በደምቢ ዶሎ በአደባባይ የተገደለው ወጣት ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል! ኢሰመጉ ድርጊቱ እንዳሳሰበው ገለፀ!

    ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በምዕራብ ኦሮሚያ ቄለም ወለጋ ዞን በደምቢ ዶሎ ከተማ፣ አማኑኤል ወንድሙ የተባለ ወጣት በአደባባይ በመንግሥት ኃይል መገደሉና የአካባቢ የመንግሥት ባለስልጣናት የወጣቱን መገደል ማረጋገጣቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ጉዳዩ ብዙሃንን በሰፊው እያነጋገረና እየተወገዘ መሆኑንም ለመገንዘብ ተችሏል።

    “ወጣቱ ለሕዝብ እንዲታይ ተደረገ እንጂ በአደባባይ አልተገደለም” ሲሉ ድርጊቱን ያስተባበሉ አንድ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣን “ወጣት አማኑዔል ‘የአባ ቶርቤ’ ቡድን አባል በመሆኑ ‘እርምጃ ተወስዶበታል’ በማለት ሲናገሩ፣ የደምቢ ዶሎ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤትም “ሰዎችን ሲገድል በነበረው እና የ ‘አባ ቶርቤ’ ቡድን አባል በሆነው ግለሰብ ላይ እርምጃ ተወሰደ” ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፏል።

    “ወጣቱ ትናንት በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት ንጋት ላይ ገመቹ መንገሻ የተባለ ግለሰብ በጥይት መትቶ ለማምለጥ ሲሞክር ‘በጸጥታ ኃይሎች ጠንካራ ትስስር እግሩን ተመትቶ ተይዟል” ሲልም ጽ/ቤቱ ገልጿል።

    ይሁንና፣ ወጣቱ “ለፍርድ ሳይቀርብ ለምን እርምጃ ተወሰደበት?” የሚሉ ዜጎች ጉዳዩን ከህግ የበላይነት ጋር አያይዘው በሰፊው እየተነጋገሩበት ሲሆን፣ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎችም ወጣቱ በአደባባይ ሲገደል ማየታቸውን እየተናገሩ መሆናቸውም የጉዳዩ አሳሳቢነት ከፍ እንዳደረገው ለመታዘብ ተችሏል።

    በተያያዘ ዘ፣ በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ “በወንጀል ተጠርጥሯል የተባለው አማኑኤል ወንድሙ ከፍርድ ውጪ የተፈፀመበት ግድያና (extrajudicial killing) በአደባባይ ለህዝብ እንዲታይ የተደረገበት መንገድ አሳስቦኛል” ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን/ኢሰመኮ አስታውቋል።

    ማንኛውንም ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የሚካሄዱ ግድያዎችን በማውገዝ “ከፍርድ ውጪ የሚካሄዱ ግድያዎች ህዝቦች በሕግ የበላይነት ላይ ዕምነት እንዲያጡ እና በዚህ ረገድ የተገኙ ስኬቶች እንዲቀለበሱ ያደርጋሉ” ያለው ኮሚሽኑ፣ ሁሉም የሕግ አስፈፃሚ አካላት ሕጋዊ መንገዶች ብቻ አንዲተገብሩም መልዕክቱን አስተላለፏል፡፡

    LEAVE A REPLY