የሰፈረባት ዛር በጋለባት ጊዜ ወቅት እየመረጠ ወራት እየለዬ
አውሬ የሚያደርጋት የጥፋት ልክፍቷ በድንገት ሲመጣ
ከዶሮወች መሀል ወሰራውን ወይም ገብስማውን መርጣ
አንገቱን ጠምዝዛ ወይ ጭርሱን ቆርጣ
በዬመታጠፊያው በየመሻገሪያው ስትጥል እያዬ
ለብዙ ዘመናት አብሯት ስለኖረ አብሯት ስለቆዬ
ከለታት አንድ ቀን
ከመውጫና መግቢያው ከበሩ ላይ ቁማ
መንፈስን በሚያውክ
ነፍስን በሚያስጨንቅ ልብን በሚያደማ
ሰቅጣጭ በሆነ ድምፅ ስለታማ ዜማ …
” በወሰራ ዶሮ እየተመኸኜ
በገብስማ ዶሮ እየተመኸኜ
የኔስ በሽታዬ ሰው ሆኖ ተገኜ ” ማለቷን ሲሰማ
ማቄን ጨርቄን ሳይል ድንገት ተሰወረ በድቅድቅ ጨለማ
በቅኔዋ መሀል ጠቆም ያረገችው
“የኔስ በሽታዬ ሰው ሆኖ ተገኜ”
በሚል ልዝብ ስንኝ የደመደመችው
አብሯት ኖሯልና ~ ባለፈው ህይወቱ እንደተላመደው
ካስደጋጭ ዜማዋ ቀጣይ እርምጃዋ በፍርሀት ቢያርደው
አገር ጥሎ ጠፋ እንደዶሮወቹ እንዳታሳርደው ።