ኦፈን ያ ጃገማ!! /በታሪኩ አባዳማ/

ኦፈን ያ ጃገማ!! /በታሪኩ አባዳማ/

ኦፈን ያ ጃገማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ጣሊያን ግራ ገባው መብረቅ አይጨበጥ
ሲያስገመግም እንጂ አይታይ ሲያደፍጥ
ከቶ ምን ፍጥረት ነው እንዲህ የሚያራውጥ!!
ደንዲ አፋፉ ላይ ታይቷል ሲባል ጀግናው
ግንደበረት ወርዶ ጣልያንን አጨደው።
በቡሳ አቋርጦ… በሺ ላይ አድፍጦ
ዱከኖፍቱ አድሮ ጨሊያ ላይ ማልዶ…
ቦዳ አቦን ተሳልሞ ጊንጪ ላይ ብቅ አለ
በጠራራ ፀሐይ መብረቁን ነደለ።
‘ካፒቴኖ ጃገማ… ካፒቴኖ’ ጣሊያን ቢማፀነው
አገሬን ሳትለቅ ሰላም የለም አለው።
ተመለስ ጃገማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ባንዳ ተልከስክሶ ለጠላት ሊሸጣት
አገሬን ሲያስማማት
ክብሬን ሊያዋርዳት
‘ኢንተኡ፣ ዲዴ’ ብሎ ጃገማ ካለበት
በቁጣ ገንፍሎ መብረቁን ጣለበት።
ጠላትሽ ኢትዮጵያ ማደሪያ የለውም
የጃገማ መብረቅ ምቾት አይሰጠውም።
የጠላት ጦር ሰፈር በጭንቅ ተሽመድምዶ
በጠራራ ፀሐይ መብረቅ መጣል ለምዶ
ጃገማ ጃገማ ጃጋማ ተወልዶ!!!
ኦፈን ያ ጃገማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
/ሚያዝያ 1 2009/

LEAVE A REPLY