በ 2017 ኢትዮጵያ ስሟ ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰረዝ ዋናውን ስራ የሰራው ኢትዮጵያዊ...

በ 2017 ኢትዮጵያ ስሟ ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰረዝ ዋናውን ስራ የሰራው ኢትዮጵያዊ በኩራት ምክንያቱን ይነግረናል /ሉሉ ከበደ/

የኢዮጵያ ገዳዮቿ ልጆቿ እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? ስንት ሺህ ዘመን ስንት ሺህ ወራሪዎችን አሳፍራ ፤ስንት መቶ ጦርነቶችን አካሂዳ ያልተንበረከከች፤ ተገንብታ እዚህ የደረሰች ምድር፤ ከአብራኳ በወጡ የበሰበሱ ልጆቿ ክፋት ለመውደቅ በቃች።ዛሬ ኢትጵያ ወድቃለች። መንግስት የላትም። ሉአላዊነቷ ተደፍሯል። ህዝቧ ጠባቂ አቶ ለጥቃት ተጋልጧል። ተሰቃይቷል።ተለያይቷል። ይህን ሁሉ አደጋ ያመጡባት ባእዳን አይደሉም። ልጆቿ ናቸው።

አንዲት እኔ ዘወትር በኢትዮጵያ የምመስላቸውን እናት እውነተኛ ታሪ እነሆ። እኒህ እናት ስምንት ልጆች ወልደዋል ። ሰባቱ ልጆቻቸው የተባረኩ ፤ የተመሰገኑ ፤በግብረገብነትና በፈሪሃ እግዜብሄር የታነጹ በመሆናቸው በሰፈር ፤ በትምህርትቤት በሁሉም አቅጣጫ ተወዳጅና ተቀባይ ነበሩ። መጨረሻ ላይ የተወለደው ስምንተኛው ልጃቸው ግን ከቤተሰቡ ለየት ያለ ባህሪ ይዞ ብቅ አለ። ከህጻንነቱ ጀምሮ ውሸታም ፤ ነውጠኛ፤ አታላይ ፤ሌባ ፤ተደባዳቢ ሆነ። ለትምህርትም አስቸጋሪ ሆነ። ቅጣት የማይበግረው ሞገደኛ ሆኖ አረፈው። ስምንትና ዘጠኝ አመት ሆኖት የመንደሩ ህጻናት ጨውና ስኳር እንዲገዙ ሱቅ ሲላኩ መንገድ ላይ እየጠበቀ ፍራንክ ቀምቷቸው ይሮጣል።ሰው ሁሉ የሚረግመውና የሚያዝንበት ልጅ ሆነ።ከቤቱም ከጎረቤቱም ያገኘውን ሁሉ የሚሰርቅ ሆነ። አድጎ ወደህብረተሰቡ ሲቀላቀልም ስራው ሁሉ ከህግ ጋር የሚያላትመው ሆነ። እናቱ ታዲያ በዚህ ልጅ በጣም ያዝናሉ። ያለቅሳሉ። ስንት ልጆች እንዳላቸው ለጠየቃቸው ሰው ሁሉ “ስምንት ወልጄ አንድ አገማሁ” ይላሉ።ገማብኝ የሚሉት ይህን የተበላሸውን ልጅ ነው። ዶሮ እንቁላል ታቅፋ ጫጩት ያልሆነው እንደሚገማባት ማለት ነው። ኢትዮጵያም ታዲያ ወልዳ ወልዳ ያገማቻቸው ልጆቿ የሚያጠፏት ሆኑ።

ሰሞኑን ኢትዮጵያ ካገማቻቸው ልጆቿ መካከል አንዱ ከጀርመኖች ጋር ተስማምቶ ስሟ ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰረዝ አድርጓል። ይህ ሰው በቅርቡ የዶክትርና ትምህርቱን የጨረሰ የጀርመን ኢቫንጀሊካን ቤተክርስቲያን ፓስተር ነው። ዶክተር በንቲ ኦጁሉ ይባላል። በ2017 የታተመው የጀርመን ኢቫንጀሊካን ቤትክርስቲያን መጽሃፍ ቅዱስ ታርሞ ባዲስ ተተረጎመ ሲባል የኢትዮጵያ ስም እንዲወጣ ዋናውን ስራ የሰራው ይህ ሰው ነው።ስለ ድርጊቱም በኩራት ይናገራል።”ኦፕራይድ ” ለሚባል ድረገጽ ጋዜጠኛ መርጋ ዮናስ በእንግሊዝኛ ጉዳዩን አስመልክቶ ከሰውየው ጋር ሰፋ ያለ ቃለምልልስ አድርጓል። ቃለ ምልልሱን ውዱ ወዳጄ እና የሙያ ወንድሜ ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ ከአመስተርዳም አድርሶኛል። እኔም አንብቤ ዝም ማለቱ አይጠቅምም አልኩና ይህን ቃለ ምልልስ ለሁላችንም በቀላሉ እንዲገባን ብየ ከእንግሊዝኛ ወደአማርኝ በመመለስ ላካፍላችሁ ወደድኩ።ሁሉም እንዲያቀው ሼር ብታደርጉት ደስ ይለኛል። ወደ ቃለ ምልልሱ እንግባ።

መርጋ :፤የዶክትርና ትምህርትዎን በማጠናቀቅዎ እንኳን ደስ ያለዎት ልልዎ እወዳለሁ። የመመረቂያ ጥናታዊ ጽሁፍዎ እንደሰማሁት “የኦሮሞ ሃገር – በቀል( ነባር ) ሃይማኖትና የኦሮሞ ክርስትና ፤ የሚቃረኑ ወይስ የሚስማሙ ፤( አብረው መጓዝ የሚችሉ) ” በሚል ርእስ ላይ ያተኮረ ነው።ይህን ርእስ ለመምረጥ ምን አመላከቶት? የሚቃረኑባቸው ነገሮች ምንድናቸው የሚስማሙባቸውስ?አንድ የሚያደርጋቸው።

መልስ፤ከዚህ ፕሮጀችት ጀርባ ያለው ምክንያት ብዙ ክርስቲያን ሚሽነሪዎች፤ ኢቫንጀሊካኖች እና ፓስተሮች የኦሮሞ ህዝብ ስለ እግዜብሄር ሃሳቡ ፤ እውቀቱ የለውም እና ሃይማኖታቸውም በጣኦት ማምለክ ወይም በሴጣን ማመን ነው ብለው ይገምቱ ነበር። በአካባቢ አህጉራችን የክርስትናና እስልምና ሃይማኖት ከመምጣት በፊት የነበረውን የኦሮሞ ሃገር በቀል ሃይማኖት መመርመር መመልከት ጀመርኩ። ስለዚህ ከስነመለኮት እይታ አኳያ የመመረቂያ ጽሁፌ የማነጻጸር ሃይማኖታዊ ጥናት ነው። እመለከት የነበረውም ነገር የኦሮሞ ነባር ሃይማኖት ከክርስትና ጋር ይጻረራል ወይስ ይስማማል የሚለውን ነው። በጥናቴ ወቅት በኦሮሞ ነባር ሃይማኖት (ዋቄፈታ) እና በክርስትና መካከል ብዙ ተመሣይነትና ጥቂት ልዩነቶችን አግኝቻለሁ። ደስ የሚል ግኝት ነው።የእስልምናም የክርስትናም ሚሽነሪዎች የኦሮሞ ነባር ሀይማኖት ከነሱ እምነት የተለየ ነው ብለው ይገምቱ ነበር።የሆነሆኖ በብዙ መንገድ ምንም ልዩነት የሌለው ሆኖ አግኝቸዋለሁ። እግዜብሄር ከሚለው መጠሪያ ጀምሮ ይታያል። እግዚአቤር በኦሮምኛ “ዋቃ” ወይም “ዋቀዮ” ይባላል። ምድርና ሰማይን የፈጠረ። ከእስልምናም ሆነ ከክርስትና መምጣት በፊት ኦሮሞ ለረጂም ጊዜ የሚያምንበት ነው። መጽሃፍቅዱስን ወደ ኦሮሞኛ የተረጎሙ የተጠቀሙበትም ይኸው ቃል ነው።” God” የሚለውን “ዋቃ” በሚለው በመተካት።እና ዋቃ የሚለው ስም በመሰረቱ ከክርስትና ሳይሆን ከኦሮሞ ነባር ሃይማኖት የተወሰደ ነው።እንዲህ ወደ ዝርዝሩ ከገባህ ጥቂት ልዩነት ብዙ ተመሳሳይነትን ታገኛለህ። ጥናቱን ለማካሄድና ለመጻፍ ብዙ ጊዜ ወስዷል። የሆነው ሆኖ አሁን የመመረቂያ ጽሁፉን ጨርሻለሁ።ዲሴምበር 2016 ሒልደሺም ዩኒቨርሲቲ ቀርቧል። ጥናቱን አስመልክቶ የቀረቡ ፈታኝ ጥያቄዎችን ክርክሮችን ጁን 2017 በተሳካ ሁኔታ አስተናግጃለሁ።

ጥያቄ፤ እርሶ እያገለገሉ ያሉበት ቤትክርስቲያን ኢቫንጀሊካል ደችላንድ አዲስ መጽሃፍ ቅዱስ አሳትሟል።ቀደም ሲል በነበረው ቅጂ ውስጥ ስህተት እናም ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው ያላቸውን ትርጓሜዎችና ቃላትን አርሟል። “ኢትዮጵያ ” የሚለውን ቃል “ኩሽ” በሚለው መቀየርን ያጠቃልላል። ከዚህ የስም ለውጥ በስተጀርባ እንደምክንያትነት የሚቀርበው ምንድነው ?

ዶክተር በንቲ፤ መልካም ። የመጽሃፍ ቅዱስ ትርጉም ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እየተካሄደ ያለ ነገር ነው። ከየትርጉም ስራው ጀርባ ያለው ሃሳብ በቀድሞዎቹ ህትመቶች ውስጥ የተወሰኑ ጉድለቶችና ግድፈቶች ይኖራሉ የሚል ነው።የተለያዩ የመጽሃፍቅዱስ ማህበረሰቦች መጽሃፍ ቅዱስን ሲተረጉሙ ኖረዋል። ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ማርቲን ሉተር መጽሃፍ ቅዱስን ከ ላቲን ወደ ጀርመንኛ ከተረጎመበት ጊዜ ጀምሮ የቋንቋና የሃሳብ ትርጉም እየተካሄደ እንዳለ ነው።በነዚያ ትርጉሞች ውስጥ ስህተቶችነበሩ።አንዳንዶቹ የቋንቋ ሊሎቹም ግንዛቤያዊ ነበሩ። አሁን እየተካሄደ ያለው ትርጉም ምክንያቱ እነዚያ ያለፉ ስህተቶች ናቸው ። እነሱን ማረም ነው።

ለምሳሌ ግሪኮች ብሉይ ኪዳንን ከሂብሩ ቋንቋ ወደ ግሪክ ሲተረጉሙ “ኩሽ” የሚለውን ወደ “ኢትዮጲስ” በመቀየር ስህተት ሰሩ።ኩሽ የጥቁር አፍሪካ ህዝብ ስም ነበር ወደ ኢትዮጲስ የተለወጠ ። ትርጉሙ “ፊቱ የተቃጠለ ህዝብ” ማለት ነው። ኩሽ በመሆንና የተቃጠለ ፊት በመሆን መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ጥቁር ህዝቦች ፊታቸው የተቃጠለ አይደለም።ጥቁሮች ናቸው በቃ። ይህ አዲሱ በጀርመን ኢቫንጀሊካን ሉትራን ቸርች በ2017 የታተመው መጽሃፍ ቅዱስ እነዚያን ስህተቶች በማረም ነው ማለት ነው።

በአሮጌው የመጽሃፍ ቅዱስ ቅጾች ውስጥ “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል 45 ጊዜ ተጠቅሷል። እነዚህ ቃላት እንደ ስህተት ተወስደው ኩሽ ወደሚለው ወደቀድሞ ተክክለኛ ቃሉ ተለውጠዋል። ግልጽ ለመሆን የ2017 ትርጉም ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ብቻ አይደለም የቀየረው። ብዙ ቃላትና ያገባብ ስህተቶችን አርሞ ተርጉሟል።በተለይ “ኢትዮጵያ” የሚለው ወደ “ኩሽ” መቀየሩን የሚያስደስት ሆኖ አግኝቸዋለሁ።ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ በመጽሃፍ ቅዱስ በመጠቀሷ የምንኮራ ነበርን። እውነታው ግን የግሪክ ተርጓሚዎች በስህተት የህዝብ ስም ነው ብለው አስበው ነበር።አሁን ያ አለመሆኑን አውቅን። ለኩሽ ህዝብ የተሰጠ ክብር የሚነካ የሚያዋርድ መጠሪያ ነበር(Derogatory)። በጀርመን ኢቫንጀሊካል ሉትራን ቸርች ይህ ተለይቶ መታወቁን በማየቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ጥያቄ፤ ቤተክርስቲያንዋ ሌሎች ለውጦችንም ማድረጓን ጠቅሰዋል። ምንድናቸው?

መልስ፤ በአዲሱ እትም ወደ መዝሙረዳዊት 68 : 31 የሄድክ እንደሆነ “ኩሽ እጆቿን ወደ እግዜብሄር ትዘረጋለች” ይላል። በቀድሞው ትርጉም ውስጥ ግን ” ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዜብሄር ትዘረጋለች ” ነው የሚለው። ከኢትዮጵያ ወደ ኩሽ ከተለወጡት 44 አረፍተ ነገሮች አንዱ ነው። ተርጓሚዎቹ አንድ ወይም ሁለት “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል ያልተለወጠበት ሀረግ ረስተዋል።የሆነሆኖ ይህንንም ከነሱ ጋር ተወያይተናል። በቅርቡ ይታረማል።ለምሳሌ በኤርሜያስ 13:23 ውስጥ ያለው አንዱ ሳይተረጉሙ የረሱት ነው። በእንግሊዝኛው ትርጉም ” ኢትጵያዊ ቆዳውን ነብር ዥጉርጉርነቱን ይቀይራልን?” ይላል። እዚህ ላይ “ኢትዮጵያ ” የሚለው ቃል ፈጽሞ ሊጠቀሙበት የማይገባ ስድብ ነው(Insult).። የትርጉም ለውጡ ስለ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። ብዙ የስም ለውጦችን ያጠቃልላል። አሁን ልነግራቸው የማልችል ቦታዎችን ጽንሰሃሳቦችን ሁሉ።

ጥያቄ ፤ በስነ መለኮትም ሆነ በሌላ ማናቸውም ከፍተኛ ትምህርታዊ ምሁራዊ ስራዎች ላይ ይህን መሰል ለውጦች ሲደረጉ ማጠቃለያ ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት ጥናቶች መካሄድ አለባቸው።የጀርመን ኢቫንጀሊካል ቤተክርስቲያን ቃላቶችንም ሆነ አገባባቸውን ከመቀየሯ በፊት በቂ ጥናት አካሂዳለች?

መልስ፤ እርግጥ። የጀርመን ኢቫንጀሊካን ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ያስተዳደር አካል ፤ የትርጉም ስራውን እንዲያካሂድ አንድ የምሁራን ቡድን መደበ።የቋንቋ ጠበብትንና የመጽሀፍ ቅዱስ ሊቃውንትን ያቀፈው ግብረሃይል በ2010 ተቋቋመ።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ትርጉሙን ሲሰሩ ቆይተው የመጨረሻ ውጤታቸውን ለቤተክርስቲያን መሪዎች አቀረቡ።የቤተክርስቲያን መሪዎችና ጉባኤተኞች አዲሱን ትርጉም አነበቡ።አስተያየታቸውንና እንዲህ ቢሆን የሚል ሃሳባቸውን ሰጡ። እንግዲህ ለሰባት አመታት ቁጥራቸው የበዛ ኤክስፐርቶችና ምሁራን በዚህ ስራ ላይ ተሳትፈዋል።ይህ አዲስ ቅጂ የታተመው የሉተርን ተሃድሶ 500 ኛ አመት ለማሰብ ነው።ከ ኦክቶበር 31 – 2016 እስከ ኦክቶበር 31-2017 የሚውለውን ክብረበአል ለመዘከር። በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት ሰዎች የበቁ የስነመለኮት ሰዎች፤ፈላስፎች፤የስነቋንቋ ጠበብት፤በሂብሩ፤ በግሪክ፤ በእንግሊዝኛ በጀርመንና በሌሎችም ቋንቋዎች የበቁና ከፍተኛ እውቀት ያካበቱ ናቸው።

ጥያቄ፤እስቲ ስለ ጥናቱ ሂደት ጥቂት ያብራሩልኛል? እና አጥኚዎቹ ምሁራን ግኝታቸውን ለማን እንዳቀረቡ?

መልስ፤አጥኒዎቹ ትርጉሙን የሰሩት አሮጌውን መጽሃፍ ቅዱስ መሰረት በማድረግ ነው።አዲሱ የትርጉም ስራ ይሁንታ ከማግኘቱ በፊት የሚያልፍባቸው በርካታ ደረጃዎች አሉ።መጀመሪያ ግለሰብ ኤክስፐርቶች የትርጉም ስራውን ያካሂዱና የሌሎች ኤክስፐርቶች እና የቤተክርስቲያን መሪዎችን ቡድን ላቀፈው ግብረሃይል አዲሱን ትርጉምና አሮጌውን መጽሃፍ ቅዱስ ያቀርባሉ። ይህ ግብረሃይል የራሱን አስተያየትና የእርምት ሃሳብ ከሰጠ በኋላ አዲሱም ጥንታዊውም መጽሃፍ ቅዱስ ለጳጳሱ ና በመላ ጀርመን የሚገኙ የኢቫንጀሊካን ቤተክርስቲያን ተወካዮች ለተሰየሙበት ጉባኤ ይቀርባል። ጉባኤውና ጳጳሱ አዲሱን መጽሀፍ ቅዱስ የሚያጸድቁ ፤የሚያሳትሙና የሚያሰራጩ ከፍተኛ አካላት ናቸው።

ጥያቄ፤ይህ ትርጉም ይህ ለውጥ በኢቫንጀሊካን ቤተክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ ምን አይነት ምልከታ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?

መልስ፤ በጀርመን ያሉ የፕሮቴስታንት ቤተክርስትያናት በአዲሱ ትርጉም ደስተኞች ናቸው።የተወሰኑ ስህተቶች ታርመዋል።ትክክለኛ ቋንቋ በመጠቀም ልዩነትን የሚፈጥሩ ቃላትን በመቀየር ቤተክርስቲያኗ መጽሀፍ ቅዱስን የተሻለ ለማድረግ ትሞክራለች።የፕሮተስታንት ቤተክርስቲያን ተከታዮች በጣም ደስተኞች ናቸው ።አሁን መጽሀፉን በየጉባኤው ላይ እንጠቀምበታለን።

ይህ አዲስ መጽሀፍ ቅዱስ የፕሮተስታንት ቤተክርስቲያን መጽሃፍ ቅዱስ ነው።የካቶሊክ ወይም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አይደለም።ኦርቶዶክስና ካቶሊክ ቤተክርስቲያኖች የየራሳቸው መጽሃፍ ቅዱስ አላቸው። ፕሮተስታንቶች 66 መጽሃፍት አሏቸው በመጽሃፍ ቅዱስ ስውጥ፤ካቶሊኮች 73 እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን 81።እንግዲህ እኔ አሁን እዚህ የማወራው በመላው አለም ሁሉ ያሉ ክርስቲያኖች ስለሚጠቀሙበት የፕሮተስታንት ቤተክርስቲያን መጽሀፍ ቅዱስ ብቻ ነው።

ጥያቄ፤የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን”ኢትዮጵያ” የሚለውን ቃል ስህተት ሆኖ አግኝታው ከመጽሀፏ ውስጥ ስታስወግድና ስትቀይር ፥ የካቶሊኮችና ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪዎች ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የማመልከት የማሳሰብ ሙከራ ይኖራል?

መልስ፤መልካም። የፕሮተስታንት ቤተከርስቲያን የአለም ቤተክርስቲያናት ምክርቤት አካል ናት።ይህ ትርጉም ለክርስቲያኖች ሁሉ የጋራ መሆን እንዳለበት እናምናለን።ምክንያቱም መሰረታዊውን የክርስቲያን እምነት የሚቀበል ነው። እውነትን መሻት ነው።እውነት ይፋ ሆናለች። እውነትም ተጽፋለች።ስለዚህ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ አቢያተክርስትያናት ፤የኦርቶዶክስ እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያናት እንደ ትክክለኛ የመጽሀፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ይቀበላሉ ብለን እናምናለን።ምክንያቱም ለሁላችንም የጋራና መሰረታዊ በመሆኑ። እኔ ባመራር ደረጃ ያለ ስልጣን ላይ እይደለም ያለሁት። የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን እመራሮች ይህን ሀሳብ ለሌሎች ክርስቲያን ቸርቾች ሁሉ እንደሚያቀርቡ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ኦርቶዶክስና ካቶሊኮችን ጨምሮ።

ይህን አዲሱን ትርጉም ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል መወሰን የኦርቶዶክሶችም ሆነ የካቶሊክ ቤተክርስቲያናት የራሳቸው ጉዳይ ነው። እኛ በትክክለኛ ቋንቋ የተቀመጠ መጽሀፍቅዱስ ነው የምንጠቀመው። ለዚህም ነው ፕሮቴስታንት የተባልነው። እኛ ከሁሉም አቢያተክርስትያናት ጋር እንሰራለን ከሁሉም ጋር እንከባበራለንም። ግን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ እንበልና ኩሽ ህዝቦች ውስጥ ሄደው መስራት ከፈለጉ ኦሮሞ፤ሲዳማ ፤ከምባታ፤አገው ፤ሃዲያ፤ሶማሌ እና ሌሎችም፤ቤተክርስቲያኗ ይህን አዲሱን ትርጉም መቀበል አለባት።በሁለት ምክንያቶች ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያን እንደምታደርግ ተስፋ አደርጋለሁ። አንደኛ ፤ ትክክለኛው ስም “ኩሽ” ነበር እንጂ “ኢትዮጵያ” አይደለም። ሁለተኛ ፡ ከአንድ ክፍለ ህዝብ ጋር ወይም ከአንድ ሀገር ህዝብ ጋር የምትሰራ ከሆነ የዛን ህዝብ ባህሉን፤ ማንነቱን ማክበር አለብህ። ስለዚህ ኩሽ ህዝብ ውስጥ ሄደው የሚሰሩ አብያተክርስትያናት ሀላፊነት ነው ያን ስህተት አውቆና አርሞ መገኘት።

ጥያቄ፡ ይህ ለውጥ ወይም ይህ ትርጉም በራሳቸው በኩሽ ህዝቦች ላይ ምን አይነት ስነመለኮታዊ ለውጥ ያመጣል ብለው ያስባሉ?

መልስ፡ መልካም። ትልቅ ለውጥ ይኖረዋል። ሰዎች ጥያቄ መጠየቅ አለባቸው።” ማነው እጆቹን ወደእግዚአብሄር የዘረጋ?” ኢትዮጵያ እይደለችም ። ግን ኩሽ ነው። በጭፍን ኢትዮጵያ ናት ብለው የሚያምኑ ሰዎችን ሊቀበሉት ይፈታተናቸዋል። እውነት ትፈታተናለች። ነጻ ግን ታወጣለች።ክርስቲያን ሰባኪዎች ቃሉን እንዴት እንደሚተረጉሙና እንሚጠቀመበትም ለውጥ ይኖረዋል። እንደ ፓስተር እኔ ቆሜ ይህ ኩሽ ነው ስል ይህን ለመስማት የማይፈልጉ ላይቀበሉት ይችሉ ይሆናል ። ግን ምክንያትና ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ለምን እንደማይቀበሉት አስረጅ። ስለዚህ ሰዎች ይህን ለመረዳትና ሊቀበሉት ጊዜ ይወስድባቸዋል። ከፊሉን ሊያወዛግበው ከፊሉን ነጻ ሊያወጣው ይችላል። አንዳንዶች በትርጉሙ ደስተኞች ሆነው ይጠቀሙበታል ሌሎች ደስተኛ አይደሉም ይሆናል። የኔ ተስፋ ሁሉም ክርስቲያን ቸርቾች አዲሱን ትርጉም በደስታ ይቀበሉታል ነው። የተደበቀው አውነት ይፋ ሆኗል። ስለ ዚህ ሁሉም ሰው ደስተኛ ሊሆን ይገባል። መጽሀፍ ቅዱስን ከሂብሩ ወደ ግሪክ የተረጎሙት ሰዎች ለምን “ኢትዮጲስ” አሉን? ፤ፊታቸው የተቃጠለ ሰዎች” “ የተቃጠለ ፊት” የሚለው መጠሪያ ክብረ ነክና አዋራጅ ስድብ ነው። ፊታችን የተቃጠለ አይደለም። ጥቁር ነው በቃ። ጥቁር መሆን ምንም ስህተት የለበትም።አግዚ እብሄር ነው የፈጠረን። ጥቁሮች ነን ። አንደጥቁርነታችን አራሳችንን አንቀበለዋለን። ማናቸውም ቤተክርስቲያን እኔን ቢሰድበኝ ቤተክርስቲያኔ አልለውም። ይህ የማንነት ጉዳይ ነው። አባትህ ያወጣልህ ስም በባእዳን ቢለወጥ ያናድድሀል ። ማንነትህን ባህልህን ሁሉ ያወድመዋል። አዚህ የሆነው ነገር በትክክል ይህ ነው። የኩሽ ህዝቦች አራሳቸውን የተቃጠለ ፊት ክብለው አይጠሩም።

ኦሮሞ ፤ ሶማሌ፤ አፋር፤ እና ሌሎችም የኩሽ ህዝብቦች መሆናቸውን ታሪክ ይነግረናል። አንድም የገባው ፤ የተገለጠለት የኩሽ ሰው ግሪኮች ለኛ በሰጡን ክብረነክ አዋራጅ ስም ደስተኛ አይደለም።የመጀመሪያው ስማችን ኩሽ መጠሪያችን እንዲሆን መልሰን ለመጠየቅ ደስተኞች ነን።ስለዚህ ለውጡ ይህ ነው።እንዳለ የኩሽ ህዝቦችን ታሪክ በትክክል ሊቀይረው ይችላል።የኩሽ ሰዎች ቋንቋዎች አሏቸው እና የሚኖሩበት መልክአምድራቸውም በደንብ የታወቀ ነው። ግን ኢትዮጵያ ከሚለው ቃል ጋር የሚዛመድ ህዝብም ፤ ቦታም ፤ ቋንቋም የለም። ባንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ ጥናት እንዳለ እሰማለሁ።መጨረሻ ላይ ይሄም ይቀየራል።ምክንያቱም ጥያቄ ያስነሳል።ኢትዮጵያ ማነው?ኢትዮጵያ ምንድነው?

ጥያቄ፤ በኢትዮጵያ በትምህርት ላቅ ባሉ (elite) ክፍሎችም ሆነ በሌላው ማህበረሰብ ዘንድ ማንነትን በተመለከተ የተጋጋሉ ክርክሮች ይስተዋላሉ።ብቸኛው ማንነታችን “ኢትዮጵያዊነት” ነው ብለው የሚከረከሩ አሉ።በሌላው በኩል ደሞ ቀዳሚው የጎሳ ማንነታችን ነው ኢትዯጵያዊነት ሁለተኛ ደረጃ ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ።ሌሎች ደሞ ጭራሽ ባጠቃላይ ትዮጵያዊ ማንነትን የማይቀበሉ አሉ። ለዚህ አነጋጋሪ ለሆነው የማንነትጉዳይ ይህ አዲሱ ትርጉም አስተዋጾ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?

መልስ፤ እውነት ነጻ ያወጣሃል ብየ አስባለሁ።የመጀመቲያው ስም “ኩሽ” ለመሆኑ ማስረጃ እስካለ ድረስ ቃሉ “ኢትዮጵያ” ነው ብሎ የሚያከራክር ምክንያት የለም።”ኢትዮጵያ” ብለው ሊጠሩን ያስቻላቸው ሳይንሳዊ ማስረጃ አያገኙም ይሆናል።ሳይንሳዊ ስል የአርኪዎሎጂ የስነቋንቋ እንዲሁም የታሪክ ማስረጃዎችን ማለቴ ነው።አሁን ስላለችው ኢትዮጵያ ታሪክ እንድነግርህ ፍቀድለኝ። ከ1900-1908 እስከዚህ ጊዜ ድረስ የዛሬዪቱ ኢትዮያ ስነ መልክአምድር (ካርታ) አልነበረም።ከዚያ በፊት ህዝቡ ኦሮሞ፤አማራ፤ሲዳማ ፤ አፋር፤ትግሬ ወዘተ….ይባሉ ነበር።

አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ካርታ ዳር ድንበር የተቋቋመው ፤ የተመሰረተው ፤ በዳግማዊ ሚኒሊክ የአቢሲኒያው ንጉስ ነው።የደቡብን ኩሾችና ሌሎችንም በቅኝ የያዘውና አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ግዛት የፈጠረ።እስከ 1931 ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ህጋዊ እውቅና አላገኘም ነበር።ከ1931 አም በፊት ሃገሪቱ አቢሲኒያ ነበር የምትባለው። እና አቢሲኒያውያን እራሳቸውን የሴም ህዝብ ብለው ነው የሚጠሩት።ንጉስ ሃይለስላሴ ናቸው በ1931 አም በመጀመሪያ ህገመንግስታቸው ውስጥ አቢሲኒያ የሚለውን ስም ጥለው ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ያጸደቁት።

ኩሽና ሌሎችም ህዝቦች በዚህ የአፍሪካ አህጉር ለሺዎች አመታት እየኖሩ በነበረበት እንግዲህ ጥያቄው እንደምን አንድ ሃገር እንዳለ ስሙ ተለውጦ “ኢትዮጵያ” ይባላል? መልካም ። ግሪኮች “ኢትዮጲስ” አሉ፤ ምክንያቱም ህዝብ ኢትዮጵያ ስለሚባል ግዛት አፈታሪክ ያወራ ነበርና። በትክክልም የኩሽ ስለነበረ ግዛት። ስለ ንግስት ሳባ ነበር የሚናገሩት። ኩሽ እንጂ ሴማዊት ስላልነበረች ሰው። ግዛቷም የኩሽ ግዛት እንጂ ኢትዮጵያ አልነበረችም። የአካዳሚክ ሰዎች ፤ ታሪክ አጥኚዎች፤ የስነመለኮት ሰዎች (የሀይማኖት ጠበብት) ይህን በደንብ መረዳት አለባቸው።ፖለቲከኞች ደግሞ እውነትን መያዝና ያለፉ ስህተቶችን ማረም ይገባቸዋል። በጣም ብርቱ ነገር ነው። ስሜ በንቲ ነው። ስለዚህ ድንገት ስሜ ወደ ጄምስ ቢለወጥ ደስ አይለኝም።

የዘር የጾታ እና ማናቸውም አይነት ልዩነት መታረም ነው ያለበት።ለምሳሌ “ባሪያ ለጌታህ ታዘዝ” የሚለው ነገር መቀየር አለበት። ጥቁር የተረገመ ነው ለማለት ካምና ትውልዱ ተረግመዋል የሚል ጽንሰ ሃሳብ አለ።ስለዚህ የጥቂር ህዝብ ችግር ሁሉ የእግዜብሄር እርግማን ነው። ይህ መቀየር መወገድ አለበትእንዳለ። ምክንያቱም እግዜብሄር ጥቁሩን ህዝብ ረግሞታል ብየ አላምንም። ይልቅስ ተርጓሚዎች የጥቁሮች አባት ካምን የተረገመ ብለው ሲጠቅሱ በስህተት የተሞላ አድሎአዊነታቸው ነው። ካምን የረገመው እግዜብሄር የክርስቲያን አምላክ ሊሆን እንደማይችል አምናለሁ።ይህ ስህተት ሆን ተብሎም ይሁን በሌላ ምክንያት ይደረግ ፤ የመጽሃፍ ቅዱስን ቅዱስነት ውድቅ አያደርገውም።ነገር ግን ስህተቶችን ማረምና እውነተኛ በሆነ አሉታዊ መንገድ ማቅረብ የበለጠ መጽሃፍ ቅዱስን ያበለጽገዋል።

ጥያቄ፥ ያሉኝ ጥያቄዎች እነዚሁ ናቸው ሌላ የሚጨምሩት ነገር ካለ?

መልስ፤ ለጥያቄዎችህ አመሰግናለሁ። እውነትን ለመናገር ደስተኛ ነኝ እናም አዲሱን ትርጉም የሚያነቡ ሰዎችን ሁሉ የምጠይቀው ነገር እርምቱ እውነት አከሆነ ደረስ እንዳይደነግጡ ነው። ገንቢ በሆነ ውይይት መሳተፍና አዲሱን ትርጉም በሰዎች መካከል በሰላም አብሮ መኖር እንዲቻል አርገን ጥቅም ላይ ለማዋል መሞከር አለብን።ለውጡ አሉታዊ እርምጃ ሆኖ እንዲታይና በክርስቲያኖች ሁሉ ጥቅም ላይ እንዲውል ተስፋ አደርጋለሁ።

በመላው አለም የመጽሃፍ ቅዱስ ተርጓሚ ማህበረሰቦችም እነዚህንና ሌሎችንም ስህተቶች አርመው ለወደፊት በትርጉም ስራ ወቅት መድሎአዊ ቃላትን ለማስወገድ እንደሚሰሩ ተስፋ አደርጋለሁ።ሁሉን አቀፍ እንዲሆኑም አበረታታቸዋለሁ።ምክንያቱም እግዜብሄር የፍቅር አምላክ ነውና የፈጠረውን ሁሉ የሚወድ። በራሱ ፍጡራን መካከል ልዩነትን የሚፈጥርበት ምክንያት የለውም።

አማኞችም ለለውጥ ልቦናቸው ክፍት መሆን አለበት። በግልጽም ሊወያዩበት ይገባል። አውቃለሁ ሀይማኖት በጣም ስሜትን የሚነካ ነገር ነው። በመላው አለም ያሉ ሀይማኖቶች በሰላም ተቻችለው አብረው እንዲኖሩ ለማድረግ ሲባል፤መነጋገር አንዳችን ሌላችንን የመረዳት ልምድ ማዳበርና አሉታዊ አስተሳሰብን ማራመድ የሰው ልጅ ባህል አንዱ ገጽታ ነው። ያም ምኞቴና ጸሎቴም ነው።

LEAVE A REPLY