዝብ መናገር አለበት፡፡ ይኼንን ካላደረገና እውነቱን ካልተናገረ ለአማራ ክልል ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ጠላት ይሆናል፡፡ የብአዴን መዋቅር ጠቅላላ ተቀይሯል ወይ? ብለህ ብትጠይቀኝ፣ የእኔ መልስ ‹‹አይመስለኝም›› ነው፡፡ ለአመራሮቹ መሞት ቅንብሩ የእሱ ቢሆንስ? ይኼ የሚታወቀው ከምርመራው ውጤት በኋላ በመሆኑ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ አቶ ገዱን እንዳይሠሩ ያደረጉት ለአምባቸው (ዶ/ር) መሞት ምክንያት አይሆኑም የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኔ ከ40 ዓመታት ባለኝ የፖለቲካ መረዳት አቶ ገዱንና አቶ ደመቀን በደንብ አውቄያቸዋለሁ፡ እንደ እነ አምባቸው (ዶ/ር) ሕይወት ባይሰጡም በብዙ ነገር መስዋዕት ሆነዋል፡፡ አሁንም ርዝራዦቹ ስላሉ ቀጣይ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የክልሉን ወቅታዊ ክስተት ሊያስተካክሉና የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት ሊሞሉ የሚችሉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው ቢሉም፣ አሁን በክልሉ የሚገኙ አመራሮች ደግሞ ምንም እንኳን ያጧቸው አመራሮች ጠንካራና ብቃት የነበራቸው ቢሆኑም፣ እነሱን የሚተኩ በርካታ አመራሮች ያሉ መሆኑን እየተናገሩ ስለሆነ የእርስዎ አስተያየትም ምንድነው?

አቶ አምሳል፡- የአቶ ደመቀ መኮንን ወደ ክልል መሄድ የማይታሰብ ነው፡፡ በሚመጥናቸው ቦታ ላይ ናቸው፡፡ አቶ መለስ እንደሞቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የሚገባቸው አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሳይሆኑ አቶ ደመቀ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነ አቶ በረከት በሠሩት ሴራና በአማራ ሕዝብ ላይ ባላቸው ጥላቻ፣ የብአዴንን ድምፅ ለደኢሕዴን ሰጥተው ዕድሉን እንዳያገኙ አደረጉ፡፡ ወደ ጠየቅከኝ ጥያቄ ስመለስ፣ አሁን የክልሉን ክፍተት ለመሙላት በእኔ ግምት የመጀመርያዎቹ አመራሮች አቶ ገዱና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ናቸው (ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አቶ ዮሐንስ የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ከመሰየማቸው በፊት ነው)፡፡ አቶ ዮሐንስ ምሁር ናቸው፡፡ አልወለዷቸውም እንጂ ያላሠለጠኗቸው ካድሬዎች የሉም፡፡ ሁሉንም ያስተማሩ ናቸው፡፡ የሚያምኑበትን ነገር ከማድረግ የሚያግዳቸው የለም፡፡ የመርህ ሰው ናቸው፡፡ ፍርኃት አያውቁም፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ክልሉን መምራትም ሆነ ክፍተቱን መሸፈን ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ከተሾሙ በኋላ፣ ክልሉ በፀጥታ በኩል አስተማማኝ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበርና ይኼም የሆነው እሳቸው በተለይ የክልሉን ወጣቶች በማቅረብና በማደራጀት ውጤታማ ሥራ በመሥራታቸው መሆኑን የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡  የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ አምሳል፡- አሁን አዲስ የፀጥታ ኃላፊ ተሹመዋል፡፡ አቶ አገኘሁ ተሻገር ይባላሉ፡፡ ለቦታው ብቁ ናቸው፡፡ ሀቀኛ፣ እውነተኛና ደፋር ናቸው፡፡ ጎንደር እንደ ዛሬ ሳይከፋፈል አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው የተሻለ ሥራ ይሠራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ይኼንን የምናገረው ግለሰቡን በደንብ ስለማውቃቸው ነው፡፡ በማንነታቸው የማይደራደሩና ኢትዮጵያን የሚወዱ በመሆናቸው ለቦታው የሚመጥኑ ናቸው፡፡ ካመኑበት ውጪ ሌላ ነገር ስለማያደርጉ በእነ አቶ በረከት ትዕዛዝ እንዲታሠሩ ትዕዛዝ ተሰጥቶ በአቶ ገዱና በአቶ ደመቀ ጥረት ነው የተረፉት፡፡ እስካሁን የነበሩበት ቦታ እሳቸውን ማግለያ እንጂ፣ በብቃታቸው ልክ መሥራት በሚችሉበት ቦታ አልነበሩም፡፡ አሁን ግን ትክክለኛውን ቦታ ያገኙ ይመስለኛል፡፡ ከክልሉ ወጣቶችም ጋር በደንብ የሚተዋወቁ ስለሆኑ፣ ለፀጥታ ሥራው ትክክለኛ ሰው ናቸው ለማለት እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የክልሉ አመራሮች መገደል፣ ክልሉ እንዲጠናከር ለማይፈልጉ፣ በክልሉ ፖለቲካና አመራር ውስጥ እጃቸውን ማስገባት ስለሚፈልጉ በር መክፈቱን የሚናገሩ አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ አምሳል፡- ይኼንን ጥያቄ በሁለት ከፍዬ አየዋለሁ፡፡ በአንድ በኩል ጠላቶች እንደሚያስቡት ሳይሆን፣ የአማራን ሕዝብና አሁን በአዲስ መልክ የተዋቀረውን አዴፓ ላልተረዳ ሥጋቱን ቢገልጽ ትክክል ነው፡፡ ግን ብቃት ያላቸው አመራሮች አሉ፡፡ አቶ ደመቀን እንኳን ብንወስድ ከአንድ ዓመት በፊት በደንብ አይታወቁም ነበር፡፡ አሁን ነው ገና እየታወቁ ያሉት፡፡ አመራር ላይ የነበሩ ግን ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር፡፡ ስለዚህ አዴፓ የሰው ችግር እንደሌለበት ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ አንድ ሰው ወደ መድረኩ ወጥቶ ካልተፈተሸ ብቃቱ አይታወቅም፡፡ እስካሁን በሥጋትና በመሸማቀቅ ወደፊት ያልወጡም ይወጣሉ፡፡ የሞቱትን የሚተኩ ብዙ ወጣቶች አሉ፡፡ ስለዚህ የሚዳከም ነገር የለም፡፡ ወይም አጃቸውን ለማስገባት የሚፈልጉ ቢኖሩም እንዳለፈው ጊዜ ዝም ብሎ የሚያያቸው የለም፡፡ አማራንና የኦርቶዶክስ እምነትን ለማጥፋት አጀንዳ ተቀርፆ እንቅስቃሴ ተጀምሮም አልተሳካም፡፡ ወደፊትም አይታሰብም፣ አይሳካምም፡፡ ፓርቲን ለማዳከም አመራሮች የተገደሉ ቢሆንም፣ የሚፈጠር ክፍተት የለም፡፡ በአማራ ላይ ብዙ ተንኮልና ሴራ ተፈጽሟል፡፡ ነጋዴው ሠርቶ እንዳያተርፍ፣ ከአገር እንዲሰደድና እንዲታሰር ተደርጓል፡፡ አንዱ ማረጋገጫ እኔ ራሴ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገደሉ በሰዓታት ልዩነት፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና በጡረታ ላይ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤታቸው ተገድለዋል፡፡ ግድያው የተቀነባበረና ተያያዥነት ያለው እንደሆነም ይነገራል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ አምሳል፡- በእርግጥ በግድያው ያልተቆራኘ ነገር የለም፡፡ የአማራ ክልል ተወላጆችና ነጋዴዎች ስም ዝርዝር ሁሉ በየድረ ገጹና በፌስቡክ እየተለጠፈ ነው፡፡ ይኼ የተደረገው ሆን ተብሎ ይመስለኛል፡፡ ኃይል ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው የፖለቲካ ኃይል ሲሆን ሌላው የኢኮኖሚ ኃይል ነው፡፡ የፖለቲካውን ኃይል ለማዳከም ከፍተኛ ራዕይ ያላቸውን አመራሮች አንዱ ኃይል ገድሏል፡፡ ሌላ መግደል የሚፈልጉት ደግሞ የኢኮኖሚን ኃይል ነው፡፡ ኢኮኖሚውንም ለመግደል ገና በምርመራ ላይ ያለን ጉዳይ፣ ማን እጁ እንዳለበት ተጣርቶ እንዳላለቀ እየታወቀ በማኅበራዊ ሚዲያ የክልሉን ባለሀብቶች ስም ዝርዝር እየለጠፉ ማሸማቀቅ፣ ሞራል መስበርንና ተስፋ ማስቆረጥ ተሰደው እንዲሄዱ ነው? አማራ መሰደጃ የለውም፡፡ አገሩና መሰደጃው ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ እውነተኛ ማስረጃ ያለው ካለ ለምን ለመርማሪው አያስረክብም? ይኼ የሴራ እንቅስቃሴ በእነማን እንደሚቀነባበር ግምት ቢኖርም የትም አይደርስም፡፡ ከንቱ ድካም ነው፡፡ መንግሥት ምርመራውን ጨርሶ ነገ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል፡፡ በዚያን ጊዜ መጠየቅ ያለበት በሕግ ይጠየቃል፡፡ ለምንድነው የኢኮኖሚውን ኃይል ለማሸማቀቅ ሕወገጥ ተግባር የሚፈጸመው? እኔ ‹‹አሉበት ወይም የሉበትም›› እያልኩ አይደለም፡፡ መንግሥት የያዘውን የማጣራት ሥራ መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ይኼ ሆን ተብሎና ቀደም ብለው በነበሩ ዓመታት የክልሉን ኢኮኖሚ ለማዳከም ነጋዴዎች ሲታሰሩ ሲፈቱ ስለነበር፣ የቀድሞ ርዝራዥ አመራሮች ዛሬም ያንን ድርጊታቸውን ለመድገም የሚሠሩት ሴራ መሆኑን መታወቅና መጋለጥ አለበት፡፡ የክልሉ ተወላጅ ነጋዴዎች እንደ ከብት ሁለትና ሦስት ጊዜ ሲታሰሩና ሲፈቱ መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሲሠራ የነበረው በአማራው ላይ ነው ቢባል ይገልጸዋል፡፡ መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት፣ ፋብሪካ፣ ኢንዱስትሪ እንደሠራ ቢገለጽም፣ ‹‹ታዲያ አገር እየመራ ምን ሊሠራ ነበር?›› የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ ይኼንን ሥራማ ጣሊያንም ሠርቶታል፡፡ ነገር ግን አንድን ዘር ለይቶ ለማጥፋት አጀንዳ ይዞ መንቀሳቀስ ግን እጅግ አስነዋሪና መወገዝ ያለበት ድርጊት ነው፡፡

የባህር ዳሩና የአዲስ አበባው ከፍተኛ አመራሮችን ግድያ ቅንብር በሚመለከት ድርጊቱን ለመፈጸም ተንቀሳቅሷል የተባለውን ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነውን ከመናቅ በስተቀር ምንም የምለው ነገር የለኝም፡፡ ንቀቴ እነዚያን የመሳሰሉ ከፍተኛ አመራሮችን በመግደሉ ነው፡፡ ስለቅንብሩ ግን በጥልቀት የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ ብቻውን አቀነባብሮ ድርጊቱን ፈጽሟል ለማለት ይከብደኛል፡፡ ሌላ አካል ያለ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ምርመራውና ታሪክ እውነቱን ያወጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያም ሆነ ይህ የአገሪቱን ትልቁንና ቁንጮ የሆኑትን የጦር መሪ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ ለአገራቸው ብዙ የሠሩትን ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራን፣ ወጣትና ብዙ ራዕይ ያላቸውን አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ አቶ እዘዝ ዋሴንና አቶ ምግባሩ ከበደን አጥተናል፡፡ አሟሟታቸው ከባድ ነው፡፡ ምርመራውም በጣም ከባድና ጊዜ የሚፈልግ ነው፡፡ በቀላሉ የሚሳካም አይደለም፡፡ ጥበብና ልዩ ቴክኒክ ይፈልጋል፡፡ አሳምነው ብቻ ያቀነባረው ነው ለማለት ይከብደኛል፡፡ ከበስተጀርባ የረቀቀ፣ በተንኮልና በወንጀል የተካኑ ኃይሎች አማካይነት ከሩቅ በሪሞት ኮንትሮል የተሠራ ይመስለኛል፡፡ ሙያው ስለሌለኝ መተንተን ቢከብደኝም እገምታለሁ፡፡ ገዳይ አንድ ያልገባው ነገር አማራን ማውደም ኢትዮጵያን ማውደም መሆኑን አለማወቁ ነው፡፡ ወይም አብሮ መውደም መሆኑን አለመረዳት ይመስለኛል፡፡ ግድያ ብቻ ሳይሆን አንዱን ብሔር ከሌላኛው ብሔር ጋር የማባላት ይሁዳዊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅና መጠንቀቅ አለበት፡፡ ይኼንን ከሥር መሠረቱ መንጥሮ እውነቱን ማውጣት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ግዴታ ነው፡፡ ግድያውን ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ብቻውን መርቶታል ማለት ከባድ ነው፡፡ ይኼ ድርጊት በደንብ ጥናት የተደረገበት እንጂ፣ በስሜት ብቻ ተነሳስቶ የተፈጸመ ድርጊት አይደለም፡፡ ‹‹አሳምነው ነው›› ብሎ መዝጋት ለእኔ አይታየኝም፡፡ ገና መቼ ምርመራው አለቀ? ገና መጀመሩ ነው፡፡ ምርመራው እንደ ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር) ተድበስብሶ መቅረት የለበትም፡፡ አገር እንደ አገር እንድትቀጥል ሰንኮፉ መውጣት አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን የወንጀል ድርጊት ተከታትለው እውነቱን እንዲወጣ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይኼንን ድርጊት ለመፈጸም ለብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው የልብ ልብ የሰጠው አካል አለ የሚል ግምት አለኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልነገሩን ብዙ ሙከራዎች እንደነበሩ ሰሞኑን ፓርላማ ተገኝተው ነግረውናል፡፡ ቀጣዩም የከፋ ስለሚሆንና አገርም እንደ አገር እንድትቀጥል ምርመራው በደንብ ተካሂዶ ሰንኮፉ ተነቅሎ መውጣት አለበት፡፡ ቅን ልቦና ለመሪ አያስፈልግም፡፡ ከሕግ በላይም ወይም ከሕግ በታችም ሳይሆን፣ ሕግን በአግባቡ መፈጸምና ማስፈጸም ያስፈልጋል፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡

LEAVE A REPLY