ወለፈንዴ ዘመን || በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

ወለፈንዴ ዘመን || በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

ዘወትር
ሁልቀን፤
አውጫጭኝ
ሰቀቀን፡፡
.
ጀምበር ገባች፣
ገባሁ፣
በሬን እዘጋለሁ፤
እንደበጋ ጥላ
ሲቀድመኝ
ስቀድመው፣
ሲገፋኝ
ስገፋው፣
ከዋልኩት እራሴ፣
ሙግት እገጥማለሁ፡፡
እጋፈጠዋለሁ፡፡
.
ጸሀይ ገባች
በቃ፤
ይከፈት ሙዚቃ፡፡
በዜማ አውጫጭኝ
በስንኝ መሮ፤
ነፍሴ ተበርብሮ፤
ብይን አልባ ሙግት፡፡
.
ሙዚቃ ተከፍቶ፣
የነፍስን መቀነት፣
መጎተት
መጎተት
መጎተት፡፡

ሙዚቃው
ስንኙ፤ . .
ሲውጡት እድሜ ነው፣
ሲያኝኩት የማይጥም፤
የልጃገረድ ምጥ፣
ጥርስ የሚያስቆረጥም፡፡

ገነት የፈተለው፤
ሲኦል የሸመነው፤
ለገድል አይመች፣
ምጥ ሲሉት – ድሪያ ነው::

ግራው – ቀኝ
ላዩ – ታች
ለሊቱ፤
ወለፈንዴ
ውበቱ፡፡

ሙዚቃው
ይሞቃል፤
ሙዚቃው
ይበርዳል፤
ሙዚቃው
ያጠብቃል፤
ሙዚቃው
ያላላል፤
እንደ ቅቤ ስፍር፣
ቆልሎ
ቆልሎ
እንደተልባ ስፍር
አንሸራቶ ያጎድላል፡፡
ዘፈኑ ደስ ይላል፡፡
ዘፈኑ ያስጠላል፡፡
. . . . .

LEAVE A REPLY