አንችን ማጣት ማለት …
በስሜት የሆነ ደስታን እንደመናድ
በአዕምሮ የሆነ ጥበብ እንደመካድ
በመንፈስ የሆነ ፍቅርን እንደማቅለል
ከመውደድ የመጣ ሸክም እንደመቆለል
ነው እኔ ምቆጠረው – ብየ ብነግርሽም
ከቶ በጄ አላልሽም
ወይም አላመንሽም
ወይም አልፈለግሽም
ወይም አልገባሽም !
…
መብትሽ ነው ፡፡
መለየት ብርቅ ነው ?
.
ለእኔም ግን መብት አለኝ
ማንም የማይሰጠኝ
ማንም የማይነጥቀኝ
ባታስጠልይኝም በሕይወትሽ አክናፍ
ባታስደርሽኝም ከመኖሪያሽ በራፍ
ለመዳን በማሰብ ካንች ፍቅር ቅጣት
ሌላ ዘዴ ዘይድሁ – “አንችን ላለማጣት”
.
ያኔ እንደነገርሽኝ
እህቴ ናት ያልሺኝ ?
ነው ወይስ ጓደኛሽ ?
ብቻ ምስጢረኛሽ…
አንቺ እርሷን መለየት? – ከቶ አይደረግም
እሷም አንቺን ማጣት? – ፈጽሞ አትፈልግም
ስለዚህ ተመቸኝ …
ከዛሬ ጀምሮ እቀበላታለሁ !
እርሷ አፍቅራኛለች – አረጋግጫለሁ፡፡
.
ያልነገርሁሽ ምሥጢር…
ያኔ አንችን ፍለጋ ደጅሽ ስመላለስ – ሲበዛ መንገዴ
ሰላም እላት ነበር – እርሷን በማናገር ልቀርብሽ በዘዴ
እርሷም በደስታ ታናግረኝ ነበር – ስላልገባት ጉዴ !
.
ከዕለታት አንድ ቀን…
‹‹ለምን ትፈራለህ ? ችግርህ ገብቶኛል
በቃል ባታወጣው ዓይንህ ይነግረኛል
ፍቅሬ ብትሆን እኮ… ለእኔም ደስ ይለኛል››
ብላ ስትነግረኝ ሴቷ ቃል አውጥታ
አልደፈርኩም ነበር – “አልሆንሽም” ብዬ መውደዷን ልገታ
.
ምክንያቱም …
ዓመታት ሲነጉዱ – እየተመላለስኩ አንችኑ ፍለጋ
ተመልሼ አላውቅም ሳልደርስ ከእሷ ጋ
መጽናኛ እንዲሆነኝ – ሀሳብ እየፈጠርሁ ጥበብ ስናወጋ
ጥበብ አፍቃሪ ናት – በጥበብ ወሬ ነው ልቧ የተወጋ፡፡
በውል ላስተዋለው – የፍቅሯ መጠኑ – ሊርቁት ይከብዳል ፤
በጊዜ ቢለካ…
አንችን ካፈቀርሁሽ – ከእኔው ጋር እኩል ነው – ቢቀር ያሳብዳል፡፡
.
ስለዚህ ወሰንኩኝ…
እኔ አንችን አጥቼ – አብጄ ከምዞር
እርሷም እኔን አጥታ – ተጎድታ ከምትኖር
እናንተ ሁለቱ – ተለያይቶ መኖር ስለማትችሉ
የፍቅራችን መፍትሄ ይሄውልሽ ውሉ፡-
.
እርሷን ላግባትና አንቺ ሚዜ ሁኛት
ቤቷ ቤትሽ ይሁን እየመጣሽ ጎብኛት
አየሽ መፍትሄ ማለት…?
.
በፍቅሬ እንዳልጎዳት እርሷን አገባለሁ
ፍቅርሽ እንዳይጎዳኝ ስትመጭ አይሻለሁ
.
ያው ነግሬሻለሁ…
አንችን ምፈልገው ልተኛሽ አይደለም
በመተኛት ብቻ… ሊገለጥ የሚችል የሰው ፍቅር የለም
.
ለሩካቤ መኖር – እንስሳዊ ግብር – ከውስጣችን ይውጣ
በመንፈስ እንሁን – በአዕምሮ እንዋደድ – ይሄው ነው የእኛ ዕጣ፡፡
—–//—-
አንችን ላለማጣት ወዳጅሽን ላግባት! (ከትንሣኤ ማግስት ከሚታተመው መድበሌ ተካቷል) /መላኩ አላምረው/