ቤልጅግ አሊ (የብዕር ስሙ ነው) አንድ እሁድ አመሻሹ ላይ ከጀርመን መልክት አደረሰኝ። « ተጓዥ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ስዊድን ስለሚመጣ እንድታገኘው…» የሚል ቆየት ብሎም ደውሎ ተነጋገርን። ለሄኖክም ስልኬን እንደሰጠው ገለጸልኝ።
ቤልጅግ አሊን በማህበራዊ ድረ ገጾች ሲጽፍ አውቀው ነበር።በኋላ ግን ኔዘርላንድ በተደረገው የአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የኳስ ውድድር ላይ በተመልካችነት ተገናኘን። ኳስ ጨዋታው የተደረገው ዘ–ሄግ በተባለው ከተማ ነበር ዘ–ሄግን የምሰማው በዜና ነበር።በዓይኔ ላየው የቻልኩት በዛ አጋጣሚ ሆነ። ዘ–ጌግ ሞቅ ያለች አነስተኛ ከተማ ናት።ሁሉን ነገር በይፋምታስተናግድ የሌላት የለም። የሌላት ቢኖር ምሳ ነው።ቁርስና እራት እንጂ ምሳ በየቤቱ ካልሆነ ሆቴል የሚዘጋጅ አይመስለኝም። በስፖርቱ ምክንያት ሜዳው ዙርያ ድንኳን ይዘው የአበሻ ምግብ የሚያዘጋጁት ባይኖሩ በረሃብ ባለቅን ነበር።
ከስዊድን ኳስ ተጨዋቾቹን አጅበን ከሄድነው መሃል የጋዜጠኛ አህመድ አሊ ስርዓት፤ ማስያዝ የመስከረም ሽንቋጭ ምክር፤ የሰለሞን አጭሬ ጨዋታ ባይኖር አክራሞቱ መልኩን ይለውጥ ነበር። ሰለሞንን ሳነሳ ሌላም ነገር መግለጽ ሊኖርብኝ ነው። ከስለሞን ጋር ሜዳው ላይ ሆነ መዝናኛ ቦታዎች አልተለያየንም። ስለሞን ከባቢው ብዙ ነው። ይጋብዛል ይጋበዛል። ከሚጋበዘው ግን እሱ የሚጋብዘው ይበልጣል። እየተጋበዘ እንጂ እየጋበዝ የሚጫወት ከሰለሞን ውጪ ብዙም አላውቅ። ሰለሞን የመብል መጠጡ ወጪ ጉዳዩ አይደልም። ዋናው ስው አግኝቶ መጫወቱ ነው። በዚህ ማሀል ግን ሰለሞን የታከተው አስሬ እየተነሳ ለሰው መጠጥማመላለሱ ነበር።አጭሬ ለሱም ዘዴ አበጀ። አንድ ባለብስክሌት ልጅ ባጋጣሚ እጁ ገባ። በሰዓት ይክፈለው በወር ይነጋገረው አይታወቅም ልጁ ከሰለሞን ጎን ቆሞ ያዘዘዘው ያመላልሳል።አንዳንዴም በምልክትም ይነግረዋል መሰለኝ የሚያስፈልገንን ይዞ ከተፍ ይላል። ቦታ ቀይረንም ስንሄድ ሜዳው ላይ ስንዘዋወርም ልጁ አለ።አልፎ አልፎ ጨዋታ ያመጣል ግን ብሶቱ ጨዋታውን ወዲያውያደናቅፍበታል። ቀኑን ሙሉ ከኛ አልተለየም። እየጠጣም እያስተናገደንም። የመጨረሻ መጨረሻ ሰሌ ልጁን አጠጣኝ እስከማለት ደርሶ ነበር።
ከቤልጅግ ጋር ሜዳው ላይ በተገናኘን ግዜ እውቁ የፖለቲካ ሰው አቶ አበራ የማነብርሃን አብሮት ነበር ተዋወቅን። ብዙ ተጨዋወትን “አበራ የማነአብን አገኘሁት…» የሚል መጣጥፍ ጀምሬ እጄ ላይ አለ። አንድ ቀን የሆነ አጋጣሚ አክየበት ለንባብ አበቃዋለሁ የሚል ሀሳብ አለኝ። ደራሲና ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔን፤ የአእምሮ ሚዲያ አዘጋጅ የሆነው ክብረት መኮንንን፤ አቶ መስፍን አማንን አግኝቻቸው በየግል አውርተናል። ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ እና ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ ቦታው ላይ እንደነበሩ ብሰማም ላገኛቸው ባለመቻሌ ቅር እንዳለኝ ነው የተመለስኩት። የተክሌ የኋላ “ ከፍ ያለውን ማለም …” የምትለዋን ድንቅ መጽሐፍ እዛው አግኝቼ በማስታወሻነት ይዣታለሁ።
ቤልጅግ አሊ የዛን ጊዜ ትውውቃችንን በመመርኮዝ ነበር ሄኖክን እንዳገኘው የፈለገው ። ሄኖክን ተጓዥ ጋዜጠኛ ሆኖ በሚጽፋቸው ጽሁፎች አውቀዋለሁ። በቅርቡም ‘’ጎንደርን ፍለጋ’’ የሚል መጽሐፉን አስነብቦናል። በአካል ደግሞ የማገኝበት ሁኔታ በመገጣጠሙ ደስ አለኝ። ሄኖክ እንግዳ ነውና ምን ማድረግ እንደሚገባኝ እቅድ አወጣሁ። በስቶኮልም ውስጥ ያላያቸውን ቦታዎችላስጎበኘው ሊተዋወቃቃቸው ከሚገባ ስዎች ጋር ላስተዋውቀው፣ ቤት ያፈራውን ግብዣ ላደርግለት አሰብኩ። የጣፈጠም ጨዋታ እንደማገኝ ገምቻለሁ። ይህን ሳደርግ እረፍት ቀኔን አመቻችቼ ወይንም ትርፍ ቀን ስራዬን ትቼ እንደሚሆን ወስኛለሁ።
ሄኖክ ማክሰኞ ቀን እንደሚገባ አውቄያለሁ። እንደገባ ጻፈልኝ በስልክም አገኘሁት። አርብ መገናኘት እንደምንችል ተነጋገርን። አርብ ለሄኖክ የተያዘች ቀን ሆነች። እነሆ! አርብ ደረሰ ሄኖክ ስልክ አያነሳም። ብጽፍለትም አይመልስም። ከአሁን አሁን ይደውላል በማለት ስልኬን ስመለከት ቆይቼ የማታ ማታ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ቅዳሜ አመሻሹ ላይ ደወለ። ቅዳሜና እሁድ እንደማይመቸኝ ነግሬው ለማክሰኞ ተቀጣጠርን። የትም ቢሄድ ተመልሶ እንድሚመጣና እንደምንገናኝ ነገረኝ። ማክሰኞ ቁርጠኛ ቀን ሆነች።
ማክሰኞ በጠዋት ተነስቼ ለሄኖክ ቀጠሮ ተዘጋጀሁ። በጠዋትከአዲስ አበባ እንደሱው የመጣ ሰው ይዤ መሀል ከተማው ላይ ሰፈርኩ። ሄኖክ እንገናኝ ስለው እማይጠፋው ቦታ ላይ ነኝ። ሲደውል ምሳ ልንበላ። ከንግዳው ጋር ሻይ ቡና ስንል ቆይተን ምሳ ሰዓት ደረሰ። ሄኖክ አይደውልም። ብደውልም አይመልስም። ምሳ ሰዓቱን ገፋ አደረኩት ሄኖክ ዘሩም የለ። ምሳችንን ከንግዳው ጋር በልተን ቀልቤ እንደተንጠለጠለ አመሸሁ። ሰዓቱ የምሽቱን ቦታ ቢይዝም ቀኑ አልጨለመም። ሄኖክ ግን የለም። አብሮኝ ያለውን እንግዳ ቤት በማሳየት ሰበብ ሄኖክ ሊገኝ የሚችልባቸውን ቦታዎች ሁሉ አዳረስኩ። ምናልባት ስዎች አግኝተውት ወይም የሚቆይባቸው ቀናት በቁጥር በመሆናቸው እኔን ለማግኘት ሳይመቸው ቢቀርስ ብዬ ነበር ፍለጋ የጀመርኩት። ሄኖክ የለም። ከአሁን በኋላ በተለየ አጋጣሚ ካልሆነ በቀር እኔም ጊዜ ስለሌለኝ ልንገናኝ እንደማንችል ገባኝ። ሄኖክ ቀጠሮውን በላ!
እውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ በአሉ ግርማ “ ቀጠሮ እማያከብር ሰው ከእድሜህ ላይ ትንሽ ትንሽ የሚሰርቅ ሊባ ነው እንዳለው ሄኖክ የማላገኘውን ውድ ቀኖቼን ሳይሆን እድሜንም እንደሰረቀኝ በአሉ አስታውሶኛል። ቶማስ ጉናርሸር የባለው ሲዊድናዊ ደራሲ ደግሞ ብሶቴን ሲያባብስ “ለአንድ ሰው ከምትሰጠው ትልቁ ስጦታ ሁሉ! ትልቁ ጊዜህን መስጠት ነው“ ብሏል። እውነት ነው። ሄኖክ ሊቀበለኝ ባይችልም ትልቁን ስጦታ ሰጥቼዋለሁ። ትመዝገብልኝ!
የዚህን አይነት ቀጠሮ አለማክበር ጉዳት በቤልጅግ አሊም ላይእንዳደረሰበት ራሱ ነግሮኛል። ቤልጅግ ይሄን መግለጹ ያስፈለገው እንዳልቀየምበት ማባበሉ ጭምር መሆኑ ነው። የቤልጅግ በእውቀቱን ፍለጋ ከኔ ይብዛም ይነስአላውቅም። የማውቀው ቢኖር ሁለታችንም በሁለት የስዩምልጆች ከእድሜአችን ላይ መሰረቃችንን ነው። አበጁ! እንኳን ሰረቁን፤ ማን ተንከርፈፉ አለን?።
እንደእውነቱ ከሆነ ጊዜ ለሰራበት ገንዘብ ነው፤ ጊዜ ካነበቡበት እውቀት ነው፤ጊዜ በሰላም እረፍት ካረጉበት ጤና ነው፤ ጊዜ ከቤተሰብ ጋር ካሳለፉት ፍሬ አለው። በተለይ የውጪ ሀገር ነዋሪ የጊዜን ጥቅም አጣርቶ ያውቃል። እነ ሄኖክ ቢሆኑ ይሄን የሚያጡት አይመስለኝም። ሃሳባቸው ለሚያገኙት ሰው ሳይሆን የመጡበትን ጉዳይ መሸፈን ነውና ብዙ ላይፈርድባቸው ይችላል። ሆኖም ማንንም ቢሆን ሊያገኙት እንደማይችሉ እያወቁ መቅጠር አይገባቸውም። ይኸን ማሻሻል እንደሚገባ መምከር ባይገባኝም ማሳሰቢያቢጤ ብሰጥም ግን የሚያስነቅፈኝ አይመስለኝም። ሄኖኬ አንተም ሆንክ ሌሎቻችሁ እባካችሁ ሰው ቀጥራችሁ አትጥፉ። እድልና አጋጣሚ እረድቷችሁ ተፈላጊ አደረጋችሁእንጂ፤ አረ! የሰው ያለህ! የሚሉ ብዙ የአገር ልጆች እንዳሉ አትዘንጉ።
ሄኖክ ጎንደርን ፍለጋን ስትጽፍ ብዙ እንደደከምከው ሁሉ እኔን አንተን ፍለጋ ብዙ ባክኛልሁ። እዚህ ባንገናኝም ስለስዊድን ምትጽፈውን ማንበቤ አይቀርም ። ላንተ ያዘጋጀሁት “የእኔ ሽበት “የተባለ አዲስ መጽሐፌ ስምህ እንደተጻፈበት እቤት ተመልሷል።በሱ ምትክ ይቺ ሄኖክን ፍለጋ ያልኳት አጭር ጽሁፌ ማስታወሻ ትሁንህ።
ማጠቃለያ ውሳኔ
“የእኔ ሽበት” የተባለው በስሙ ስጦታ እንዲሆነው የፈረምኩበት መጽሐፍ ለተጓዥ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በተገኝህበት ቦታ እንዲሰጠው እኔና ቤተሰቤ ወስነናል።