በአዲስ አበባ ጉዳይ ለመምከር፣ ፓርላማው ለነገ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም የአራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሂዳል፡፡
ምክር ቤቱ በነገ ስብሰባው የአዲስ አበባ እና የድሬድዋ ከተሞች ምክር ቤቶች ተወካዮችን፤ በተጨማሪም የአካባቢ ምርጫን በተመለከተ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የባንክ ሥራ አዋጅና እና የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ምርምሮ ረቂቅ አዋጆቹን ያፀድቃል፡፡
የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በተጨማሪም የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን እና ካሳ የሚከፈልበትን ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅንም በተመሳሳይ ሁኔታ መርምሮ፣ በዚህ አስቸኳይ ስብሰባው ላይ ሊያፀድቀው እንደሚችል የሚወጡ መረጃዎች ከወዲሁ ያመላክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳይሸጥ አቶ ግርማ ዋቄ አሳሰቡ
የኢትዮጵያ መንግስት ሊሸጣቸው ካሰባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች መሐል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለግል ባለሀብቶች ከተሸጠ ውጤቱ ጥሩ ሊሆን እንደማይችል አቶ ግርማ ዋቄ ገለፁ፡፡
በሁለት የተለያዩ ዙሮች አየር መንገዱን በማስተዳደር፣ አሁን ያለበት የገዘፈ ደረጃ እንዲደርስ ያስቻሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድና ፍላይ ኢምሬትስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ዋቄ፤ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ምክንያት ካልሆነ በቀር፣ አየር መንገዱ ከበቂ በላይ አትራፊ ሆኖ የሚሰራ ግዙፍ ተቋም ስለሆነ ለመሸጥ ማሰቡ በእጅጉ እየተሳሳተ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ ከመንግስት ገንዘብ ሳይጠይቅ በሚገባ ስራውን እያከናወነ ባለበት በዚህ ሰዓት ለምንድን ነው ለመሸጥ የሚቸኮለው? በማለት የሚጠይቁት አንጋፋውና ስመጥሩ የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያ “መሸጥ ከታሰበ መንግስት ከአየር መንገዱ የሚያገኛቸው ጥቅሞች ይቀራሉ? ወይስ ይቀጥላሉ? የሚለው ሁሉ መታየት አለበት፣ ባንቸኩልም መልካም ነው፡፡ ከማለታቸውም በላይ አየር መንገዱ ከዚህ በላይ ብዙ ነገር ማድረግ የሚችል ነውና ሽያጩን መተው ነው የሚሻለው” ሲሉም በቢሊዮን ዶላር ለመሸጥ ለተዘጋጀው የአብይ አህመድ መንግስት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትርፋማነቱ ባሻገር ሃገራዊ ሀብትና ኩራት መሆኑም መዘንጋት እንደሌለበት ያስታወሱት ግርማ ዋቄ፤ ሊሸጥ የታሰበው ተቋም በ 2025 ዓ.ም ሊተገብረው ያወጣውን እቅድ ከአራት አመት በፊት አስቀድሞ እንደሚጨርስም ያላቸውን ዕምነት በርግጠኝነት አስቀምጠዋል፡፡
የተተከሉት ከ300 ሚሊየን በላይ ችግኞች በትክክል ተቆጥረዋል ተባለ
በ”አረንጓዴ አሻራ” ዘመቻ በትናንትናው ዕለት በአንድ ጀምበር ተተከሉ የተባሉት ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በትክክል መተከላቸው ተነግሯል፡፡ የተተከሉት ችግኞችም በአግባቡና በትክክል ለመቆጠራቸውን ጉዳዩን የያዘው መንግስታዊ ተቋም ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡
የችግኝ ተከላ ሂደቱን ሲከታተል የነበረው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሲሆን፣ በሥሩም ቁጥጥሩን በአግባቡ የሚከታተል አንድ ቡድብ ተቋቁሟል፡፡ ችግኞቹ በትክክል መተከላቸውን ለመቆጣጠር ቀድሞ የተሰራ ሶፍትዌር እንደነበርም ተሰምቷል፡፡
ሶፍትዌሩ በዛፍ መትከያ ቦታዎች ላይ የተከላውን ሂደት ለመቆጣጠር የተመደቡ ሰዎች ስልክ ላይ ብቻ የሚሰራ ሲሆን፣ በአካል በመገኘት የቆጠሩትን ችግኝ ብዛት የሚያስተላልፉበት ሥርዓትም ነበረው፡፡
በዚህ አሰራር መሰረት በተመደቡበት ቦታ ላይ ምን ያህል ችግኞች እንደተተከሉ ቁጥሩን ሲያስገቡ፤ ሶፍትዌሩ በተለያዩ ቦታዎች የሚደርሱትን አሃዞች በማጠቃለል እየደመረ ውጤቱን ይሰጣል፡፡ በመጨረሻም ሶፍትዌሩ በአጠቃላይ በመላ ሃገሪቱ የተተከሉት ችግኞች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል፡፡ ማረጋገጫም ይሰጣል፡፡
ይህንና ሌሎች የመቆጣጠሪያ መንገዶችን በመጠቀም በትናንትናው ዕለት ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት፣ ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው መረጋገጡን ሶፍትዌሩን ሲቆጣጠር የነበረው ቡድን አስተባባሪ አቶ ኢምራን አቡበክር ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም በተለያዩ አለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን የተዘገቡ ቁጥሮች ብዙዎችን ያወዛገቡ ሲሆን የመገናኛ ተቋማቱ በምንጭነት የሚጠቅሱት የመንግስት ባለስልጣናት ምንም አይነት መረጃ ሳይኖራቸው የሚጠቅሱት ቁጥርን በሚመለከት ምንም አይነት ምላሽ አልተሰጠም።
በወለጋና በጉጂ በተከሰቱ ማፈናቀሎች 3ሺ ሕፃናት ከቤተሰብ መለየታቸው ታወቀ
በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በጉጂ ዞን በተነሳው ግጭትና ማፈናቀል ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩ ከሶስት ሺህ በላይ ተፈናቃይ ቤተሰብ አልባ ሕፃናት እንዳሉ ተነገረ፡፡
እንደ ብሔራዊ አደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መግለጫ ከሆነ፤ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት በሃገሪቱ የተከሰተውን የለውጥ ሂደት ተከትሎ በሚነሱ ፖለቲካዊ ሁከቶችና ግጭቶች በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡
በዚህ መሰረት ከቤኒሻንጉል ክልል ተፈናቅለው የመጡ በምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ የሚገኙ 1130 ሕፃናት በግርግሩ ከቤተሰቦቻቸው ሲለያዩ፣ ጥቂት የማይባሉ ሕፃናት በርሃብና በግጭት ሳቢያ ወላጆቻቸውን በሞት አጥተዋል፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ አስከፊ ችግር የተጋረጡት 1000 ወንዶች እና 130 ሴት ሕፃናት ናቸው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በጉጂ ዞን ከሚገኙ ተፈናቃዮች፣ 1.919 የሚሆኑት ሕፃናት በዚህ ወቅት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሙሉ በሙሉ ተለያይተው ነው ያሉት፡፡ ከእነዚህ ሕፃናት መሐል 1027 ሴቶችና 892 ወንዶች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሕፃናቱ በስደት ወቅት በነበረው ግርግር ሳቢያ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ናቸው፡፡ የብሔራዊ አደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩትን ሕፃናት አፈላልጎ ከወላጆቻቸው ጋር ለማገናኘት ያደረገው ጥረት ተሳክቶ፤ 197 ሴት፣ 219 ወንድ በድምሩ 416 ሕፃናት ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ችለዋል፡፡ የአንዳንዶቹ ሕፃናት ቤተሰቦች ሕይወታቸው በማለፉ፣ ኮሚሽኑ የልጆቹን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለማመቻቸት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል፡፡
ከቤኒሻንጉል ጉምዝ “ቦሌጅንደይ” እና “ያሶ” ወረዳ ተፈናቅለው፣ በቡሬ እና ሀር ሊሙ ተጠልለው ከሚገኙ ዜጎች ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ ከወላጆቻቸው የተለያዩ በርካታ ሕፃናት መኖራቸውም ተሰምቷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንም ዓይነት፣ የደረጃ ዕድገት እንዳይሰጥ ታገደ
በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ቦርድ ክስ ተመስርቶበት የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ክርክሩ እስኪያልቅ ድረስ ማንኛውንም ዓይነት የሥራ ደረጃ ዕድገት እንዳይሰጥ እግድ ተጥሎበታል፡፡
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ ማህበር የመጣውን ክስ ሲከታተል የቆየው፤ በሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የተዋቀረው አስተዳራዊ ችሎት ነው የዕግድ ትዕዛዙን ያስተላለፈው፡፡ ሐምሌ 18 ቀን 2011 ዓ.ም በተሰጠው የእግድ ትዕዛዝ ባንኩ የደረጃ እድገት ማስታወቂያዎችን እንዳያወጣ እና ማንኛውንም የሥራ ዕድገት አሰራር እንዳይተገብር ያሳስባል፡፡
ቁጥራቸው ከ28 ሺህ በላይ የሚሆን የባንኩ ሰራተኞች በማህበራቸው አማካይነት በመሰረቱት የውል ክስ፤ ባንኩ በኅብረት ስምምነቱ ላይ በተጠቀሱ ስድስት መስፈርቶች ብቻ ዕድገት ይሰጥ ሲሉ ነበር ክሳቸውን ያቀረቡት፡፡ የሰራተኞችን አቅም የምለካበት አዲስ አሰራር በጥናት አግኝቻለሁ የሚለውን ንግድ ባንክ በበኩሉ፤ የህብረት ስምምነቱ ላይ ባሉ መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ አልስማም በሚል የደረጃ ዕድገት አሰጣጡ ተገቢ መሆኑን በመግለጽ ሲከራከር ቆይቷል፡፡
በወለጋ ለስድስት ወራት የተዘጉት ፍርድ ቤቶች ሥራ ጀመሩ
በአካባቢው የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ ዞን ለወራት ሥራ አቁመው የነበሩ ፍርድ ቤቶች፣ አገልግሎት ወደ መስጠት መመለሳቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይፋ አድርጓል፡፡
ታጣቂው የ”ኦነግ ሸኔ” ጦር በአካባቢው ከፈጠረው ሁከትና መከላከያ ሠራዊቱ ሰላምን ለማስፈን ከወሰደው ዕርምጃ ጋር ተያይዞ፤ ግልፅ የሆነ አለመረጋጋት በመታየቱ የዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ፣ የወረዳ እንዲሁም የዞን ፍርድ ቤቶች ለስድስት ወራት ያህል ዝግ ሆነው መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡
በአሁኑ ሰዓት አብዛኞቹ የሕግ ተቋማት የተከፈቱ ሲሆን፣ በዞኑ ውስጥ ካሉ በርካታ ወረዳዎች መሐል ስድስቱ ግን አሁንም የፍትሕ ተቋሞችን ለመክፈት አልቻሉም፡፡
የተነሳውን ሁከትና ግጭት ተከትሎ በተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ብዙ ጥቃቶች ሲፈፀሙ፤ በዳኞቹ ላይ ግን እስካሁን ምንም ጉዳት አለመድረሱን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ጎንፋ አቶማ አስታውቀዋል፡፡
ለግማሽ ዓመት ፍርድ ቤቶቹ ተዘግተው መቆየታቸው ፍትህን በሚፈልግ በርካታ ሕብረተሰብ ዘንድ ቅሬታን አስነስቶ የነበረ ቢሆንም፣ ችግሩ የፍርድ ሂደቱን ለማከናወን ከባድ ከመሆኑ አኳያ መ/ቤቶቹን መዝጋት ግድ ሆኖ ቆይቷል፡፡
73 ዓመት ያለፋቸው ሰነዶች ወደ ብሔራዊ መዛግብትና መጻሕፍት ኤጀንሲ ተዛወሩ
ከ73 ዓመት በላይ ዕድሜን ያስቆጠሩ ሰነዶች ወደ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ማዘዋወሩን የፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
ኤጀንሲው ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ በእጁ የሚገኙትንና የማይጠቀምባቸውን የተመዘገቡ ሰነዶች ነው ወደ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ያዘዋወረው፡፡
በ418 አቃፊ ፋይሎች የተዘጋጁት ሰነዶች፣ ለብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት መዘዋወራቸው ተረጋግጧል፡፡ የኤጀንሲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ታምሩ፤ ሰነዶቹ ለተለያዩ ጥናቶች ጠቃሚ በመሆናቸው ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታና በተደራጀ መልኩ ተቀምጠው አገልግሎት እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡