ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም

ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም

ዛሬ በርካታ የአማራ ወጣቶች ከፍ/ቤት በጅምላ በፖሊስ ታፍሰው ታሰሩ
 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አ.ብ.ን) አባላትና ደጋፊ ናቸው የተባሉ በርካታ ወጣቶች በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡

ከሰኔ አስራ አምስቱ የአማራ ክልላዊ መንግስት ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ የሽብርተኝነት ተግባር ፈጽመዋል በሚል በሕግ ጉዳያቸው የተያዙ ተጠርጣሪዎች፣ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ሰዓት ተቃውሟቸውን የሚገልጽ “እውነትና አማራነት አይታሰርም” የሚል መፈክር የተጻፈበት፣ ተመሳሳይ ቲሸርት ለብሰው በመታየታቸው ወጣቶቹ በፖሊስ ተከበው ለዕስር ሲዳረጉ የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ለመታዘብ ችሏል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግስት ገና በጨቅላነት ዕድሜው በአደባባይ ቃል የገባውና “ከእንግዲህ በኋላ እንዲህ በሚል ክስ ማንም ኢትዮጵያዊ አይታሰርም” በማለት ቃል የገባለት የ”ሽብርተኝነት” አዋጅ፤ ከተራ ዲስኩርና ፕሮፐጋንዳ ባልዘለለ መልኩ ዛሬም በተግባር ላይ መዋሉ ብዙዎችን እያስቆጣ ይገኛል፡፡
በዚህ አላስፈላጊ ሕግ ምክንያት ግልጽ የሆኑ የበቀልተኝነት ስሜት በመንግስት በኩል እየተወሰደ እንደሚገኝና በአጋጣሚውም የባላደራው ም/ቤት አባላትና ጥቂት የማይባሉ የአማራው መብት ተሟጋቾች የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ብሶቶች እየተስተጋቡ፣ “አጣርቼ አስራለሁ” ያለው መንግስትም ሳያጣራ በጅምላ ማፈሱን በመቃወም ነበር ወጣቶቹ ዛሬ በፍርድ ቤት ዙሪያ ሐሳባቸውን የሚገልጸውን ቲሸርት በብዛት በመልበስ አደባባይ የወጡት፡፡
ከፍርድ ቤት ታፍሰው የተሰሩት ወጣቶች መነሻና መሰባሰቢያቸውን አራት ኪሎ ግንፍሌ ድልድይ አካባቢ ከሚገኘው የአ.ብ.ን ዋና ጽ/ቤት ነበር ያደረጉት፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተደርጎ በነበረው የኢትዮጵያ ቡናና መቀሌ ሰባ እንደርታ ጨዋታ ላይ ለበርካታ ንጹሕ ኢትዮጵያዊያን ሞትና አካል ጉዳት ዋነኛ ተጠያቂ የሆነው ግለሰብን የሚያሞግሱ፤ “እኔም ጌታቸው አሰፋ ነኝ” የሚሉ ቲሸርቶችን የለበሱ የትግራይ ወጣቶች ከተማዋን ባጥለቀለቁዋት ወቅት ዝም ያለው ፖሊስ፤ ዛሬ ፍትህ መዛባቱን በጨዋነት መንገድ የገለጹ የአማራ ወጣቶችን በጅምላ ማፈሱ ስርዓቱ ግልጽ በሆነ የፖለቲካ ችግር የተበተበ መሆኑን ያሳያል ይላሉ አስተያየት ሰጭዎች፡፡
የ10.7 ቢሊዮን ብር የአ/አ ስድስት ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ኩባንያዎች መሰጠቱ ተቃውሞ ገጥሞታል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ገፅታ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ የተባሉ 10.7 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግባቸውን ፕሮጀክቶች ከአምስት የውጭ ኩባንያዎች ጋር በመፈራረም አስረክቧል፡፡
እነዚህን ስድስት ፕሮጀክቶች ለውጭ ኩባንያዎቹ በተሰጡበት ሐምሌ 11 ቀን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቅቀው ዕውን ሲሆኑ፣ በከተማዋ ላይ መልካም ገጽታ እንደሚፈጥሩ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ ጊዮርጊስ ማዘጋጃ ቤት ፊት ለፊት የሚገኘውና በሚድሮክ ኢትዮጵያ ተይዞ ለዓመታት ያለ ግንባታ ታጥሮ ቆይቶ በቅርቡ ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን በተደረገው 30,300 ካሬ ሜትር ላይ የሚገነባው ዓድዋ ፓርክ ቀዳሚው ፕሮጀክት ነው ተብሏል፡፡
ወደ የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚደረግ ጉዞ የሚጀምርበት ይህ ቦታ “ሁሉም ከዚህ ይጀምራል” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ፕሮጀክት የቻይናው ጂያንግሱ ሊትድ በ4.6 ቢሊዮን ብር ገንብቶ ለማጠናቀቅ ውል ፈፅሟል፡፡
አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ የሚገነባው ቤተ መጻሕፍት ሁለተኛው ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በ19 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚገነባ ሲሆን፣ 30 ሺህ ሰዎችን በአንድ ጊዜ የሚይዝ ግዙፍ ቤተ መጻሕፍት እንደሆነም ተነግሮለታል፡፡
የጣልያኑ ጂኦም ሉጂ ቫርኔር ገንቢው ሲሆን ይህ ኩባንያ በሸራተን ማስፋፊያ ላይ የታቀደው የወንዝ ዳር ልማትን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲገነባ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ በቻይና ኩባንያ እንዲሰራ በመፈለጉ ምክንያት ቫርኔር ሥራውን ተነጥቋል፡፡
ከቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ተነስቶ በ22 ማዞርያ፣ እንግሊዝ አሜምባሲ ድረስ የሚገነባው መንገድ በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠ የአዲስ አበባ ከተማ ፕሮጀክት ነው፡፡ 3 . 133 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው መንገድ 330 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል፡፡
የአዲስ አበባ ቀለበት መንገድን በመገንባት የሚታወቀው የቻይናው ሲአርቢሲ ኩባንያ (አሁን ስሙ አይ.ኤፍ.ኤች ኢንጅነሪነግ ኩባንያ ተብሏል) ያከናውነዋል ተብሏል፡፡
ከፑሽኪን አደባባይ እስከ ጎተራ ማሳለጫ ድረስ የሚገነባው ሌላኛው ፕሮጀክት፤ ዲዛይኑ ከተሰራ ሶስት ዓመት ያለፈው ሲሆን ቦታው በከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅም የሚታወቅ ነው፡፡ 2.3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ ከ30 እስከ 45 ሜትር ድረስ የጎንዮሽ ስፋት ይኖረዋል፡፡ ይህንን ስራ የቻይናው ሲሲሲ ኩባንያ ያካሂደዋል፡፡
ከአራት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ በሚወስደው መንገድ ከሒልተን ሆቴል ከፍ ብሎ በሚገኘው አስር ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍና አንድ ሺህ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ መያዝ የሚችል ዘመናዊ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ህንጻን የዓድዋ ሙዚየምን የሚገነባው የቻይናው ጂያንግሱ ሊሚትድ ተረክቦታል፡፡ ይህ የፓርኪንግ ግንባታ ቤተ መንግሥቱ ለሕዝብ ክፍት ሲሆን በጎብኚዎች ሊፈጠር የሚችለውን የፓርኪንግ ችግር ለማቃለል የታሰበ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
ከተገነባ አርባ ስድስት ዓመት የሞላውና ከዚያን ጊዜ አንስቶ በቂ ዕድሳት ያልተደረገለት ማዘጋጃ ቤትን ማደስ ሌላኛው ፕሮጀክት መሆኑ ተነግሯል፡፡ “ኤሊክ ፊት አወት” የተሰኘው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኩባንያ ይህንን ግንባታ ለማከናወን ውል ፈፅሟል፡፡ አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ባገለለ መልኩ ስድስት ግዙፍና የ10.7 ቢልዮን ብር ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ለአምስት የውጭ ኩባንያዎች እንዲሰጥ መደረጉ ከወዲሁ ብዙዋችን እያነጋገረ ነው፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያውን ኩባንያዎችና ባለ ሙያዎች መንግስት አገር በቀል ድርጅቶችን ባላበረታታ መልኩ የወሰደውን ዕርምጃ በእጅጉ እየኮነኑ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡
ከብድርና ቁጠባ ተቋማት መሀል አምስቱ ወደ ባንክ ሊያድጉ ነው
በሃገሪቱ ከሚገኙና በተለያዩ ክልሎች ውስጥ መሰረታቸውን ከጣሉ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት መሀል አምስቱ ወደ ባንክ ሊሸጋገሩ መሆናቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው አዲስ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደደቢትና ኦሞ የተሰኙት ብድርና ቁጠባ ተቋማት ናቸው ወደ ባንክ የሚሸጋገሩት፡፡ አንጋፋዎቹ የብድርና የቁጠባ ተቋማት የፋይናንስ አቅማቸው ከብዙ አዳዲስ ባንኮች ጭምር የተሻለ እየሆነ ቢመጣም በትላልቅና የተሻለ ትርፍ ሊያመጡ በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ማፍሰስ ሳይችሉ ለመቆየት ተገደዋል፡፡ በመሆኑም ድርጅቶቹን ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያሸጋግር የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወደ መደበኛ የባንክ ሥራ እንዲገቡ ለመፍቀድ ዝግጅት ላይ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ ይፋ አድርጓል፡፡
ሂደቱን ዕውን ለማድረግ ሕጋዊ ማዕቀፍና ድንጋጌዎች እየተዘጋጀ ቢሆንም የአነስተኛ ብድር ተቋማቱ ወደ ባንክ ሲሸጋገሩ በእነሱ ቦታ የአገልግሎት ክፍተት ይፈጠር ይሆን ወይ? የሚለው ዋነኛ ስጋት ሆኗል፡፡ እነዚህ ተቋማት ወደ ባንክ ሲያድጉ የክልል መንግስታት በተቋማቱ ውስጥ ያላቸው ድርሻ በባንኮች ውስጥ የማይቀጥል ከመሆኑ ባሻገር፤ መንግስት ለተቋማቱ የሚያደርጋቸው የቢሮ፣ የብድርና ሌሎች ድጋፎች ሙሉ ለሙሉ ይቀራሉ፡፡ በባንክ ሕግ መሰረት ማንኛውም ሰው ከ5 በመቶ በላይ የአክሲዮን ባለቤት ሊሆን አይችልም፡፡
ወደ ባንክ ከፍ የሚሉት አነስተኛ የብድር እና ቁጠባ ተቋማቱ 5 ሚሊዮን የብድር ደንበኞች አሏቸው፡፡ የቁጠባ ደንበኞቻቸው ግን ከተበዳሪዎቻቸው ጋር የማይመጣጠኑ ሆነው ታይተዋል፡፡ ተቋማቱ ያበደሩት ጠቅላላ ገንዘብ 32 በመቶ እያደጉ 51.7 ቢሊዮን ብር ሲደርስ ካፒታላቸው ግን 15.5 ቢልዮን ብር ብቻ ሆኖ ተቀማጭ 38.4 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ጠቅላላ ሀብታቸው ደግሞ 76.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡
በሙሉ ወንጌል ውስጥ የተፈጠረው ችግር እንዲፈታ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሳሰቡ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተከስቶ የነበረው አለመግባባት በአፋጣኝ ዕልባት እንዲያገኝ ውሳኔ አስተላልፈዋል ተባለ፡፡
ከሰሞኑ በጽሕፈት ቤታቸው ቅሬታ አቅራቢዎችን ጠርተው ያነጋገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተከሰተው ነገር በእጅጉ አሳፋሪና አንገት አስደፊ መሆኑን ገልፀው፤ ጉዳዩ በፍጥነት መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ደምዎዝ ሳይከፈላቸው የቆዩ አካላትም እስከ እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲከፈላቸው፤ በዕግድ የቆዩ ሰዎችም ወደ ቤተክርስቲያኗ እንዲመለሱ ከረር ያለ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ ታህሳስ ከ12 – 13 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፤ ቤተ ክርስቲያኗ ከሐምሌ 2006 ዓ.ም ጀምሮ ትጠቀምበት የነበረውን ደንብ ማሻሻሉ ይታወሳል፡፡
የተሻሻለ የደንብ ክፍተት አለ በሚሉ ሰዎችና በሕግ አውጪዎቹ መሀል በጉዳዮ የተፈጠረው አለመግባባት ወደለየለት ፀብ አምርቶ በርካታ ሰዎች ለድብደባ የተጋለጡበትና ወደ ክስ የተሄደበት አጋጣሚ መፈጠሩም አይዘነጋም፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎች በሰላም ሚኒስቴር በኩል መፍትሔ ለማግኘት በተደጋጋሚ ባቀረቡት ደብዳቤ አማካይነት ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ሳሉ ነው ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ጣልቃ በመግባት ውሳኔ ያስተላለፉት፡፡ በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ቀጠና ኹለት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰባት ሰዎች ደምዎዝ ተቋርጦባቸው፤ ምዕመናን ከኪሳቸው በማዋጣት ደምዎዛቸውን ሲከፍሉ መቆየታቸውን ታማኝ ምንጮቹን በመጥቀስ አዲስ ማለዳ ዘግቧል፡፡
ዶ/ር ምህረት ደበበ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን መከሩ
በልዩ ልዩ አነቃቂና የሞራል ግንባታ ሰጪ ንግሮቻቸው የሚታወቁት ዶ/ር ምህረት ደበበ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ነገሮችን አስፍቶ ለማሰብ የሚረዳ ሥልጠና ሰጡ፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት አዘጋጅነት ከሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በፓርቲዎች ውህደትና ጥምረት ላይ ያተኮረ የውይይትና ሥልጠና ፕሮግራም መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ በፕሮግራሙ ተጋባዥ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ምህረት ደበበ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ “የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ጥቅምና ጉዳት” የሚል ይዘት ያለው የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር ምህረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ለማድረግ ሲያስቡ በቅድሚያ የትኞቹ መሠረታዊ ነጥቦች ላይ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸውና ውህደት ለማድረግ ከሁሉም በፊት ጥርጣሬን ማስወገድ ወሳኙ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
“በተናጠል ማንንምና የትኛውንም ጉዳይ ማሸነፍ አይቻልም” ያሉት ዶ/ር ምህረት ደበበ፤ “ውህደት መፍጠርና በጋራ መንቀሳቀስ በቀላሉ ለድል ያበቃል” ሲሉ መክረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በማያያዝም “ፓርቲዎች በቅድሚያ አገርን የሚመጥን የጋራ ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸው፤ “ኢትዮጵያ ጥቂት ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንጂ ብዙ ደካማ የፖለቲካ ድርጅቶች አያስፈልጓትም” ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 131 ደርሷል፡፡

LEAVE A REPLY